002

በዓለ ሆሣዕና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ የሆሣዕና በዓል ነው፡፡ ስለዚህ በዓል አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፤ ከትንቢቶቹም አንዱ እንደሚከተለው ተጠቅሷል፡፡ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያና በአህያይቱ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” /ትን. ዘካ. 9፡9/

002

ከዚህም ጋር ስለበዓለ ሆሣዕና አራቱም ወንጌላውያን ጽፈዋል፡፡ ይህም፡- ማቴ. 21፡1-11፣ ማር. 11፡1-10፣ ሉቃ. 19፡28-40፣ ዮሐ. 12፡12-15 አራቱም ወንጌላውያን የጻፉት የበዓሉ ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጻ_ል፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፡፡ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ገና ማንም ያልተቀመጠባት አህያ ከውርንጫይቱ ጋር ታሥረው ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማንም ስለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ አላቸው፡፡ የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፡፡ እነርሱም አህያዋንና ውርንጫዋን ሲፈቱ የአህያው ባለቤት አህዮቹን ስለምን ትፈቷቸዋላችሁ? አላቸው እነርሱም ለጌታ ያስፈልጉታል አሉ ፈቀደላቸው ወዲያው አመጡለት፡፡ የታሠሩትን ፈትታችሁ አምጡልኝ ማለቱ ሰው ሁሉ ከኃጢአት ማሠሪያ የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ ነው፤ ደቀ መዛሙርቱም ልብሳቸውን በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ጎዘጎዙ የዚህም ምስጢር ኮርቻ ይቆረቁራል ልብስ አይቆረቁርም የማትቆረቁር ሕግ ሠራህልን ሲሉ፤ አንድም ልብስ በአካል ያለውን ነውር ይሸፍናል አንተም ከባቴ አበሳ /በደልን የምትሸፍን/ ነህ ሲሉ ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአህያዋና በውርንጭላዋ ላይ በጥበብ በአንድ ጊዜ ተቀምጦባቸዋል ለእርሱ የሚሳነው ነገር የለምና፡፡ በአህያ የተቀመጠበት ምክንያት ደግሞ ቀድሞ ነቢያት ዘመነ ጸብዕ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው ይታያሉ፡፡ ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉና ዘመነ ሰላም ደረሰ ሲል ትንቢቱን ባወቀ አናግሯል ምስጢሩም በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም እሱም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝ አልታጣም ሲል ነው፡፡ ሲሄዱም ሕዝቡ ልብሳቸውን በመንገድ አነጠፉ፡፡ እንኳንስ አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ነው፡፡ እንዲሁም ሕዝቡ፣ ሕፃናቱ ሳይቀሩ ዘንባባ ይዘው የሚቀድሙትም የሚከተሉትም “ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር” /ለዳዊት ልጅ መድኃኒትን መባል ይገባዋል፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው/ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ያመሰግኑ ነበር፡፡ ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው፡፡ የዘንባባው ምስጢርም፡- አብርሃም ይስሐቅን ይስሐቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፤ እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ ዘንባባ ይዘው እግዚአብሔርን አመስግነዋልና በዚህ መሠረት ሕዝቡ፡- የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲሄድ ዘንባባ ይዘው አመስግነውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሲያመሰግኑ ከሕዝቡ መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ መምህር ሆይ፡- ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ መልሶም እላችኋለሁ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግናሉ አላቸው፤ ድንጋዮች ሳይቀሩ አመስግነውታል፡፡ (ሉቃ. 19፥40)

በዚህ መሠረት ይህ በዓል የምስጋና በዓል ነው፡፡ እኛም ፈጣሪያችንን ሁልጊዜ ማመስገን አለብን የተፈጠርነውም ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ነው፡፡ ስሙን ለመቀደስ ማለት ስሙን ለማመስገን ማለት ነው፤ ክብሩን ለመውረስ ማለት ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ማለት ነው፡፡ የተፈጠርነው ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ስለሆነ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል፡፡ ምስጋናውም በፍጽም እምነት፣ በቅንነትና በንጹሕ ልብ መሆን አለበት፡፡ “እባርኮ ለእግዚአብሔር በኵሎ ጊዜ ወዘልፈ ስብሐቲሁ ውስተ አፉየ” /እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ ምስጋነውም ዘወትር በአፌ ነው/ /መዝ. 33፡1/

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመስግነን መንግሥቱን ለመውረስ እንድንችል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም የቅዱሳን አማላጅነታቸው አይለየን፡፡

ለበዓለ ሆሣዕና ያደረሰን አምላክ ለብርሃነ ትንሣኤውም በሰላም ያድርሰን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ከላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ /ቀሲስ/ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ

‹‹ጥንተ ስቅለት››

የዓለም መድኅን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ በቀራንዮ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሕይወቱን ለዓለም ቤዛ፣ አድርጎ የሰጠው መጋቢት ፳፯ ቀን ፴፫ ዓ.ም እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ይህ ቀን ስለክርስቶስ ሕማም፣ ስለመከራ መስቀሉና ስለሞቱ የተነገሩት ትንቢቶችና ምሳሌዎች ሁሉ የተፈጸሙበት፤ ሰማያዊ አምላክ ስለሰው ልጆች ፍቅር ሲል ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራዎችን የተቀበለበትና በሞቱ ሞትን ሽሮ የአዳምን ዘር ሁሉ ከሞት ሞት ያዳነበት፣ ለዓለሙ ሁሉ ፍቅሩን የገለጠበት፣ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙም ዓለምን ነፃ ያወጣበት፣ በአጠቃላይ ዐሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል በትዕግሥት ተቀብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በገዛ ፈቃዱ የለየበት የስቅለቱና የሞቱ መታሰቢያ የሚከበርበት ቀን በመሆኑ ጥንተ ስቅለት ተብሎ ይጠራል፡፡
በዓሉም በዓለ መድኃኔዓለም እየተባለ በየዓመቱ በመድኃኔዓለም ስም በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ታቦተ ሕጉ እየወጣና ዑደትም እየተደረገ በታላቅ ክብር ሲከበር የኖረ ታላቅ መንፈሳዊ በዓል ነው፡፡
መድኃኔዓለም ማለት ምን ማለት ነው? ክርስቶስ፣ ማለት መሲህ፤ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት፣ አማኑኤል ማለትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ተብሎ እንደሚተረጎም ሁሉ መድኃኔዓለም ማለትም ዓለምን ሁሉ የሚያድን የዓለም መድኃኒት ማለት እንደሆነ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንማራለን፡፡
ዓለም የዳነውም ከላይ እንደተገለጠው በመስቀሉ ላይ በአፈሰሰው ደሙና በሞቱ አማካይነት በተገኘው ጸጋ ነውና የጥንተ ስቅለቱና የመስቀሉም ምሥጢር ዓለምን የማዳን ምስጢር ስለሆነ የጥንተ ስቅለቱ የመታሰቢያ በዓል በሚከበርበት በመጋቢት ፳፯ ቀን ምእመናን ሁሉ በቤተክርስቲያን በመገኘት በእሱ ደም ዓለም የዳነ መሆኑን በሚገልጠው መድኃኔዓለም በተሰኘው ስሙ እየተማጸኑና ዓለምን ለማዳን የተቀበለውን መከራ መስቀል እያስታወሱ በዓሉን በድምቀት ያከብሩታል፡፡
መድኃኔዓለም የሚለው የጌታችን ስም ቃሉ ራሱ የድኅነት ወይም የመዳን ቃል እንደሆነ በምሥጢር የሚያስረዱት ቅዱሳት መጻሕፍት ብዙዎች ናቸው ከእነዚህም መካከል፡ –
፩ኛ. ‹‹እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር›› ‹‹እግዚአብሔር ዓለም ከመፈጠሩና ከተፈጠረም በኋላ ዘለዓለማዊ ንጉሥ ነው፡፡ የምድር ማዕከል በሆነች ቀራንዮም መድኃኒትን አደረገ›› የሚለው የነቢዩ ዳዊት ትንቢት አንደኛው ማስረጃ ነው (መዝ. ፸፫ ፥ ፲፬)፡፡
፪ኛ. ቅዱስ ሊቃስ እንደ ጻፈው ክርስቶስ በተወለደበት ሌሊት የጌታችን ክብር በዙሪያቸው ሲያበራ ያዩ እረኞች ታላቅ ፍርሃትን ከመፍራታቸው የተነሣ፤ ሰማያዊ መልአክ ‹‹ኢትፍርሁ እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ዜና ዘይከውን ፍስሐ ለክሙ ወለኵሉ ሕዝብ እስመናሁ ተወልደ ለክሙ መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ›› ‹‹እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ተወልዶላችኋልና፤›› በማለት የነገራቸው ቃል ትልቅ ማስረጃ ነው ለማለት ይቻላል (ሉቃ. ፪ ÷ ፲ – ፲፩)፡፡
መጋቢት ፳፯ ቀን የሚከበረውን የመድኃኔዓለምን በዓል ጥንተ ስቅለቱ ነው ብለን ስንናገርና የስቅለቱን መታሰቢያ በዓል ስናከብር በዚሁ ቀን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈፀሙትን ጸዋትወ መከራዎችና እሱ በመስቀል ላይ እያለ በሰማይና በምድር የተፈጸሙትን ተአምራት አብረን ልናስባቸውና ልብም ልንላቸው ይገባል፡፡
በእሱ ላይ ከደረሱት ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራዎች ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል፡ – የአይሁድ መማክርት የመከሩበት ከንቱ ምክርና በዕለተ ረቡዕም እንደዚሁ በአይሁድ ሸንጎ የተወሰነበት ጠማማና የተዛባ ፍርድ የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ቀጥሎም መጋቢት ፳፮ ቀን የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ማታ ለ፳፯ አጥቢያ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻውን እራት መግቦ፣ ምሥጢረ ቊርባንን ከመሠረተ በኋላ ሌሊቱን በሙሉ በአይሁድ ጭፍሮችና በሊቃነ ካህናት ሎሌዎች የደረሰበት ስቃይና መንገላታት እጅግ የሚያሰቅቅ ነው፡፡
ጭፍሮቹ በይሁዳ መሪነት እሱን ይዘው በቁጥጥራቸው ሥር ከአደረጉ በኋላ እንደታሰረ በመጀመሪያ ወደ ሐና ዘንድ ከዚያም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ፣ ቀጥሎም ወደ ጲላጦስ ከጲላጦስ ደግሞ ወደ ሔሮድስ ከዚያም እንደገና ወደ ጲላጦስ እያመላለሱ እንዲንገላታና እንዲሰቃይ አድርገውታል፡፡ በዚያውም ላይ እየሰደቡትና እየዛቱበት ፊቱን በጥፊ ራሱን ደግሞ በዱላ ይመቱት እንደነበረ ቅዱሳት መጻሕፍት በሰፊው ያስረዳሉ (ማቴ. 27÷27-31)፡፡
መጋቢት ፳፯ ቀን በዕለተ ዓርብ ከሦስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት የተቀበላቸው መከራዎችም እጅግ በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡ ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል፣ በሚያሰቅቅና በሚዘገንን ሁኔታ በጅራፍ ተገርፎአል፤ መስቀሉን ተሸክሞ በቀራንዮ ተራራ እየወደቀ እየተነሣ፣ የገዢው የጲላጦስ ወታደሮችም እያዳፉት፣ ርኩስ ምራቃቸውንም እየተፉበትና እያፌዙበት ወደ ተራራው እንዲወጣ ተደርጎአል፡፡
ስለእሱ የተጻፈው የነቢያት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ልብሱን ገፈው ከለሜዳ አልበሰውታል፡፡ በልብሱም ላይ ዕጣ ተጣጥለው ተካፍለውታል፤ የእሾህ አክሊል ጕንጕን በራሱ ላይ በማድረግ የሰማይና የምድር ንጉሥ እንዳልሆነ ሁሉ ‹‹ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን››! እያሉ ተሳልቀውበታል፡፡
በመጨረሻም ጐኑን በጦር ወግተውታል፡፡ እጆቹን እና እግሮቹን በ፭ ችንካሮች (ቅንዋት) ቸንክረው በመስቀል ላይ ሰቅለውታል፡፡
በመስቀል ላይ እያለም ሰባት ዐረፍተ ነገሮችን ተናግሮአል፤ ከእነዚህም በጣም የሚያስደንቀው ጠላቶቹ እያሰቃዩት፣ እያንገላቱትና እየገደሉትም ሳሉ ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው›› ሲል የተናገረው ቃል ሲሆን የመጨረሻውም ‹‹እነሆ ሁሉም ነገር ተፈጸመ›› በማለት ከተናገረ በኋላ ወዲያውኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በራሱ ፈቃድ ለይቶ ሞት የማይገባው አምላክ ለሰው ልጆች ሕይወት ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ መስጠቱ ነው፡፡
የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በክርስቶስ ላይ ያቀረቡት መሠረተ ቢስ ክስና ውንጀላ በታሪክ ሂደት በጣም ሲያስገርም የሚኖር ነው ይኸውም፡ –
፩ኛ. ለቄሳር ግብር መክፈል አይገባም በማለት አስተምሮል፤
፪ኛ. ዕለተ ሰንበትን ሽሮአል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሏል ወዘተ አያሉ በሐሰት የሚመሰክሩ ምስክሮችነ በገንዘብ አባብለውና አደራጅተው በሐሰት በማስመስከር ምንም ዓይነት ወንጀል ያልፈጸመው ንጹሐ ባሕርይ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጀለኞች መካከል በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት፤ በርባን የተባለው ወንጀለኛ ግን ከእስር እንዲፈታላቸው ለጴንጤናዊው ጲላጦስ ያቀረቡት ልመናና ገዥው ጲላጦስም ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጀል እንዳልፈጸመ ራሱ እየመሰከረና እያረጋገጠ፣ ሚስቱም በሕልም ተረድታ እጁን በዚህ ጻድቅና ንጹሕ ሰው ደም እንዳያስገባ እያስጠነቀቀችው ‹‹ኢየሱስን ስቀለው በርባንን ፍታው›› የሚለውን ጩኸታቸውን በመስማትና እነሱን በመፍራት ብቻ ‹‹እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› በማለት እጁን ከታጠበ በኋላ ራሱ በጅራፍ ገርፎ እናንተ እንደ ሕጋችሁ ወስዳችሁ ስቀሉት ብሎ ለጠላቶቹ አሳልፎ በመስጠት የፈጸመው ስሕተትና በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ የሰጠው የተዛባ ፍርድ እጅግ የሚያሳዝን በመሆኑ ከጥንተ ስቅለቱ ጋር በትዝብት አብሮ ሲታወስ ይኖራል፡፡
ክርስቶስ የተሰቀለው መጋቢት ፳፯ ቀን ከሆነ እንደገና በሌላ ጊዜ በዓለ ስቅለትን ማክበር ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ በአእምሮአችን ሊጉላላ ይችል ይሆናል፡፡ በእርግጥ ጥንተ ስቅለቱን ማክበር በበቃ ነበር፡፡ ሆኖም ክርስቶስ የተሰቀለው በዕለተ ዓርብ ሲሆን ከመቃብር የተነሣውም በዕለተ እሑድ በመሆኑ ስቅለት ከዕለተ ዓርብ፣ ትንሣኤም ከዕለተ እሑድ፣ ዕርገት ደግሞ ከዕለተ ሐሙስ እንዳይወጡ፤ ሌሎቹም በዓላትና አጽዋማት በተወሰነላቸው ቀን እንዲውሉ ማድረግ ይቻል ዘንድ የቀድሞ አባቶችና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሰባት አዕዋዳት አዘጋጅተው እና ቀምረው ሁሉም ሥርዓቱን ጠብቆ ድርጊቱ በተፈጸመበት ቀን እንዲከበር የወሰኑ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት ፳፯ ቀን በየዓመቱ እየታሰበ በዓለ ስቅለቱ ደግሞ ከሰሙነ ሕማማቱ ጋር በዓመት አንድ ጊዜ በዕለተ ዓርብ በጾምና በጸሎት እንዲሁም በአክፍሎትና በስግደት እንዲከበር በማድረግ ሕግና ሥርዓት ስለሠሩ በዚሁ መሠረት ሲፈጸም ኖሯል፡፡ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡
ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ የሆነው የጌታችን የጽንሰቱ በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበርበት ቀን ከመሆኑ የተነሣ በዓሉን በዓል ተጭኖት ነው እንጂ ፫ኛው ቀን መጋቢት ፳፱ኝም ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣበት ጥንተ ትንሣኤ በመሆኑ እንደጥንተ ስቅለቱ ሁሉ ጥንተ ትንሣኤውም ከበዓለ ጽንሰቱ ጋር አብሮ የሚታሰብ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባንም፡፡“ወስብሐት ለእግዚአብሔር”

ሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድማገኘሁ

መልካም ባልንጀራ

ምስጢር የሚያወያዩትን አብሮ የሚሠሩትንና ጧት ማታ የሚገናኙትን እንዲሁም አብሮ አደግየሆነውን ሰው ባልንጀራዬ ነው ብሎ መናገር የተለመደ ነው፡፡ ዛሬ ለኔ ነገ ላንተ እየተባባሉ አብረው ከሚውሉት፣ ከሚያመሹት ጓደኞቻቸው ሌላ ባልንጀራ ያለ የማይመስላቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡ በመሠረቱ አብሮ መብላትና መጠጣት ወይም በአንድ ላይ ተምሮ ማደግና አብሮ መኖር ይልቁንም ትንሽ ትልቁን ክፉና ደጉን ምስጢር መካፈል ባልንጀራ ሊያሰኝ ቢችልም ይህ ብቻ ራሱ የፍቅር መመዘኛና መለኪያ ይሆናል ማለት ዘበት ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ የተመሠረተው ፍቅር አብዛኛውን ጊዜ በጥቅም ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን ሰብአዊ ርኅራኄና ከልብ የመነጨ መንፈሳዊ ስሜት የተዋሐደው ሊሆን አይችልምና ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፤ በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር፣ የባልንጀራህን ሚስት ቤትና ንብረት በአጠቃላይ የባልጀራህን ገንዘብ ሁሉ ማንኛውንም አትመኝ” የሚለውን ሕግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡላቸውና በባልንጀራቸው ላይ ክፉ ሥራ እንዳይሠሩ ትምህርት ሲሰጧቸው ባልንጀራዬን እንዴት እክዳለሁ? እንዴትስ ተንኮል እፈጽመበታለሁ? በማለት ራሳቸውን ለባልንጀራቸው ታማኝ በማድረግ ሊናገሩና ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን የተፈጥሮ ጓደኛቸው የሆነውን ሰብአዊ ፍጡር ሲያሳዝኑትና ሲያስቀይሙት ይታያሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ክፉ ተግባር በሰዎች ላይ መፈጸም “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” የሚለውን መጣስ ነውና ይህ ኃጢአት ነው ሲሏቸው ደግሞ ባልንጀራዬ ማን ነው? የማላውቀው ሰውስ እንዴት ባልንጀራዬ ይሆናል በማለት ድርቅ ብለው ይከራከራሉ፤ የሚበላና የሚጠጣ የጽዋ ጓደኛ ከዚህም ሌላ በሀብትና በእውቀት ተመጣጣኝ ሆኖ ውለታ የሚውልና ብድር የሚመልስ ወይም በሥጋ ተዛምዶ የሚቀርብና የሀገር የወንዝ ልጅ የሆነ አፈር ፈጭቶ ውኃ ተጎንጭቶ አብሮ ያደገ ወይም በአንድ ትምህርት ቤት አብሮ የተማረ በሥራና በጉርብትና ምክንያት ወቅታዊ ፍቅር የመሠረተና ምስጢር የተጫወተ … ወዘተ ብቻ ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ግን “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” ሲል የተናገረው ማንኛውም ሰው በተፈጥሮ የሚመሳሰለው ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ባልንጀራው መሆኑን አውቆ አንዱ የሌላውን መብት በመጠበቅ እርስ በርሱ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ በሰላምና በደስታ እንዲኖር ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከሰዎች መካከል እኔን አይመለከተኝም ሳይል አንዱ ሌላውን እንዲረዳው ነው፡፡ ይህም አባባል ባልንጀራ በወገን፣ በጾታ፣ በጎሳ፣ በዘርና በመሳሰለው ጠባብ አስተሳሰብ ሳይወሰን እያንዳንዱ ሰው ለሌላው ሰው ወገኑና ባልንጀራው እንዲሁም ከአንድ ፈጣሪና ከአንድ አባት የተገኘ የተፈጥሮ ወንድሙ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ላይ እንደተጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተማር ላይ ሳለ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው አስቦ፡- መምህር ሆይ የዘለዓለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? በማለት በጠየቀው ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? አለው፡፡ ሕግ አዋቂውም መልሶ፡- ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም ኃይልህ በፍጹም ሀሳብህ ውደድ ባልንጀራህንም እንደራስህ ውደድ ሲል መለሰ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም እውነት መልሰሀል ይህንን ብታደርግ በሕይወት ትኖራለህ ሲል ነገረው፡፡ ነገር ግን ሕግ አዋቂው ራሱን ከፍ አድርጎ በመመልከት ባልንጀራዬ ማን ነው? ሲል እንደገና ጠይቋል በዚህ ጊዜ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደጉና ሳምራዊ ታሪክ ከተረከ በኋላ “አንተም እንደዚሁ አድርግ” በማለት ለሰዎች ሁሉ መልካም መሥራትና እርስ በእርስ መዋደድ እንደሚገባ አስረድቶታል፡፡

እንግዲህ ባልንጀራ የሚባለው ባገኙ ጊዜ ብቻ አብሮ በልቶ ጠጥቶ በችግር ጊዜ ወደኋላ የሚሸሽ ሰው ሳይሆን “ባልንጀራህን እንደራስህ ወደድ” በሚለው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት የችግረኞችንና ጉዳተኞችን ችግር እንደራሱ ችግር በመቁጠር ውለታና ብድር ሳይሻ ሁሉንም በእኩልነት ተመልክቶ በጤናም ሆነ በሀብት ወይም በእርጅና ምክንያት የተቸገሩትን ሁሉ በአቅሙ መጠን የሚቻለውን የሚረዳ ነው፡፡ ከዚህም ሳምራዊ ሰው የምንማረው ይህንኑ ነው፡፡

እኛም እንደደጉ ሳምራዊ ሰው በዘመናችን ሁሉ ለሰዎች መልካም አድርገን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ፮ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

ቅዱሱሳን ፓትርያርኮቻችን በበዓሉ ላይ ተገኝተው በዓሉን ሲያከብሩ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፬ኛ ፓትርያርክ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ ከ34 በላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የእስልምና ዋና ሐላፊ ሸክ አህመድ፣ የቤተክህነት ሠራቶኞች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በርከት ያሉ ምእመናንና እንግዶች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በደማቅ መልኩ የ፮ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በዓል ተከብሯል። በዕለቱ  የመርካቶ ቅዱስ ራጉኤል ሊቃውንት “ብፅዕት ከርስ እንተፆረተከ፣ ወብፁዓት አጥባት እንተኃጸናከ፣ ወበእንተዝ ቅዱስ ማትያስ ፓትርያርክ አብያተ ክርስቲያናት አፍቀራከ…እያሉ ያሬዳዊ ዝማሬ ሲያቀርቡ፣ የሰንበት ት/ት ቤት መዘምራንም  “ ብፁዕ ወቅዱስ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጸሎትከ ትኩነነ… የሚል መዝሙር አቅርበዋል።

በመቀጠልም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨውና ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በዓሉን አስመክተው ንግግር አድርገዋል። ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ እንኳን ለዚህች ፮ኛ ዓመት በዓለ ሢመትዎ በሰላም አደረሶት በማለት፣ ከሁሉም ቀድማ የነበረች ቤተክርስቲያናችን፣ የራስዋ ጳጳስና ፓትርያርክ ባልነበረባት ጊዜ በትግል ቆይታ እነሆ በእግዚአብሔር ፈቃድ በራሷ ጳጳሳት መተዳደር ከጀመረች ከአምሳ ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። በቅርቡ የተደረገው የእርቅና የአንድነት ጉባኤም  ደስ የሚያሰኝ ነው፤  አሁንም አጠናክረን በመቀጠል ቤተክርስቲያናችን በአንድነትና በፍቅር መያዝ አለብን ብለዋል።

ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት በዓሉን በበዓሉ ላይ ተገኝተው በዓሉን ሲያከብሩ

በመጨረሻም፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ጋብዥነት፣ የካህናት አለቃ የምእመናን ወዳጅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ በዓል ያደረሰን ከሁሉ በፊት እርሱ ይክበር ይመስገን ብለው እናንተም እዚህ የተገኛችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ብለዋል። በዛም ሰፋ ያለ አጥንትን ሰርስሮ የሚገባ ት/ት ሰጥተዋል፤ በተለይም የቤተክርስቲያን የወደፊት ዓላማ ምን መሆንና ምን መምሰል እንዳለባት፤ ወደኋላ መለስ ብለን አይተን፣ አሁን የት እንዳለን ተገንዝበን ለወደፊት ምን መሥራት እንዳለብን ራእይን የሚያሰንቅ  መልእክት አስተላልፈዋል።  ፍልሰተ ምእመናን አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ ላይ ያተኮረው ንግግራቸው፣ ክስተቱን ለመቀልበስ ቅዱስ ሲኖዶስ መሠረታዊ የሆነ የአስተዳደር፣ የሐዋርያዊ ተልኮ መርሐ ግብር፣ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ ሲስተም ዘርግቶ፣ የሰው ኃይል አስተዳደር አዘምኖ፣ሙሉ የምእመናን ጥያቄ የሚመልስ መሠረታዊ  የመልካም አስተዳደር ለውጥ ለማምጣት በቆራጥነት መሥራት አለበት። ይህንም የመሰለ ለውጥ እውን ለማድረግም የቤተክርድቲያኒቱን ምሁራን በሚገባ ማሳተፍና መጠቀም አለበት። የሃይማኖታቸው ፍቅር እንደ እሳት እያቃጠላቸው ስሕተቶች እንዲታረሙ ሐሳብና አስተያየት ለሚያቀርቡ፣ ቤተክርስቲያንን እንርዳ እናግዝ፣ እናገልግል የሚሉት ምሁራንና ሊቃውንትም ገንቢ ሐሳባቸውንና ዕውቀታቸውን ተቀብለን እናስተናግዳቸው ካሉ በኋላ በዚህ መንፈስ መግባባት ከተፈጠረ እየበዙ የመጡ ጩኸቶች ወደ ዝማሬ የማንለውጥበት ምክንያት አይኖርም በማለት አባታዊ ምክራቸውናን ለየት ያለ የወደፊቱ ራእያቸውን የሚያንጸባርቅ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ወደኋላ መለስ ብለህ ጉድለትህን ማየት ብልህነትና አስተዋይነት ነው፣ ችግሩ ለይተህ ማወቅም ግማሽ የችግሩ መፍትሔ እንደማግኘት ነው። ከላይ እንዳየነው ቤተክርስቲያናችን ራሷን እየቃኘች መሆኑን የሚያገናዝብ ነው። የተጠቀሱት ቁምነገሮች በተግባር ከዋሉ ጥሩ የሚባል ለውጥ እንደሚገኝም አያጠራጥምና እኛም በጉጉት እየጠበቅን የበኩላችን እንወጣለን ቶሎም ወደ  ትግበራ እንዲሸጋገር ያስፈልጋል !

የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በታችኛው መዋቅር የሚገኙትን የአድባራትና ገዳማት እንዲሁም የወረዳ ሠራኞች የሚሠሩትን ሥራ ለእነርሱ በመተው የቅዱስ ሲኖዶስ የሥራ ድርሻ በሆነው ነገር ላይ ብቻ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ይኸውም ትልቁንና የወደፊት የቤተክርስቲያናችንን ሕልውና የሚያረጋግጠውን ዘመኑን የዋጀ ሕገ-ደንብ፣ የአሥራር ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ እንዲሁም ጥናትና ምርምሮችን በማድረግና በማስደረግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከውድቀት ሊታደጋት ይገባል።

ከዚህም በተጨማሪ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን መሠረት በማድረግ ጣልቃ ገብነቱ ተወግዱ ሁሉን ልሥራው ማለቱም ተገቢ አለመሆኑን ተገንዝቦ ሕግ አውጪው አካል ሕግ የማርቀቅና የማውጣት፤ሕግ ተርጓሚው አካል ደግሞ የመተርጎምና የመተንተን፤እንዲሁም ሕግ አስፈፃሚው አካል የወጣውንና የተተርጎመውን ሕግ የማስፈፀምና አፈፃፀሙንም የመከታተል ሥራውን በተግባር ላይ ሊያውል ይገባል እንላለን፡፡

እንኳን ለ6ኛ ዓመት በዓለ ሢመትዎ በሠላም አደረስዎ

የሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል፡፡

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የዓብይ ጾም መግባትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ

በቤተክርስቲያንችን ቀኖናዊ ሥርዓተ እምነት መሠረት በጾምና በጸሎት ከምንዘክራቸውና ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ከምናስገዛበቸው አጽዋማት መካከል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ በአርዓያነት ያሳየን ጾመ ኢየሱስ ወይም ዓብይ ጾም አንዱ ነው፡፡

በዚሁ የገዳመ ቆሮንቶስ ጾም ወቅት የሰውን ልብ በእጅጉ የሚገዳደሩና ለውድቀትም የሚዳርጉ የኃጢአትና የበደል ምክንያቶች ሁሉ በክርስቶስ ባሕሪያዊ ገንዘብ በሆነው በኃይሉ ችሎት ከመንገዳቸው ወጥተዋል የሰይጣንም ሽንፈት ተረጋግጧል፡፡

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም ይህንን አስመልክተው በዛሬው ዕለት በርካታ ሊቃነ ጳጳሳትና የተለያዩ የሚዲያ አካላት በተገኙበት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ሥፍራ ተስጥቶት በሰፊ አገልግሎትና ጸሎት የሚዘከረውን  ዓብይ ጾም አገልጋዮችና ምእመናን እንዴት አድርገው መጾምና ማገልገል እንዳለባቸው ሰፊና ጥልቅ መግለጫ  ከመስጠትም ባሻገር ዘመኑ የጭካኔና የመለያየት እየሆነ ስለመጣ ክፉውን ለማስታገስ፤ ተቋማዊም ሆነ ሀገራዊ ችግሮቻችን ለመፍታትና ወደ አንድነታችን ለመመለስ ብቸኛው መፍትሔ ጾምና ጸሎት በመሆኑ አብዝተን እንድንጸልና እንድንጾም እንዲሁም እጆቻችንን ለምጽዋት እንድንዘረጋ አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላለፉ፡፡

የሀገረ ስብከቱ የሕትመትና ሚዲያ ክፍልም እየተቀበልነው ያለው ጾም ራሳችንን የምንገዛበት፤ለጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ የምናገኝበትና ከአምላካችንም ሆነ ከወገኖቻችን ጋር ያለንን መስተጋብራዊ ግንኙነት የምናጠናክርበት እንዲሆን እየተመኘን ቅዱስነታቸው  የተሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ጊዜ ሰጥታችሁ ሙሉውን ታነቡት ዘንድ ከታች ባለው ክፍል አስቀምጠናል፡፡

የምሕረት ጌታ የብርሃን አባት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“ እስመ ኅሊናሁ ለነፍስትነ ፀሩ ለእግዚአብሔር ውእቱ፤

      የሥጋችን አስተሳሰብ የእግዚአብሔር ጠላት ነው ”(ሮሜ ፰፡፯)

እኛ ሰዎች ከሁለት ነገሮች የተገኘን ውሕድ ፍጥረቶች መሆናችን ከእግዚአብሔር ቃል በተጨማሪ በየዕለቱ የምናሳየው እርስ በርሱ የተቃረነ ድርጊት ተጨባጭ ማስረጃ ነው፤

ከዚህ አኳያ ሰው ሁሉ ከአንድ ምንጭ የተገኘ በመሆኑ ከመንፈስና ከሥጋ የተገነባ ድንቅ ፍጡር ነው፤ ሥጋና መንፈስ በሰው ዘንድ በተዋሕዶ ይኑሩ እንጂ ፍጹም ስምምነት ያላቸው ነገሮች ግን አይደሉም፤ ይልቁንም በመካከላቸው ከባድ ተቃርኖ እንዳለ “እስመ መንፈስኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ ሥጋ ወሥጋኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ መንፈስ; መንፈስ ሥጋ የማይወደውን፣ ሥጋም መንፈስ የማይወደውን ይወዳል” በማለት ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡

የሁለቱ ነገሮች ተቃርኖ በዚህ ብቻ የሚያበቃም አይደለም፤ ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ አበጋዝና የሚያስገኙት ውርስም አላቸው፤ የሥጋዊ ምኞት ምንጭ ዲያብሎስ ሲሆን በባሕርዩ ለእግዚአብሔር የማይገዛ ስለሆነ የእግዚአብሔር ጠላት ነው፤ ለተከታዮቹም ሞትን ያወርሳል፤ የመንፈሳዊ ምኞት ምንጭ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ነውና በባሕርዩ ለእግዚአብሔር ታዛዥ; ተገዥና የዘላለም ሕይወትን የሚያወርስ ነው፤

ከዚህ አንጻር ሰው ለሥጋዊ ምኞቱ ተገዢና በሥጋዊ ፈቃድ ተሸናፊ በሆነ ጊዜ ለሥጋውና ለነፍሱ የሚተርፍ ጉዳትን እንደሚያከማች፣ በአንጻሩ ደግሞ ለመንፈሳዊ ምኞቱ ተገዢና ተባባሪ በሆነ ጊዜ ለሥጋውና ለነፍሱ የሚተርፍ ሀብተ ሕይወትን እንደሚያፈራ ዛሬም ግልፅ ሆኖ ይታወቃል፤ ለዚህም የቀዳማዊ አዳም ሥጋዊ ዝንባሌና መንበርከክ፣ የዳግማዊ አዳም (ክርስቶስ) መንፈሳዊ ምከታና ድል ማድረግ ተጨባጭ ማረጋገጫዎቻችን ናቸው፡፡

ቀዳማይ አዳም የዲያብሎስን ምክር ሰምቶ፤ ጣዕመ መብልዕን ሽቶ፣ ለፈቃደ ሥጋው አድልቶ፤ በራሱና በልጆቹ ነፍስና ሥጋ ላይ የሞት ውርስን አውርሶአል፤ ዳግማይ አዳም የተባለ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በተቃራኒው ጣዕመ መብልዕን ትቶ፣ በኃይለ መንፈስ ተዋግቶ ፣ የዲያብሎስን ፈተና በእግዚአብሔር ቃል መክቶ የአሸናፊነትና የዘላለማዊ ሕይወት ርስትን ለእኛ ለልጆቹ አውርሶአል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ የዚህ ዓለም ወዳጅ የእግዚአብሔር ጠላት ነው ሲል ሜዳው ሸንተረሩ፣ ሣሩ ደንጊያው ወይም ከተማው ገጠሩ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም በዚህ ዐውደ ሐሳብ ዓለም ተብሎ የተገለፀው ፍሬ ሐሳብ እግዚአብሔርን የሚቃወም ማንኛውም ፈቃደ ሥጋ ነው፤ ይህ ዓይነቱ ፈቃደ ሥጋ ለእግዚአብሔር የማይገዛ ብቻ ሳይሆን ጠላትም ነው፤ በሰው ላይም ሞትን የሚያመጣ ነውና “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ” ተብሎ ተጻፈ

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

        በነገው ዕለት የምንጀምረው የጾም ሱባዔ ሁለት ዓላማ ያለው ነው፤ ይኸውም አንደኛው ጌታችን በመዋዕለ ጾሙ ፈቃደ ሥጋንና የእርሱ አበጋዝ የሆነው ዲያብሎስን በፈቃደ መንፈስ ድል ማድረጉን ለማሰብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሥራው ሁሉ እንድንመስለው ባስተማረን መሠረት እኛም  በኃይለ ጾም መሣሪያነት እየታገዝን እንደሱ ፈቃደ ሥጋንና ዲያብሎስን በመዋጋት የፈቃደ ነፍስ ልዕልናን ለማረጋገጥ ነው፤ ይህንም ውጊያ በድል ለማጠናቀቅ የሥጋ መሣሪዎችን ጠንቅቆ ማወቅ አስፈላጊ ነው፤ ሥጋ ነፍስን የሚወጋባቸው የታወቁ መሣሪያዎች አሉት፤ ቅዱስ መጽሐፍ እነሱን እንደሚከተለው በዝርዝር አስቀምጦአቸዋል፣

        ይኸውም­፡-

 • ዝሙት                    – ቊጣ      
 • ርኵሰት                    – አድመኛነት
 • መዳራት                    – መለያየት
 • ጣዖትን ማምለክ             – መናፍቅነት
 • ምዋርት                    – ምቀኝነት              
 • ጥል                       – መግደል
 • ክርክር                     – ስካር
 • ቅንዐት                     – ዘፋኝነትና ይህንን የሚመስል ሁሉ ይላል፤

በማያያዝም እንደነዚህ ያሉትን የሚያደርጉ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ብሎ ይደመድማል፡፡

      ዲያብሎስ እነዚህ የጥፋት መሣሪያዎቹን ተጠቅሞ አዳምንና ሔዋንን ባሳተበት ስልት ሥጋችንን በማስጐምጀትና ጠቃሚ ነገሮች እንደሆኑ አስመስሎ እነሱን በኅሊናችን ውስጥ በማቀጣጠል ወደ መሥገርተ ሞት ወጥመዱ ይከተናል፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በየጊዜው የምንጾመው እነዚህ የሥጋና የዲያብሎስ የሆኑ መሣሪያዎችን የመንፈስ መሣሪያዎች በሆኑ፡-

 • በፍቅር፣                        – በቸርነት፣
 • በመንፈሳዊ ደስታ፣               – በእምነት፣
 • በሰላም፣                        – በበጎነት፣
 • በትዕግሥት፣
 • በየዋህነትና ራስን በመግዛት ለመሰባበርና ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

 ከላይ እንደ ተመለከትነው የመንፈስ ቅዱስና የዲያብሎስ መሣሪያዎች ምን ምን እንደሆኑ ተገንዝበናል፤ በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ በመላው ዓለም በተለይም ደግሞ በሀገራችን ያለውን የሁለቱ አሰላለፍ ምን እንደሚመስል ማስተዋሉ የሚከብድ አይሆንም፤ ሰው ሁሉ መንፈሳዊ ዕውቀቱን ተጠቅሞ፣ የዲያብሎስ መሣሪያ የሆኑትን ጥሎ፣ የመንፈስ ፍሬዎች ወይም መሣሪዎች የሆኑትን አንግቦ፣ ፈቃደ ሥጋንና ዲያብሎስን ቢመክት ኖሮ አሁን እየሆነ ያለው ሁሉ አይከሠትም ነበር፤

ነገር ግን “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ፤ ሰው በተፈጥሮ አዋቂና ክቡር ሆኖ ሳለ በተሰጠው ዕድል መጠቀም አላወቀበትም” ተብሎ በእግዚአብሔር ቃል እንደተገለፀው ያለመታደል ጉዳይ ሆኖ ሊሆን አልቻለም፤ ይሁንና ተወደደም ተጠላ በመጨረሻው ቀን ማለትም በጌታ ቀን ዲያብሎስና መሣሪያዎቹ በኃይለ መንፈስ መሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን ከገጸ ምድር ሙሉ በሙሉ መጥፋታቸው አይቀሬ መሆኑ ቅዱስ መጽሐፍ ስለሚነግረን እስከዚያውም ቢሆን በሚጠፋ ነገር ከምንጠፋፋ የማይጠፉትን የመንፈስ መሣሪያዎችን ጨብጠን በሕይወት መኖርን ምርጫችን ብናደርግ ከጥበበኞች ሁሉ የምንበልጥ ጥበበኞች እንሆናለን ፡፡

ለመጪው ሕይወት ብቻ ሳይሆን አሁን ላለንበት ጊዜያዊ ሕይወትም ቢሆን፡-

 • ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣
 • ከጥል ይልቅ ፍቅርን፣
 • ከቊጣ ይልቅ ትዕግሥትን፣
 • ከመናፍቅነት ይልቅ እምነትን፣
 • ከርኵሰት ይልቅ ቅድስናን፣
 • ከመግደል ይልቅ ማዳንን፣
 • ከአድመኝት ይልቅ ሰላምን፣
 • ከስካር ይልቅ ራስ መግዛትን፣
 • ከዘፋኝነት ይልቅ ዘምሮን እጅግ እንደሚበልጥ ሁላችንም እንስማማበታለን፤ ነገሩ እውነትና ዘላቂ ሐቅ ስለመሆኑ ከስምምነታችን የበለጠ ማስረጃ ሊገኝ አይችልም፤ ስለሆነም በዚህ የጾም ወቅት እነዚህን ለመተግበር ክርስቲያኖች በቀንም፣ በሌሊትም ሊተጉ ይገባል፡፡

በመጨረሻም

መዋዕለ ጾም ማለት ፈቃደ ሥጋን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለን ለፈቃደ ነፍሳችን ብቻ የምንታዘዝበት፣ የእግዚአብሔርን ድምፅ ብቻ እየሰማን ለእርሱ  የምንገዛበት ጊዜ ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅም ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት መሆኑን ተገንዝበን ከሁሉ በላይ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ነዳያን ወንድሞቻችንን  በመመገብና በማልበስ ሁሌ ከጎናቸው ሳንለይ ወርኃ ጾሙን እንድናሳልፍ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ወርኃ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው

በሰላም ያድርሰን

እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

 ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

የካቲት ፳5 ቀን ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የክፍል ኃላፊዎች የስድስት ወር ሪፖርት አዳመጠ

1003
Photo File

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራአስኪያጅ ቆሞስ አባ ሞገስ ኃ/ማርያም ፣ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወ/ሐና፣ የየክፍሉ ኃላፊዎች፣ የሀ/ስብከቱና የሰባቱ ክፍለ ከተሞች ሠራተኞች በተገኙበት በሀ/ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ የሁሉም ክፍል ኃላፊዎች የስድስት ወር ሪፖርት ቀርቧል። በሪፖርቱ ብዙ አመርቂ የሚባሉ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በአንጻሩ ደግሞ ብዙ ሊሠሩ የሚገባቸው ሳይሠሩ እንደቀሩና ለወደፊቱ ትኩረት ተሰጥቶባቸው በአግባቡና በጊዜው ተጠናቀው እንደሚቀርቡ ተገልጿል። ለገቢ ተብሎ ቤተክርስቲያንን የሚያስነቅፉ ነገሮችም መቅረት እዳለባቸው ተደምጧል። በገቢ ደረጀም ሀ/ስብከቱ በስድስት ወር ዕድገት ቢያሳይም ካለፉ ዓመታት ሲነጻጸር በስድስት ወር ጉድለት እንዳሳየ ተነግሯል። የክፍለ ከተሞች ሒሳብ አያያዝም መቀየርና መስተካከል እንዳለበትም በክፍል ኃላፊው አጽንኦት ተሰጥቶበታል።

 የሁሉም ሪፖርት ከተደመጠ በኋላ ስለ ቤተክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ሁኔታ ውይይት ተደርጓል። በተለይ በአሁኑ ሰአት አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው የአንዳንድ አብያተክርስቲያናት በተለያዩ ሰዎች መታሸግ የሀ/ስብከቱና የክፍላተ ከተሞች ራስ ምታት ሆኗል።በዚህ ጉዳይም ጠለቅ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን ጉዳዩን አስመልክቶ ከክፍላተ ከተማ ሥራአስኪያጆች እንደተደመጠው የችግሩ ፈጣሪዎች የቤተክርስቲያን ተልእኮ ያልገባቸው የአንዳንድ ካህናትና ሰባክያነ ወንጌል እጅ እንዳለበት ተናግረው፣ ተጨበጭ መረጃ ያላቸው መሆኑንም ገልጸዋል ። እነዚህ አካላት ሕዝቡን በማሳደም አብያተክርስቲያናት እንዲታሸጉ እያደረጉ መገኘታቸው አሳፋሪና አስነዋሪ፣ እንዲሁም ከአንድ የቤተክርስቲያን አገልጋይ የማይጠበቅ ኩፉ ሥራ መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን  ኮንነዋል።  

በመቀጠልም ሀ/ስብከቱና ክፍለከተሞች ተባብረው በአንድነት እጅና ጓንት ሆነው ካልሠሩ ችግሩ እንደሰደድ እሳት እየሰፋ መሄዱ የማያጠራጥር ጉዳይ መሆኑ ከተሰብሳቢዎች አንደበት ተሰምተዋል። ችግሩን ለመቅረፍና ዳግም እንዳይከሰት ተናብቦ መሥራት፣ የቅድመ መከላከል ሥራ ቢሠራና ውይይቶች በተደጋጋሚ ቢደረጉ የሚሉት ሐሳቦች እንደ መፍትሔ ቀርበዋል።

በሌላ መልኩ በአሁኑ ሰዓት የሀ/ስብከቱ ግቢ በባለ ጉዳዮች ተጨናንቆ መገኘቱ ሀ/ስብከቱን ዕረፍት የነሣ ሲሆን ችግሩ የሚቀረፈው ሀ/ስብከቱ ለክፍለከተሞች ሙሉ ሥልጣን ሰጥቶ ባለ ጉዳዮች ባሉበት የክፍለ ከተማ ጽ/ቤት እንዲዳኙ ሲደረግ ብቻ መሆኑን በሀ/ስብከቱ ዋና ሥራአስኪያጁ በአጽንኦት ተገልጿል።

ችግሩ ከክፍለከተማ በላይ ካልሆነ ማንኛውም ባለ ጉዳይ ክፍለ ከተማውን ጥሶ ወደ ሀ/ስብከቱ መምጣት እንደሌለበት በመግለጽ ክፍለከተሞች ከቅጥር፣ ሽግሽግና ዕድገት ውጪ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሙሉ የመሥራት መብት እንዳላቸውና በደብዳቤም ተገልጾ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

በመጨረሻም ዋና ሥራ አስኪያጁ ምክር አዘል የሆነ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ለቤተክርስቲያን ነቀርሳ የሆኑትን እንደነ ሙስና፣ ዘረኝነት፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ ክፋትና የመሳሰሉትን እጅ ለእጅ ተያይዘን ልናስወግዳቸው ይገባል፤ በነዚህ ርካሽ በሆኑ ድርጊቶች ክብራችንን፣ ንጽኅናችንን፣ ቅድስናችንን ልናጉድፍ አይገባም  ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።

እንዲህ ያሉ የውይይት መድረኮች በየግዜው ቢደረጉና ጠቃሜ የመፍትሔ ሐሳቦችን እየተለዩ በአፈጣኝ ወደ ትግበራ ቢገባ ችግሮች ተቀርፈው ሰላም እንደሚገኝ ምንም ጥርጥር የሌለው መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን።

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌልን አስመልክቶ በሥሩ ከሚገኙት ከገዳማትና አድባራት ስብከተ ወንጌል ሐላፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት አደረገ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኘው የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ስብከተ ወንጌልን አስመልክቶ  በስሩ ከሚገኙት የገዳማትና አድባራት የስብከተ ወንጌል ሐላፊዎች ጋር ሰፊ የሆነ ውይይት ያደረገ ሲሆን በስብሰባው ላይ የአንድነት ጉባኤ፣ የስብከተወንጌል ኮሚቴ  የሚጠበቅበትን ሥራ ለምን አልሠራም፣ ሥልጠናን እንዴት እንስጥ የሚሉት ታላላቅና ወቅታዊ የሆኑ አጀንዳዎች ተነስተዋል፡፡ አጀንዳዎቹ ለታዳሚዎቹ በክፍለ ከተማው የስብከተ ወንጌል ሐላፊ በመጋቤ ሐዲስ ዘለዓለም ቀርበዋል፡፡ መጋቤ ሐዲስ ዘለዓለም ጉባኤው እንዲካሄድ በተሰጣቸው ሐላፊነት መሠረት የራሳቸውን ትልቅ ጥረት አድርገዋል፡፡ በስብሰባው ላይ የክፍለ ከተማው ሥራ  አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ግርማም ተገኝተዋል፡፡ የአንድነት ጉባኤውን  አስመልክቶ ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ከሰባኪያኑ አንደበት ተደምጧል፤ ሰባኪያኑ በአንዳንድ አጥቢዎች ላይ መልካም የሆነ የአንድነት ጉባኤ እየተዘጋጀ የሚገኝ ሲሆን በአንዳንድ አጥቢያዎች ደግሞ እየተሠራበት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡ በሌላ መልኩ ይህ የአንድነት ጉባኤው በጾም ወቅት ብቻ ሳይሆን  ዘወትር ሊካሄድ ይገባዋል የሚል ሐሳብም ከታዳሚዎቹ ተነስቷል፡፡ የአንድነት ጉባኤው  ከተጠናከረ ብዙ ምዕመናን የእግዚአብሔርን ቃል ይማራሉ፣ የተሰጠንንም አደራ በአግባቡ እንወጣለን፣ ኢ-አማንያንም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ማምጣት እንችላለን የሚሉ ድምጾች ተሰምተዋል፡፡

ለአንድነት ጉባኤው በአንዳንድ አጥቢያዎች በጀት አለመመደብ፣ የሰበካ ጉባኤ ሕንጻ ቤ/ክርስቲያን ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ፣ ለወንጌል አገልግሎት ትኩረት አለመስጠትና የመሳሰሉት እንደ ችግር ተነስተዋል፡፡ ለእነዚህ ችግሮችም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተሰንዝረዋል፡፡

ከመፍትሔዎቹ መካከልም የወንጌል አገልግሎት ትልቅ ትኩረት ቢሰጥበት፣ ወጥ የሆነ የስብከተ ወንጌል መዋቅር ቢኖር፣ለስብከተ ወንጌል ቋሚ የሆነ በጀት ቢበጀት፣ የመድረክ ስብከት ላይ ብቻ ትኩረት ባይደረግ፣ ምዕመናንን በተለያየ መንገድ ብናስተምር የሚሉት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተጠቁመዋል፡፡

ይህን አስመልክቶ የክ/ከተማው የስብከተ  ወንጌል ሐላፊ   መጋቤ ሐዲስ ዘለዓለም  የተነሱትን ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ተመርኩዘው ገንቢ ሓሳቦችን አስተላልፈዋል፡፡ ንግግራቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት  ልናደርግ ይገባል በሚለው ጀምረው የስብከት ወንጌል ክፍል በጀት እንዲመደብለት ሰባኪያነ ወንጌሉ እቅድ አቅደው ለሰበካ ጉባኤ እንዲያቀርቡ መልክእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡   ክፍለ ከተማውም ሰበካ ጉባኤው እንዲፈጽመው ጥብቅ ክትትል ያደርጋል ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡  እንዲሁም የክፍለ ከተማው ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት  ግርማ  ስብከተወንጌል  የቤተክርስያኒቷ ሕልውና ነው በሚል ጀምረው እጅግ ጠቃሚና አስደሳች የሆነ ንግግር አድርገዋል፡፡ ስብከተ ወንጌል ከሰበካ ጉባኤ በጀት  ጠያቂ መሆን አልነበረበትም፣ የራሱ የሆነ በጀት ከቤተክርስቲያኒቱ ታስቦ  ሊመደብለት ይገባል፣ ስብከተ ወንጌልን የበጀት ባለቤት ካደረግን ሁሉም ሰባኪያነ ወንጌል እንስብክ እናሰብክ ይላሉ፣ የነፍስ ጉዳይ ስለሆነ ልንቀልድ አያስፈልግም፡ ከአዲሱ የሀገረስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስና ከአዲሱ ሥራ አስኪያጅ ጋር በመሆን አብረን አመርቂ የሆነ ሥራ መሥራት

ይገባናል፣ ስብከታችን ከካህናትና ከቢሮ ሠራተኞች መጀመር አለብን፣ በሰበካ ጉባኤ ምርጫም ሰባኪያነ ወንጌል ሊካተቱ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በሌላ በኩልም ሁለተኛው የዕለቱ አጀንዳ የስብከተ ወንጌል ኮሚቴ የተፈለገውን ያህል ሥራ ለምን  አልሠራም የሚለው ተነስቷል፡፡ ይህንንም አጀንዳ አስመልክቶ ከታዳሚዎቹ ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተሰጥተዋል፡፡ ኮሚቴው ከእኛ ውጭ አትሥሩ፣ጉባኤ ሲዘጋጅ የኮሚቴው አለመገኘት፣ ሰበካ ጉባኤው በስብከተ ወንጌል ኮሚቴው ላይ ጫና ማድረግ፣ በሰበካ ጉባኤው ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል ኮሚቴ እንደገቢ ማሰባሰቢያ መቆጠር፣ ስብከተ  ወንጌል የሰበሰበውን ገቢ በጽ/ቤቱ አካውንት  አስገቡ በማለት ጫና ማሳደር፣ የአመራር ችግር መኖር፣ ለአንዳንድ አጥቢያዎች  መመሪያና ደንብ የተሰጠ ሲሆን ለሌሎች ደግሞ አለመሰጠት እንደ ችግር ተነስቷል፡፡ ለችግሮቹም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተሰጥተዋል፡፡ የስብከተ ወንጌል በእያንዳንዱ አጥቢያ በደንብ ቢሠራበት፣ ለሁሉም አጥቢያ የስብከተ ወንጌል ኮሚቴ  መመሪያና ደንብ ቢሰጥ፣ የቤተክርስቲያን ሕልውና ለሆነው ለወንጌል አገልግሎት ትልቅ ትኩረት ቢሰጥበት የሚሉት ሐሳቦች ተሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ጉባኤው 7 አባላት ያሉት ኮሚቴ መርጦ የዕለቱን ስብሰባ በጸሎት ዘግቷል፡፡በቤተክርስቲያናችን እንዲህ አይነት የውውይት መድረክ በጣም ጠቃሚዎች ስለሆኑ ሁሌም ቢለመዱና በሌሎች ክፍላተ ከተማም በተከታታይ መልኩ ቢሠራባቸው መልካም ነው፡፡በተለይም ስብሰባ አድርገናል የውውይት መድረክ አዘጋጅተናል ከማለት በዘለለ በተሰብሳቢዎቹ የሚሰነዘሩትን የመፍትሔ አቅጣጫዎች ትኩረት ተሰጥቶባቸው ወደ ተግባር ቢሸጋገሩና ለውጥ ለማምጣት በደንብ ቢሠራባቸው መልካም ነው እንላለን፡፡

ከሚዲያ ክፍል

አዲሶቹ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሥራ ሐላፊዎች ከገዳማቱና አድባራቱ ሐላፊዎች ጋር ትውውቅ አደረጉ

Photo by Kidu

በአዲስ መልኩ የተመደቡት የጽሕፈት ቤቱ የሥራ ሐላፊዎች ከአንድ ሳምንት በፊት በሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ሐላፊዎችና የሥራ ባልደረቦች እንዲሁም በክፍላተ ከተሞች ሠራተኞች አቀባበል የተደረገላቸው ቢሆንም በቀን 11/2011 ዓ/ም ደግሞ ቅዱስ ፓትርያሪኩና ሌሎችም በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ከአድባራቱና ገዳማቱ አስተዳደሪዎችና ጸሐፊዎች ጋር በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ የትውውቅ መርሐ ግብር ተደርጓል፡፡

በዚሁ የትውውቅ መርሐ ግብር ላይ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የቅዱስ ፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ መልከጼዴቅ ²ቤተ-ክርስቲያን መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶችን ለአገልጋዮቿና ሠራተኞቿ በሚገባ መልኩ የማሟላትና የማስተካከል ግዴታ አለባት ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እንደሚታየው ለአምሮትና ለቅንጦት በሚል የስሜት መነሣሣት የቤተክርስቲያንን ሀብትና ንብረት መዝረፍ ግን ከነውርነቱም አልፎ ወንጀል ነው ብለዋል²፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሥራ አፈጻጸም ክንውናችን መዋቅሩን የጠበቀና ማዕከላዊነቱን ያገናዘበ አሠራር መሆን ይኖርበታል ይህም ተግባራዊ ከሆነ ሁሉም ሠራተኛ ሐላፊነቱን ስለሚገነዘብ አንዱ የሌላውን የሥራ ድርሻ ሊቀማ አይችልም ሲሉ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ቆሞስ መ/ር አባ ሞገስ ኃ/ማርያም ደግሞ ²የተቀበልነው ሐላፊነትና የተሰጠን አደራ ከባድ ቢሆንም የተጠራንበት ዓላማ ግን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሆነ ከእናንተ ከአባቶቻችንና ወንድሞቻችን ጋር በመተባበርና እጅ ለእጅ በመያያዝ እየተናበብን ራሳችንን ከዘረኝነትና ጎሰኝነት በማጽዳት የተቻለንን ሁሉ እንሠራለን በማለት ተስፋ አዘል ንግግራቸውን አስደምጠዋል²፡፡

Photo by Kidu

በመጨረሻም ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በልዩ ሀገረ ስብከታቸው ውስጥ እየተከሰተ ስላለው መሠረታዊ ችግርና ስለ አዲሶቹ ሹማምንት አስመልክተው ²ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሁለቱም ሹማምንት ያስተላለፉት መልእክት ተስፋ አዘልና ብስለት የሚታይባቸው በመሆኑ እንድትቀበሉልኝ እፈልጋለሁ ፤የሀገረ ስብከታችን ችግር በአንድ ቀን ተነጋግረነው የሚፈታ ጊዜያዊ ችግር ሳይሆን ተቀምጦ ሰፊ ውይይትን የሚጠይቅ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮት አለበት፤ስለሆነም በየጊዜው እየተገናኘን መምከርና መወያየት ይኖርብናል፡፡ የተስፋ ጉዟችንንና የቤተ-ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ልማት የሚያደናቅፉ በርካታ ናቸው እነዚህ መደናቀፎች ደግሞ ለቤተ-ክርስቲያናችን ከፍተኛ ጠንቆች ስለሆኑ በጸሎትና በጾም ልንዋጋቸው ያስፈልጋል፡፡

በቤተ-ክርስቲያናችን ሥርዓተ ሕግ መሠረት የዓቢይ ጾምን ወይም ጾመ-ኢየሱስን ለመቀበል በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ በዚሁ ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን ጾም ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት በማስገዛት ስለ ቤተክርስያናችን ብሎም ስለ ሀገራችን  አብዝተን ልንጸልይና ልንማጸን ይገባናል፤ ያለንበት የእኛ ዘመን ተኝቶ የሚያሳድር ሳይሆን  መጾምና መጸለይን እንዲሁም መተባበርን አብዝቶ የሚጠይቅ ክፉ ዘመን ነው፤በርከታ ምዕመናን እየተዘረፉብን ነው ያለነው ይህንን ዝርፊያ አሜን ብለን በጸጋ ልንቀበለው ፈጽሞ አይገባም በሁሉም ነገር ጠንክረንና ነቅተን መንጋችንን ልንጠብቅ ይገባናል በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡     

   በመሆኑም የሀገረ ስብከታችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቀነስ ብሎም ዘለቄታዊ መፍትሔ ለመስጠት  ቅዱስ ፓትርየሪኩ ያቀረቡት የእንወያይ ሐሳብ በእጅጉ መልካም ከመሆኑም በላይ በሠራተኞችና የሥራ ሐላፊዎች  መካከል ያለውን መራራቅ የሚያቀራርብ ወደ አንድነትም የሚያመጣ፤ለዘረኝነትና ጎጠኝነት እንዲሁም ለሙስናና ሙሰኝነት መስፋፈት ምክንያት የሚሆኑ አንዳንድ ክፍተቶችና አሠራሮች ላይ ግልጽ ውይይት በማድረግ መፍታት የሚቻልበት መሆኑን ከሌሎች መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት መማርና ተሞክሮ መካፈል ይቻላል፡፡

ከዚህ በመነሣት የጽ/ቤቱ የሥራ ሐላፊዎች  ከላይ እስከ ታች  ያለውን መዋቅራዊ አሠራር በመፈተሽ አፋጣኝ መልስ ለሚያስፈልጋቸውም ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ለመስጠት ተቀራርቦ መሥራቱና መወያየቱ አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ተረድተው በሥራ ላይ ቢያውሉት መልካም ነው እንላለን፡፡

ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሐላፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

የአ/አ/ ሀ/ ስ/የፓ/ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ መልከጼዴቅ እና ዋና ሥራ አስኪያጅነት መ/ር አባ ሞገስ ኃይለ ማርያም

ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመደቡት ብጹእ አቡነ መልከጼዴቅ እና በዋና ሥራ አስኪያጅነት የተመደቡት መ/ር አባ ሞገስ ኃይለ ማርያም በሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ሐላፊዎችና የሥራ ባልደረቦች እንዲሁም የክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ዛሬ የካቲት 2011ዓ/ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ምናሴ ወልደሐና የተመራው የአቀባበል መርሐ ግብር ከሌሎች ጊዜያት የአቀባበል ሥርዓት መረጋጋት  የታየበት ሲሆን በብጹእነታቸው ጸሎት ተጀምሮ የዋና ሥራ አስኪያጁን መልእክት ያስከተለ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አሰኪያጅ  መምህር አባ ሞገስ ኀይለ ማርያምም ሕግ ይወጽእ እምጽዮን በሚል  የመነሻ ሐሳብ ነገሥታት ሕዝባቸውን የሚመሩበትን ሕግ አውጥታ፤ የሰጠች ቤተክርስቲያናችን ለራሷ የሚሆንና ራሷን የምታስተዳድርበት ሕግም አላት፤ ለመሪዎች ስኬታማነት የተመሪዎች ሚና ቁልፍ ጉዳይ ነው ይህም ከተተገበረ ተመሪዎች ወደ መሪነት የማያድጉበት ምንም ምክንያት የለም፤ የየመምሪያውና የዋና ክፍል ሐላፊዎች ለተመደባችሁበት ቦታና ለተቀበላችሁት ሐላፊነት ሥራ አስኪያጆች ናችሁ  ስለዚህ ሕግን በማክበር ከዘር፥ ከአካባቢና ከቋንቋ አድሎኝነት በጸዳ መልኩ አብረን በጋራ እንሠራለን፤ ጎጃም፥ ጎንደር፥ ትግራይ.፤ ጅማ፤ አሩሲ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ቦታ እንጅ እንደዚህ ዓይነት ሕዝብ የለንም ይህም የልዩነታችን ምክንያት ሊሆን አይገባም በማለት  የሀገርና የቤተክርስቲያን ወቅታዊ ተግዳሮት ስለሆነው ዘረኝነትና ጎጠኝነት ጠንካራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ብጹእነታቸው እንግዲህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ (ዮሐ 6፤28) በጥብርያዶስ ባህር አጠገብ በተፈጸመው ታምራዊ ክስተት የእጁን በረከት የለመዱ ጥቅመኞች ሁልጊዜ ዳቦ ብቻ ፍለጋ ስለተከተሉት “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለበላችሁና ስለጠገባችሁ ነው እንጅ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም” ለሚጠፋ መብል አትሥሩ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፡፡ ብሎ ሲወቅሳቸው እንግዲህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ (ዮሐ 6፤28) የሚል ወሳኝ ጥያቄ ማንሳታቸውን አስታውሰው የአገልጋይ የመጨረሻው ተስፋ እንጀራ ወይም መብል ሳይሆን የሕይወት አክሊል ነው፡ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ፈቃድ የማይቃወም አካሄድና ሥራ ሊኖረን ያስፈልጋል፤ ዛሬም በእኛ ዘመን ጥያቄው ቀጥሎ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ ልንል ደግሞም ለተጠራንበትና ለተመረጥንበት መሠረታዊ ጥሪ ልንኖር ይገባል ለዚህ ደግሞ ትህትና ፤እውቀት፤ የዋህነትና መንፈሳዊ ሕይወት ያስፈልጋል፡፡

የጥሪውን መልስ ለመስጠት ደግሞ የቃላት ቅመማ ወይም ብልጣብልጥነትና  የቲዎሪ ብዛትም አያስፈልግም ይልቁንም እነዚህ ዘመን ያለፈበት አሮጌ ሕይወት መሆኑን ተረድተን በዕለት ከዕለት ተግባራችን ጥሪውን እንመልስ ባለን ቆይታ በግልፅ እንነጋገር እናውራ እንመካከር የፈሪሳውያንን ጠባያትም እናስወግድ፤ የውሸት መወድስና ቅኔም አናብዛ ፤የእኛ ተልእኮ ዓለምን ማግባበት ወደ አንድነትም ማምጣት እንጅ የትርምስ የመሸነጋገልና የመለያየት መሆን የለበትም፤ ዛሬ በቤተ-ክርስቲያናችን እየታዩ ያሉት ሰላማዊ ሰልፎችና የተቃውሞ መፈክሮች በአገልጋዩ ጥሪውን አለማክበርና በአስተዳደራዊ ክፍተቶች ቢሆንም ለቤተክርስቲያናችን ግን ጉዳት እንጅ ጥቅም አይደለም ስለሆነም የሥራ ክፍፍል ማድረግና ነጥሮ የወጣውን የቃለ ዓዋዲውን ሕግ ማስፈጸም ያስፈልጋል በማለት ንግግራቸውንና አባታዊ መልእክታቸው አጠቃልለዋል፡፡

በመጨረሻም ለእድምተኞች በተሰጠው የመናገር ዕድል የሀገረ ስብከቱ ትምህርትና ሥልጠና ዋና ክፍል ሐላፊ የሆኑት መጋቤ ሐዲስ ኃይለእግዚእ በተሰጠህ ሐላፊነት ላይ ብዙ ጊዜ አትቆይምና ቶሎ ቶሎ ዝረፍ የምንባልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፤ ከአንድ ግለሰብ ጉቦ ተቀብሎ መብላት የግለሰቡን ደም እንደመጠጣት ይቆጠራል እንደዚህ ሊሆን አይገባም ከመስረቅና ጉቦ ከመቀበል ደመወዛችን እንዲጨመር መጠየቅ ነው ሲሉ፤ የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤ/ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት መልአከ ጽዮን ቆሞስ አባ ኅሩይ ደግሞ በርካታ አቀባበሎችን አድርገናል ነገር ግን ልብን በሚሰብር የእግዚአብሔር ቃል መልእክት የተላለፈበት ልዩ ቀን ግን ዛሬ ነው፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት አለ እነዚህ እየተከላከላችሁ የምትሰሩ ከሆነ ከአጠገባችሁ አለን በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌሎች ታዳሚዎችንም ባናገርንበት ወቅት በዕለቱ የተላለፉት አባታዊ መልእክትና መመሪያዎች የወደፊት የሀገረ ስብከቱን ትንሣኤ በተስፋ የሚያፈጥኑ፤በሰራተኛው ላይ እየደረሰ ያለውን የሥነ ልቦና ጉዳት የሚፈቱ ቢመስሉም ከሰኞ እስከ ዓርብ ያለውን የሥራ ሰዓትና ሰፊውን ጊዜ ለባለጉዳዮች ከመስጠት ይልቅ የክ/ከተማና የሀገረ ስብከቱን ሠራተኞች ወደ ማወያየቱ ካልመጣና የየዋና ክፍሎቹን ሥራዎች በሚመለከታቸውና የትምህርት ዝግጅት ባላቸው ወጣት የሰው ኃይል ካልተደራጀ አሁንም ቢሆን የለውጡ ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሐላፊዎች እነዚህንና ሌሎችም መሰል የሰሉ ሐሳቦችን ለማግኘትና ችግሩን ለማቃለል ተከታታይ የሆኑ ውይይቶችን ከሠራተኞች ጋር ማድረግና የሥራ ክፍፍል ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው እንላለን፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል መልካም የሥራ ዘመን ይሆንላችሁ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የሥራ ሐላፊዎች ተመደቡለት


ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ: የጉራጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ጳጳስ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክያን መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤ/ክህነት መዋቅራዊ አስተዳደር ሥር ከሚገኙት አህጉረ ስብከቶች መካከል አንዱና አንጋፋው እንዲሁም የቅዱስ ፓትርያሪኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የሆነው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካሉበት ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተነሣ ብጥብጥና ትርምስ የማያጣው ተቋም እየሆነ ከመምጣቱም በላይ በርካታ የሥራ ሐላፊዎችን ያፈራረቀ ነው፡፡

በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዘመነ ፕትርክና ብቻ አምስት ሥራ አስኪያጆችን አፈራርቆ ስድስተኛውን ሥራ አሥኪያጅ እየተቀበለ ያለው ይኸው ተቋም የቀድሞዎቹን የሥራ ሐላፊዎች ካነሣ በኋላ በምክትል ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ጥበባት ምናሴ ወልደሐና ለሦስት ሳምታት ያክል ሲመራ ቆይቷል፡፡

ትናንት ጥር 24/2011ዓ/ም ከስአት በኋላ በተደረገው የቋሚ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በሐምሌ ወር 2009 ዓ/ም ከተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት መካከል አንዱ የሆኑትና የጉራጌ ሀገረ ስብከትን እያስተዳደሩ ያሉትን ብጹእ አቡነ መልከጼዴቅን የቅዱስ ፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አድርጎ ሲመድብ በምዕራብ ሽዋ ሀገረ ስብከት ሥር የምትገኘው ታሪካዊት የመናገሻ ቅድስት ማርያም ገዳም አበምኔት መ/ር አባ ሞገስ ኃለማርያምን ደግሞ ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ እስከ ሚቀጥለው የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ላሉት ጥቂት ወራት ያስተዳድሩ ዘንድ በጊዜያዊነት ሾሟል፡፡

የአሁኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ምደባ ከአሁን በፊት ከነበሩት የብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና የቋሚ ሲኖዶስ የሹመት አሰጣጥ ለየት የሚያደርገው የመጀመሪያው ነገር ሹመቱ ለጥቂት ወራት የተሰጠ ጊዜያዊ ሹመት መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በስድስተኛው ፓትርያሪክ ማለትም በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዘመነ ፕትርክና  ከተሾሙት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ዝርዝር ውስጥ ብቸኛው መነኮስ መሆናቸው ነው፡፡

መምህር አባ ሞገስ ኀይለ ማርያም አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ

በጊዜያዊ መልኩ ወደ ሀገረ ስብከታችን የተመደቡት የሥራ ሐላፊዎች በየጊዜው በሁከትና ትርምስ እንዲሁም የተማረውን ወጣት የሰው ኃይል ጡረታ በማውጣት ለሚታወቀው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሻለ የመፍትሔ አቅጣጫና አማራጭ ሐሳብ በማቅረብ ወጣቱን የሰው ኃይል በማሳተፍ እንዲሁም የሚሰራበትን የአሠራር system በመዘርጋትና ዘመኑን በመዋጀት የለውጡን በር ይከፍቱት ዘንድ ተስፋ እያደረግን ሰፊ ትንታኔና አጠቃላይ ዘገባው ደግሞ በሚቀጥለው ክፍለ ጊዜ እንደምንመለስበት እናረጋግጣለን፡፡

ለብጹእ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅና ለዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አባ ሞገስ ኃይለማርያም መልካም የሥራ ዘመን ይሆንላችሁ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡

በሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል