ለመሆኑ ቴክኖሎጂ ለቤተክርስቲያን ሐዋሪያዊና ማኀበራዊ አገልግሎት ለምን ለምን ይጠቅማል?

ቀደምት አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በወቅቱ በተሰጣቸው ጥበብ በየአገሩ ቋንቋ እየተገለፀላቸው ዓለምን እየዞሩ እግዚአብሔር በሰጣቸው ፀጋ የዓለምን ሕዝብ ክርስትናን አስተምረዋል፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ጥበብን ሁሉ የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ታዲያ እግዚአብሔር እውቀትንና ጥበብን የሚሰጥ መሆኑን ካመንን እግዚአብሔር እውቀቱንና ጥበቡን ሰጥቷቸው የተሠራውን ቴክኖሎጂ ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት ብንጠቀምበት ጥቅሙ/ ጉዳቱ ያመዝናል? በእኛ አመለካከት ቴክኖሎጂዉን በመጠቀም የዓለምን ሕዝብ ማስተማር ይቻለል፣ የቤተክርስቲያኒቱንም ታሪካዊ ቦታዎች ማስተዋወቅ ይቻላል፡፡ ወቅታዊ የሆኑ የቤተክርስቲያን ጉዳዮችንም ለዓለም ሕዝብ በተለያየ ቋንቋ ማሠራጨት ይቻላል፡፡

ለምሳሌ፡-    

  1. በቪዲዮ ኮንፈረንስ
  2. በቻቲንግ
  3. በቴሌ ኮንፈረስ
  4. በኢሜል . . .

በጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በቪዲዮና በመሳሰሉት የቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮም ይሁን ማሕበራዊ ጉዳዮችን በቀላሉ ማዳረስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በቴክኖሎጂው የማይከናወኑና የግድ በአካል በቤተክርስቲያን በመገኘት የሚከናወኑ ሥርዓቶች አሉ፡፡እነሱም፡-ሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ማለትም ሚስጥረ ጥምቀት፣ ሜሮን፣ ቁርባን፣ ክህነት፣ ንስሐ፣ ተክሊል እና ቀንዲል ሲሆኑ ከእነዚህም በተጨማሪ አጠቃላይ ስብሐተ ነግህ፤ የሰርክ ጸሎት፤ ሰዓታት፤ማኀሌት፤ፍትሐት እና የመሳሰሉት በዚህ ቴክኖሎጂ አይከናወኑም ነገር ግን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ብዙ ማህበራዊ ጉዳዮችን ማከናወን ይቻላል፡፡

በመሆኑም ሁሉም ምእመናን የቤተክርስቲያኒቱ ልሳናት ወይም ሚዲያዎች የሆኑትን ለይተው ማወቅና መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስሙ የቤተክርስቲያን የሆነ ነገር ግን በድረገጹ  የሚለቀቀው ጽሑፍ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነና ቤተክርስቲያኒቱ የማታውቃቸው ልዩ ልዩ የግል ድርጅቶች በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ ብዙ ችግር እየፈጠሩ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ምእመናንንም ሆኑ ልዩ ልዩ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች በቤተክርስቲያኒቱ ፈቃድና እውቅና ተሰጥቶአቸው በሚመለከታቸው አካላት ታምኖባቸው የተለቀቁ ሳይቶችን ብቻ ብትጐበኙ መልካም ነው እንላለን፡፡