መልካም ባልንጀራ

ምስጢር የሚያወያዩትን አብሮ የሚሠሩትንና ጧት ማታ የሚገናኙትን እንዲሁም አብሮ አደግየሆነውን ሰው ባልንጀራዬ ነው ብሎ መናገር የተለመደ ነው፡፡ ዛሬ ለኔ ነገ ላንተ እየተባባሉ አብረው ከሚውሉት፣ ከሚያመሹት ጓደኞቻቸው ሌላ ባልንጀራ ያለ የማይመስላቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡ በመሠረቱ አብሮ መብላትና መጠጣት ወይም በአንድ ላይ ተምሮ ማደግና አብሮ መኖር ይልቁንም ትንሽ ትልቁን ክፉና ደጉን ምስጢር መካፈል ባልንጀራ ሊያሰኝ ቢችልም ይህ ብቻ ራሱ የፍቅር መመዘኛና መለኪያ ይሆናል ማለት ዘበት ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ የተመሠረተው ፍቅር አብዛኛውን ጊዜ በጥቅም ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን ሰብአዊ ርኅራኄና ከልብ የመነጨ መንፈሳዊ ስሜት የተዋሐደው ሊሆን አይችልምና ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፤ በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር፣ የባልንጀራህን ሚስት ቤትና ንብረት በአጠቃላይ የባልጀራህን ገንዘብ ሁሉ ማንኛውንም አትመኝ” የሚለውን ሕግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡላቸውና በባልንጀራቸው ላይ ክፉ ሥራ እንዳይሠሩ ትምህርት ሲሰጧቸው ባልንጀራዬን እንዴት እክዳለሁ? እንዴትስ ተንኮል እፈጽመበታለሁ? በማለት ራሳቸውን ለባልንጀራቸው ታማኝ በማድረግ ሊናገሩና ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን የተፈጥሮ ጓደኛቸው የሆነውን ሰብአዊ ፍጡር ሲያሳዝኑትና ሲያስቀይሙት ይታያሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ክፉ ተግባር በሰዎች ላይ መፈጸም “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” የሚለውን መጣስ ነውና ይህ ኃጢአት ነው ሲሏቸው ደግሞ ባልንጀራዬ ማን ነው? የማላውቀው ሰውስ እንዴት ባልንጀራዬ ይሆናል በማለት ድርቅ ብለው ይከራከራሉ፤ የሚበላና የሚጠጣ የጽዋ ጓደኛ ከዚህም ሌላ በሀብትና በእውቀት ተመጣጣኝ ሆኖ ውለታ የሚውልና ብድር የሚመልስ ወይም በሥጋ ተዛምዶ የሚቀርብና የሀገር የወንዝ ልጅ የሆነ አፈር ፈጭቶ ውኃ ተጎንጭቶ አብሮ ያደገ ወይም በአንድ ትምህርት ቤት አብሮ የተማረ በሥራና በጉርብትና ምክንያት ወቅታዊ ፍቅር የመሠረተና ምስጢር የተጫወተ … ወዘተ ብቻ ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ግን “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” ሲል የተናገረው ማንኛውም ሰው በተፈጥሮ የሚመሳሰለው ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ባልንጀራው መሆኑን አውቆ አንዱ የሌላውን መብት በመጠበቅ እርስ በርሱ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ በሰላምና በደስታ እንዲኖር ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከሰዎች መካከል እኔን አይመለከተኝም ሳይል አንዱ ሌላውን እንዲረዳው ነው፡፡ ይህም አባባል ባልንጀራ በወገን፣ በጾታ፣ በጎሳ፣ በዘርና በመሳሰለው ጠባብ አስተሳሰብ ሳይወሰን እያንዳንዱ ሰው ለሌላው ሰው ወገኑና ባልንጀራው እንዲሁም ከአንድ ፈጣሪና ከአንድ አባት የተገኘ የተፈጥሮ ወንድሙ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ላይ እንደተጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተማር ላይ ሳለ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው አስቦ፡- መምህር ሆይ የዘለዓለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? በማለት በጠየቀው ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? አለው፡፡ ሕግ አዋቂውም መልሶ፡- ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም ኃይልህ በፍጹም ሀሳብህ ውደድ ባልንጀራህንም እንደራስህ ውደድ ሲል መለሰ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም እውነት መልሰሀል ይህንን ብታደርግ በሕይወት ትኖራለህ ሲል ነገረው፡፡ ነገር ግን ሕግ አዋቂው ራሱን ከፍ አድርጎ በመመልከት ባልንጀራዬ ማን ነው? ሲል እንደገና ጠይቋል በዚህ ጊዜ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደጉና ሳምራዊ ታሪክ ከተረከ በኋላ “አንተም እንደዚሁ አድርግ” በማለት ለሰዎች ሁሉ መልካም መሥራትና እርስ በእርስ መዋደድ እንደሚገባ አስረድቶታል፡፡

እንግዲህ ባልንጀራ የሚባለው ባገኙ ጊዜ ብቻ አብሮ በልቶ ጠጥቶ በችግር ጊዜ ወደኋላ የሚሸሽ ሰው ሳይሆን “ባልንጀራህን እንደራስህ ወደድ” በሚለው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት የችግረኞችንና ጉዳተኞችን ችግር እንደራሱ ችግር በመቁጠር ውለታና ብድር ሳይሻ ሁሉንም በእኩልነት ተመልክቶ በጤናም ሆነ በሀብት ወይም በእርጅና ምክንያት የተቸገሩትን ሁሉ በአቅሙ መጠን የሚቻለውን የሚረዳ ነው፡፡ ከዚህም ሳምራዊ ሰው የምንማረው ይህንኑ ነው፡፡

እኛም እንደደጉ ሳምራዊ ሰው በዘመናችን ሁሉ ለሰዎች መልካም አድርገን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *