መንፈሳዊ ትምህርት (ሥልጠና)

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በቅዳሜ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ /በመጀመሪያ እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ በኋላ በመጀመሪያው የሥነ ፍጥረት ቀን ቅዱሳን መላዕክትን ፈጥሮ ተሰወረባቸው መላዕክትም መኑ ፈጠርነ ወእምአይቴ መጻዕነ ማን ፈጠረን ከየትስ መጣን /ተገኘን / የሚለውን የምርምር ሀሳብ አንስተው ሲወያዩ አላዋቂ ዲያብሎስ ሁሉም ቅዱሳን መላዕክት በቦታ አቃማመጥ ከእርሱ በታች ሁነው ስለአያቸው እኔ ፈጠርኳችሁ አላቸው ቅዱሳን መላዕክትም በቦታ ከሆነ እኛ ከእኛ በታች የሆኑትን አልፈጠርንም በማለት የመመራመር ሥራቸውን ቀጥለው በአሉበት ሰዓት ሊቀ መላዕክት ቅ/ገብርኤል “ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክበ ለአምላክነ” ፈጣሪያችን አምላካችን እግዚአብሔርን እስከ ምናገኘው ድረስ ሁላችንም በተፈጠርንበት ሕልውና ፀንተን ልንኖር ይገባናል የሚለውን ትምህርት ለቅዱሳን መላዕክት በመንገሩ /በማስተማሩ/ የማረጋጊያ፣ የማጽናኛ ፣ ትምህርት ሰጥቷል ይህንን የማረጋጊያ ትምህርት በአግባቡና በጥልቀት ሰንመለከተው የመማር ማስተማር ሥራ የተጀመረበት ወቅት መሆኖን ቅዱሳን መጻሕፍትና ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን ያረጋግጡልናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዘር የሆነውን አዳምን በመልኩና በምሳሌው ከፈጠረ በኋላ ባለግዕዛን አእምሮ /ነጻ አእምሮ/ ሰጥቶ የማወቅ የመመራመር ጥበብንና እውቀትን ከመሰጠቱም ሌላ የሚበሉና የማይበሉ ዕጽዋትን ነግሮና አስተምሮ የማይበላው የተከላከለውን በልቶ ቢገኝ የሞት ሞት እደሚሞት አምላካችን በሰው ዘር ታሪክ የመፍጠርና የማስተማር ሥራውን በአዳም እንደ ጀመረ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

የአዳም ሦስተኛ ዙር የሆነውና እግዚአብሔርን በማገልገል የሚታወቀው ደገኛው ሰው ሄኖስ በሰማይ ላይ የተጻፈ ጽሁፍን አይቶና ተመልክቶ ዛሬ ለብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት መጻፍና በዓለም ለሚገኙ ልዩ መጻሕፍትና የምርምር ሥራዎች መከናወን በዚያን ጊዜ ለነቢዩ ሄኖስ በደፍደፈ ሰማይ ተገልጦ የታየው ጽሁፍ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ምንም እንኳን ያ ዘመን ትምህርቱም ሆነ ታሪኩ የሚነገረውና የሚተረክው ጽሁፍ የማይከናወንበት የሕገ ልቡና ዘመን ቢሆንም የአጻጻፍ ሁኔታ /ጽሁፍ/ የተገለጠበት ጊዜና ወቅት ነበርና የጽሁፍ ትምህርት የተጀመረበት እንደሆነ ሊቃውንት በምርምር ሥራቸው ዘግበውት ይገኛል፡፡

ሰዎች በምድር ላይ እግዚአብሔርን መበደል በጀመሩበት ወቅት ጻድቁንና ንጹህ ሕሊና ያለውን ኖኅን አስነስቶ የበደሉ ሰዎችን አስተማሪ ትምህርቱን አልቀበል በማለት በደላቸው እየበዛ በሄደ ቁትር ኖኅና ልጆቹ የሚድኑበትን የጥበብና የእምነት ትምህርት ኖኅ ተምሮና ተመራምሮ ከእግዚአብሔር ቁጣና መቅሰፍት ራሱንና ቤተሰቡን አዳነ ከጥፋት ውሃ በሰላም ኖህ በተማረው ትምህርት ለእግዚአብሄር መስዋዕት አቀረበ የእግዚአብሔርን አዳኝነት ለልጆቹና ለቤተሰቡ አስተማሪ ከእግዚአብሔርም በረከትን አገኘ፡፡

የእውነተኛው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ የሆነው አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ ተብሎ የተነገረለት አባት እናት የትውልድም ዘመን የሌለው ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍፃሜ የሌለው መልከ ጼዴቅ ከእግዚአብሔር የተማረውንና በተሰጠው የሥልጣነ ካህናት ማዕረግ አብርሃምን እንዳሰተማረው እንደባረከውና አብርሃም ከአገኘው ሀብት ሁሉ ከአሥር አንዱን /አስራቱን/ ለእግዚአብሔር መስጠት እንዳለበት የነገረውና የሐዲስ ኪዳን መስዋዕት ምሳሌውን አብርሃም ያወቀውና የተማረው ከመልከ ጼዲቅ እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍና መተርጎማን ሊቃውንት ይነግሩናል፡፡

አበ ብዙኃን ተብሎ የተነገረለት አብርሃምም የእግዚአብሔርን ህልውና /መኖር/ ተመራምሮ የአወቀ ከመልከ ጼዲቅና ከእግዚአብሔር በአገኘው ትምህርትና በረከት ለልጆቹና ለተከታዮቹ ነገረ አስተማረ፡፡ 

ከዚህ በላይ ያለው አጭር ታሪክ ስንመለከት ሕገ ኦሪት መጻፍ እስከ ጀመረበት ጊዜ ብዙ ቅዱሳን አበው ከእግዚአብሔር በአገኙት ጥበብና ዕውቀት ተምረውና ተመራምረው ከመዝ ይቤ እግዚአብሔር እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልኩ ከእርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ የአስተማሩበትና ዘመኑም ሕግ ያልተጻፈበት በሕገ ልቡና እግዚአብሔርን አውቀውና አዳኝነቱንም ተረድተው ያአስተማሩበት እንደሆነ የታሪክ ሂደት ያስረዳናል፡፡ ይህን ታሪክ ስንመለከት በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን ዘመን ለተነሱት ታላላቅ ቅዱሳን ነቢያት ሐዋርያት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የትምህርትና የምርምር ሥራዎቻቸው ዋና መነሻ ታሪክ እንዲሆን ተረድተናል /እንረዳለን/፡፡

የመንፈሳዊ ትምህርት አሰጣጥ

በሕገ ኦሪት

እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ የእምነት ሕግንና ሥርዓትን አስተምሮ ሰጠው ለልጆቹም ሆነ ለሕዝበ እስራኤል የሚያስተምርበትን የሕግ መጽሐፍ ጽፎ እንዲይዘውና እንዲያስተምር ታዘዘ በተለይም በዘዳግም ምዕራፍ 6፡4-9 ያለውን ኃይለ ቃል ስንመለከተው የመማር ማስተማር ሥራና ተግባር በቃልም በጽሁፍም የተጀመረበትና የተከናወነበት ጊዜ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ቃሉም “እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም  ዛሬ አንተን የማዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ፡፡ ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም ስትነሳም ተጫወተው፣ በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው በአይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው”፡፡ በማለት እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ እንዳሰተማረውና ሙሴም የተማረውን ትምህርትና የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለልጆቹና ለሕዝብ እስራኤል በትጋት ፣ በቅንነትና ፍጽም በሆነ ፍቅር አስተማረ 5ቱን የሙሴ መጽሐፍ ተብለው የሚነገርላቸውን ሕገ ኦሪትም ኦሪትም ለትውልድ በማስተላለፍ እስከ አሁን ድረስ እንማርበታለን ዘመኑም 3500 ዓመት እንደሆነው ከቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ እንረዳለን /ከሙሴ እስከ አሁን ያለው ዘመን)

እግዚአብሔር አምላክ ክህነትን ከምስፍና ጋር አጣምሮ የያዘውን ሙሴን የሚረዳና የክህነት አገልግሎትንም ከምስፍና ለመለየት ስለፈለገ ወንድሙን አሮንን ካህን አድርጎ እንዲሾመው ካህኑ አሮንንም የሙሴ አፈ ጉባኤ /አፈ መምህር/ ሁኖ የክህነት አገልግሎትን እርሱና ልጆቹ ተሾመ የማስተማር ሥራ ወይም ቀጥሎ አስተማሪ /ዘጸ 28፡1 ፣ 29፡1/ የአሮንን ፈለግ በመከተል ሌዋውያኑ የማስተማር ስራቸውን አስተምረዋል፡፡ የክህነት አገልግሎትንም ሰጥተዋል፡፡ ሌላው በዘመነ መሳፍንትና ዘመነ ንግስታት የተነሱት ካህናትና ነቢያት ስለእግዚአብሔር ሕልውና ሳያፍሩና ሳይፈሩ አስተምረዋል፡፡ ሕዝቡ በምክረ ካህን ፣ በፍቃደ ካህን እንዲጓዝ ምክርና ተግሳጽ ሰጥተዋል ከእነዚህም በዋናነት የሚጠቀሱት ኢያሱ፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል ዳንኤልና ሌሎችም ነቢያት የማስተማር ሥራቸውን በብቃትና በንቃት ተወጥተዋል ታላቁንና የመጨረሻውን የክብር አክሊል ከፈጣሪያቸው ተሸልመዋል፡፡

የመንፈሳዊ ትምህርት አሰጣጥ በአዲስ ኪዳን

በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል የነበረው መጥምቀ መለኮት ቅድስ ዮሐንስ “ነስሑ ወእመኑ እስመ ቀርብት ይእቲ መንግስተ ሰማት” መንግስት ሰማት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ያስተምር እንደነበረ የንስሐ ጥምቀትም ያጠምቅ እደነበረ ብዙ ተከታይ ተማሪዎችም እንደነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይነግረናል፡፡ /ማቲ 3፡2 ፣11፡2/

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው 12 ዓመት በሆነው ጊዜ በኢየሩሳሌም ከበነበሩ መምህራን መካከል ተገኝቶ እንደተማረና ለመምህራኑም ልዩ ልዩ ጥያቄ እንዳቀረበላቸው በመልስና ከቃሉ ንግግር ማማር የተነሳ የሰሙትና ይገረሙ እንደነበር ከቅዱስ ቃሉ መረዳት ይቻላል /ሉቃ 2፡46/ ከዚህም በተጨማሪ ጌታችን መድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይግባውና እንደ አምላክነቱ ሳይሆን እንደ ሰውነቱ ቀስ በቀስ በሚያድግበት ወቅት ዕድሜው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ትምህርት ቤት ገብቶ እንደተማረ መምህራኑ በሚያስተምሩት ጊዜ ልዩ ልዩ ጥያቄ ያቀርብ እደነበርና የተግባረ ዕድ ሥራንም መምህራኑን ይረዳቸው እንደነበር በተአምረ ኢየሱስ ተጠቅሶ /ተጽፎ/ ይገኛል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በመዋዕለ ሥጋዌው 30 ዓመት ሲሞላው ተጠምቆ ገዳመ ቆሮንጦስ ገብቶ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ የማስተማር ሥራውን ጀመረ ደቀ መዛሙርቱንም ከተለያዩ ተግባረ ሥራ ለወንጌል አገልግሎት መረጠ /ማሬ 4፡17/ 12ቱን ሐዋርያት ደቀ መዛሙርት መርጦና አስተምሮ ሙሉ ሥልጣንም ሰጥቶ በዓለም ዙሪያ ወንጌልን እንዲያስተምሩ ከተሟላ የእምነት ትጥቅ ጋር ተላኩ /ማቴ 10፡1-42/

በመቀጠልም በድንቁርና ዓለም ውስጥ ያለው የሰው ዘር ያውቅ ይረዳና ይማር ዘንድ ሌሎችን ሰባ መምህራንን መርጦ አሰልጥኖና ባለሙሉ ሥልጣን አድርጎ አልጫ የሆነውን ዓለም በትምህርት ጨው እንዲያጣፍጡ ሾማቸው /ሉቃስ 10፡1/ በአጠቃላይ በ3 ዓመት ከ3ወር ውስጥ ዓለምን ዞረው የሚስተምሩ ደቀ መዛሙርትን መርጦና ሹሞ ከመላኩም ሌላ የ5 ገበያ ከ5,000 ሕዝብ በላይ ይከተለው እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል ከዚህ ላይ መርዳትና መናገር የምንችለው የመማር ማስተማር ሥራ ቀደም ሲል የነበሩት መምህራን ነቢያት የጀመሩትና ያስተማሩ ቢሆንም የህግና የሥርዓት ጀማሪውና ፈጸሜው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመማርንና የማስተማርን ጥቅም የሰው ልጅ አውቆና ተረድቶ እንዲማር ራሱ ለሰው ልጆች አርአያ ምሳሌ ለመሆን የጥበብና የዕውቀት ምንጭና ፈጣሪ ቢሆንም እንደሰውነቱ ትምህርት ቤት ገብቶ ተምሮአል አስተምሮአል ባለሙሉ ሥልጣን አድርጎ ሐዋርያትን ሰባ ሁለቱን ደቀ መዘሙርት መርጦ የሰማይና የምድር ስልጣን ሰጥቶ ስለላካቸው ዓለምን በ4 ማዕዘን ዙረው አስተማሩ፡

የነቢያትንና የሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ብዙዎች መምህራን ሊቀውተ ቤተ ክርስቲያን የማስተማር ጠቀሜታን አውቀውና ተረድተው ዋጋቸው ከልዑል እግዚአብሔር ለመቀበል ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው አስተምረዋል መክረዋል ፡፡

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመንፈሳዊው የትምህርት አሰጣጥ እንዴት እንደነበር በአጭሩ ስንመለከተው በቀዳማዊው ምንሊክ ዘመን /በ900 ዓመተ ዓለም አካባቢ/ ጽላተ ሙሴና ሰባው ለቃውንት /የብሉይ ኪዳን መምህራን/ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ሀገራችን ኢትዮጵያን በፈጣሪ  የምታምንና ሕገ እግዚአብሔርን የምታስተምር እደነበረች ታሪክ ቢነግረንም የሕገ ኦሪት ትምህርት መስፋፋትና መጠናከር የጀመረው ከቀዳማዊ ምንሊክ ከታቦተ ሙሴ መግባትና በሊቀ ካህናቱ አዛርያስ መሪነት የሰባው ሊቃውንቱ  ወደ ሀገራች መምጣት ከእነርሱም ጋር የመጡት መጻህፍተ ብሉያት መገኘት ሲሆን የክርስቶስንና የሐዋርትን አስተምሮ ተከትሎ በ34 ዓ.ም ጥቅምት ወደ ሀገራችን በኢትዮጵያው ጀንደረባ አማካኝነት መግባት /የሐ.ሥራ 8፡26-40 / በመቀጠልም በ4ኛው ክፍለ ዘመን በአብርሃና አጽብሃ ዘመነ መንግስት በከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ አማካኝነት የሀዲስ ኪዳን እምነትና ሥርዓትን ተቀብላ ዲያቆናትን፤ቀሳውስትን፤ መምህራን፤ በማስተማርና ሥልጣነ ክህነትን በመስጠት ቤተ ክርስቲያን እንድትሰፉና እንድትስፋፋ ሆነች፡፡ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትም እንዲሠሩ ሆነ በመቀጠልም በ5ኛ ክፍለ ዘመን የ9ኑ ቅዱሳን ወደ ሀገራችን መግባትና ገዳማትን መመሥረትና ማስተማር የቤተ ክርስቲያን መጠናከሪያ የወንጌል ማስተማር ሥራ በመስፋፋት ላይ እደነበር ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ጠቅለል ለማድረግ የትምህርትና የሌሎችንም የሥራ ዘር ማዕከል የነበረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአሠራር መላላት፣ የተጠናከረ የአደረጃጀት ሥልትና ዘዴ ያለመኖር፣ የእኔነት ስሜትና ፈላጎት ያለመኖር ይሁን ወይም ባልታወቀ ምክንያት የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በልዩ መልክ ያበራላትና የተቀደሰ ተግባሯንና ዓላማዋን በልዩ የመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ታከናውንና ታስተምር የነበረችው ቤተ ክርስቲያን የመማር ማስተማሩ ሥራ ቀዝቅዞ ይታያልና በከፍተኛ ሁኔታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት አደረጃጀቱም ሆነ አሠራሩ የቤተ ክርስቲኒቱ አስተምህሮ እንዳለ ሆኖ ዘመኑ በሚፈቅደው መልኩ ለሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ሠራተኞች የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠትና ሠራተኞችን በማብቃት እንደ አባቶቻችን ለቤተ ክስቲያን ብዙ ሥራ መስራት ይቻላል ፡፡