ለአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ ከአሁን በፊት በሚያስተዳድሩበት ደብር ደማቅ የሽኝት መርሐ ግብር ተደረገላቸው

ሰኔ 7 ቀን 2012 የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ፤ የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥት ግርማ እና ሠራተኞች፤ የደብሩ ማኅበረ ካህናትና የደብሩ ሰ/ት/ቤት ወጣቶች እንዲሁም በርካታ የአካባቢው ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት በጀሞ ምሥራቀ ጸሐይ ቅ/ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በቃለ እግዚአብሔር የታጀበ ደማቅ የአሸኛኘት መርሐ ግብር ተደርጓል።


የሽኝት መርሐ ግብሩ የተዘጋጀበት ዋንኛ ዓላማ በአስተዳዳሪነት ቦታው ላይ ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ በማኅበረ ካህናቱና ማኅበረ ምእመናኑ መካከል ያለውን አንድነት በማጠናከር፤ ስብከት ወንጌልን በማስፋፋት፤ለደብሩ ማኅበረ ካህናትና ለሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በየጊዜው የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግና የደብሩን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከፍ በማድረግ እንዲሁም የደብሩን ይዞታ በማስከበር ላይ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለመዘከርና አባታዊ ፍቃራቸውን ለማሰብ መሆኑን በቀረበው ሪፖርት ላይ ተገልጾ የከበረ ስጦታም ተበርክቶላቸዋል።

በአሁኑ ወቅት ደብሩን በማስተዳደር ላይ የሚገኙት መልአከ ፀሐይ ቀሲስ ሰናይ ባያብል ባደረጉት ንግግር እኛ ይህንን መስቀል በስጦታ መልክ ያበረከትንላቸው አሁን በሥራ አስኪያጅነት የተሾሙበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአንድ አቅጣጫ ሲጠግኑት በሌላ አቅጣጫ የሚናድ ከመሆኑም በላይ ብዙ ውጣ ውረድ እና ድካምን የሚጠይቅ ቦታ ስለሆነ መከራ አለብዎት ግን ይበርቱልን ለማለት መሆኑን ገልጸው ምንም እንኳን ከዚህ ቦታ በዕድገት ቢቀየሩም ይህንን ደብር በተለየ መልኩ አይተው አባታዊ ምክረዎትና መመሪያዎት እንዳይለየን ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ አጭር ቃለ ወንጌል ካስተማሩ በኋላ ዛሬ ያደረጋችሁት መልካም ተግባር ምንም እንዳልናገር አቅም አሳጥቶኛል፤ከእናንተ ጋር በቆየሁባቸው ጊዜያት በርካታ በጎ ነገሮችን ተምሬለሁ ነገር ግን መሥራት የምፈልገውን እና ማድረግ ያለብኝን ያክል ግን ሠርቻለሁ ብዬ አላስብም፤እናንተ ግን ራሳችሁ የሠራችሁትን ሁሉ ለእኔ ስለሰጣችሁኝ አመሠግናለሁ፤ ይህንን ታላቅ ደብር ባስተዳደርኩበት ወቅት የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት እና ደብሩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ባደረግኩት ጥረት ያለምንም ቅሬታ አብራችሁኝ የተሰለፋችሁ ማኅበረ ካህናት፤ የአስተዳደር ሠራተኞች፤ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች፤ የልማት ኮሚቴዎች እና እጅግ የማከብራችሁና በገንዘባችሁም ሆነ በዕውቀታችሁ እግዚአብሔርን የምታገለግሉት የአካባቢው ምእመናን ሁሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፤ምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ገብርኤልና ቅ/አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ለእኔ ልዩ የሆነ የሱባኤና የጸሎት ቦታ ነው አብሬያችሁ አለሁ እናንተም የጀመራችኋቸውን የልማት ሥራዎች በሚገባ አጠናክሩት፤በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈው መርሐ ግበሩ በጸሎት ተጠናቋል፡፡

ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በዚሁ ታላቅ ደብር በአስተዳዳሪነት መቆየታቸውን ከአሁን በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡


መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ- በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *