ማኀበራዊ ጉዳይ

የኢትዮጵያ ቤት ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተዋጽኦ የሚመነጨው ከዐሥርቱ ሕግጋት እና ከስድሰተቱ ቃላተ ወንጌል ነው፡፡ ዐሠርቱ ቃላተ ኦሪት እና ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በመተባበር ማኅበራዊ ሕግጋትን ያስተምራሉ፡፡ ማኅበራዊ ሕጎች በአንድ የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ የእረስ በእርስ ትስስር እና መተሳስብን ፍቅርንና አብሮ በሰላም የሚኖርበት አንድነትን የሚያጠብቁ መሠረቶች ናቸው፡፡ በመልካም መሠረት ላይ የሚኖር የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ በጊዜ ሂደት የራሱ የሆነ ባህል ይፈጥራል፡፡ ባህል ደግሞ የማንነቱ መገለጫ ከሌላ የኅብረተሰብ ክፍል የሚለይበት ኦርቶዶክሳዊ ማንነቱ የሚታወቅበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከተሉትን ማኅበራዊ አሰተዋጽኦዎች አድርጋለች እያደረገችም ነው፡፡ 

ማኅበራዊ አስተዋጽ

፩∙ በበጎ አድራጎት አገልግሎት መሳተፍ

የበጎ አድራጎት መነሻው ቅድሳት መጻሕፍት ሲሆኑ በኅብረተሰብ መካከል መተሳሰብን እና ሰብአዊ ርህራሄን ከማጎልበት ባሻገር ለነፍስ ዋጋ የሚያሰጡ ትምህርቶችንም የያዙ ናቸው፡፡
ስለሆነም የመንፈስዊ አገልግሎት ዋጋ ከመስጠቱም ባሻገር በህብረተሰቡ ዘንድ የመተሳሰብና የሰብአዊ ርኅራኄ መንፈስ ለማዳበር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ የህንንም ለማድረግ ጠቃሚ የሆኑት ስልቶች ሕዝቡን ማስተማር፤ ማደራጀት፤ ማስተባበር እና ተቋማትን መክፈት ናቸው፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መነሻውም ሃይማኖት ነው፡፡

እግዚአብሔር ራሱ ያለምንም ከፍያ /በጸጋ/ ፍጥረትን ሁሉ መልካም መሆናቸውን እያረጋገጠ ከመፍጠር የዕለት ተዕለት ፈላጎታቸውን እሰከ መስጠት ድረስ መሠረት ሆአኖል፡፡ አምላካቸውን የተከተሉ ሰዎችም ከአምላካቸው ተምረው ይህንኑ የበጎ ፋቃድ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ አበ ብዙኀን አብርሃም ያለምንም ክፍያ መንገደኞችን ማብላቱንና ማጠጣቱ ዋና ማስረጃ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅድስ ውስጥ የተዘረዘሩ ብዙ አገልግሎቶች በበጎ ፈቃድ የተከናወኑ ናቸው፡፡ ሰው የተቸገረ ወገኑን እንዲሁም እንግዶችን እየተቀበለ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበት ያለውን ለሌለው መርዳትና ማገዝ ይጠበቅበታል፡፡ ደጉ ሳምራዊ ተጎድቶ፣ ቆስሎ ያየውን ሰው፤ ማንም ሳያስገድደው በፈቃዱ አንስቶ፤ ቁስሉን በዘይት ቀብቶ፤ ለሚረዱት ሌሎች ሰዎች ገንዘብ ሰጥቶ፤ ተመልሶ እንደሚረዳው ቃል ገብቶ መሄዱ የሚታወስ የቤተ ክርስቲያን ተግባር ነው፡፡ አሁንም በቤተ ክርስቲያን ካህናት፤ ዲያቆናት፤ ምእመናን ብዙ ነገሮችን በበጎ ፈቃድ የሠራሉ፡፡
የሕፃናት ማሳደጊያ እና የአረጋውያን መጦሪያ ተቋማት መከፈት

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲየን ድሆችን የመርዳት የቆየ ባህል አላት፡፡ ምጽዋት ከመሥዋዕት ይበልጣል እንዲል፡፡ /ማቴ ፱፥፲፩፤ሆሴ ፮፥፮፤ አረጋዊ መንፈሳዊ/፡፡ ብራብ አበልችሁኝ፤ ብጠማ አጠጣችሁኝ፤ ብታረዝ አለበሳችሁኝ፤ የሚለው የምጽዋት ዋጋ በቅዱስ መጽሐፍ፣ በብዙ ገድላትና ድርሳናት ጎልቶ ስለተሰበከ ምጽዋትን ለተቸገሩ መስጠት በጠቅላላ የኢትዮጵያውያን ታላቅ መንፈሳዊ እሴት ነው፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ የማኅበረሰባችን ማኅበራዊ ዋስትና ይኸው ክርስቲያናዊ ባህላችን ነው፡፡ የቀድሞው፣ የዛሬውም የቆሎ ተማሪ የተማረው እና እየተማረ ያለው ቤተ ክርስቲያን በዘረጋችውና በሺሕ በሚቆጠሩ ዓመታት በዘለቀው በዚሁ ተቋም አካል ጽኑ ሃይማኖታዊ ባህል እንጂ በመንግሥት ወይም በሌሎች ድጋፍ አይደለም፡፡ በአጠቃለይ ቤተ ክርስቲያን ለተራቡት ቀለብ፣ ለታረዙት ልብስ፣ ለሕሙማን ፈውስ፣ ለአረጋውያን መጦሪያና ለእጓለምውታን ማሳደጊያ የሆነ ማኅበራዊ ዋስትና ለማረጋጥ በማስተባበር የተቻላትን ሁሉ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
እነዚህ መኅበራዊ ተቋማት እንደዘመናችን ዓይነት መዋቅር ባይኖራቸውም በስንበቴና በጡት ልጅ እና በመሳሰሉት ማኅበራዊ መጠሪያዎች የሚታወቁ ማኅበራዊ ዋስትናዎች ነበሩ፡፡ ዘመናዊ የማኀበራዊ ዋስትና በኢትዮጵያ እሰከሚጀመርበት ድረስ ጧሪ የሌላቸው ሰዎች እና አሳዳጊ ያጡ ሕፃናት በዚህ መንገድ ሲረዱ ኑረዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት ከተመሠረቱም በኋላ ቤተ ክትስቲያን አዲሶቹን ተቋማት መሥርታ የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎቷን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
በድርቅ ጊዜ ርዳታን በማስተባበር ስደተኞችን መርዳት
ቤተ ክርስቲያን የተቸገሩትን መርዳት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተግባሯ በመሆኑ ተግባሩን ስታከናውነው ኖራለች፡፡ ዛሬም በዘመናዊ መልክ ልማትና ተራድኦ ኮሚሽን በማቋቋም ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት እህል ዘይት እና ሌሎች ምግቦችን በማቅረብ የሰብአዊ እርዳታና መልሶ ማቋቋም ተግባር አከናውናለች እያከናወነችም ትገኛለች፡፡
መንፈሳዊ ማኀበራትን መደራጀት
ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምሳሌ የሚሆኑ ዝክሮች፣ ሰንበቴዎችና ማኅበሮች ወዘተ በስፋት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የተቀደሱና ጠናካራ ትውፊቶች የበጎ አገልግሎት ለመሰጠት አመቺ ናቸው፡፡ በገጠሩ አካባቢ በስፋት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በድንገት ሀብት ንብረቱ ቢቃጠልበት ርዳታ ያደርጉለታል፡፡ እንዲሁም ጧሪ ዘመድ ሳይኖረውና የሚሠራ ጉልበቱ ሲደክም ከቤታቸው በማስቀመጥ ተፈራርቀው የጦሩታል፡፡ ይህም ተግባር መጽሐፍ ቅድሳዊ ተግባር በመሆኑ በሕዝቡ አኗኗር ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደሩ ለዚህ ድርጊት የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ክፍተኛ ነው ::

፪ መልካም ዜጋን በማፍራት

ሰው ሁሉ ለሚኖርባት ዓለም ነጻና ክቡር ዜጋ ነው፡፡ዜግነት የተፈጥሮ ሲሆን መልካም ዜግት ግን የመልም ጠባይና ምግባር ውጤት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛና ቅድስት በመሆኗ ዜጎች ሁሉ በሃይማኖትና በምግባር ለሀገራቸውና ለሰማያዊት ርስታቸው መልካምና ታማኝ እንዲሆኑ ከማስተማርና ከመምከር የተቆጠበችበት አፍታ ጊዜ የለም፡፡ ምንም እንኳን በሥልጣኔ ስም የሚመጡ ጉዳዮች የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢፈታተኑትም ቤተክርስቲያን ግን ከጥንት ጀምሮ ልጆቿ በሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው የሀገርና የወገን አለኝታዎች እንዲሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርታለች፡፡

፫ የሥራ ባህልን በማዳበር

ሥራ የኑሮ መሠረት መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡የምትመራባቸው ቅዱሳት መጻሕፍትም የሥራን ጠቃሚነት በስፋት የሚተነትኑና የሥራን ባህል የሚያዳብሩ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአባታችን አዳም ገነትን ያበጃት ይጠብቃትም ዘንድ ሓላፊነትን ሰጥቶት ነበር፡፡ አዳም ከተሳሳተም በኋላ ጥሮ ግሮ በወዙ እንዲበላ፣ በስንፍና ተዘልሎ እንዳየቀመጥ፣ በወገኖቹ ላይ ጥገኛ ሆኖ እንዳይከብድባቸው ይልቁንም የድካሙን ፍሬ ቢመገብ መልካም እንደሚሆንለት ተነግሮታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መሠረት በማድረግ ልጆቿ ዘወትር በሥራ የተጠመዱ እንዲሆኑ ይህ ካልሆነ ግን አእምሮአቸው የዲያብሎስ ተገዥ እንደሚሆን ታሰተምራለች፡፡ ከዚህ አኳያ ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡን ሁለንተናዊ እድገት በማጽናት ለኢኮኖሚ ጤናማ እድገት፣ ለሕዝቡ ልማትና ደኅንነት መጠበቅ የበኩሏን ድረሻ እየተወጣች ነው፡፡

፬∙ሥነምግባርን በማሰተማር

ሥነምግባር የሚለው ቃል በሥራ ማማር፣ የሥራ መልካምነት ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ክርሰቲያኖች በጎ ሥራን እንዲሠሩ፣ ሰዎችን ያለምንም ልዩነት እንዲወዱ፣ የራስን ሰውነት ሕይወትና ክብር ከሚጎዱ ዲርጊቶች እንዲረቁ ሕይወታቸውን በቅድስና መንፈሳቸውን በንጽሕና እዲያዙ ታሰተምራለች፡፡ ከዚህም ትምህርቷ የተነሣ ምእመኖቿ በጎ ሕሊና እንዲኖራቸው፣ ከአንደበታቸው መልካም ቃል እንዲወጣ ንግግራቸው ሁሉ ከቁጣና ከትዕቢት የራቀ ጠብን ከመጫር ይልቅ ሰላምና እርቅ አንድነት እንዲያወርድ ወደ እግዚአብሔር መቅረብና ከእርሱ ጋር ሊያኖር የሚችል መልካም ሥራን መሥራትን የሚፈልጉ እንዲሆኑ አድረጋለች፤ እያደረገችም ነው፡፡ በማኅበራዊ ሕይወትም የሌላውን ድካምና ስሕተት ለቅመው ከመክሰስና ከመተቸት ይልቅ ባለማወቅ ያጠፋነውን ወደ ማወቅ አድርሰው ያርሙታል፣ የደከመውን ያበረቱታል፡፡ ክፉውን ወደ መልካም ይለውጡታል፡፡ ሕይወታቸው በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ሳይሆን በሰውም ፊት የተገለጠ ሰለሆነ በኅብረተሰቡም ፊት መልካም የሆነውን የፈጽማሉ፡፡ ‘’ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታው ማነም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ  ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለንና’’ ፡፡ በአጠቃለይ ቤተ ክርስቲያን ባላት የሥነ ምግባር ትምህርቷ ኅብረተሰቡ ለእግዚአብሔር እንዲሁም ለሀገሩና ለባልንጀራው ታማኝ እንዲሆንና ሓላፊነቱን፤ ተጠያቂነቱን በአግባቡ እንዲወጣ፤ ያለ እድልዎ ሥራን እንዲያከናውን በማሰተማር ሙስናን በመከላል ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ ስታበረክት ቆይታለች እያበረከተችም ትገኛለች፡፡
ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን ፤ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ፤መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ፡፡ በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ መሠረት ቤተ ክርስቲያን የእንግዚአብሔር የሆነውን አሥራት በኩራት ለቤተክርሰቲያን ግብርን ደግሞ ለመንግሥት በወቅቱ እንዲከፍሉ ለማድረግ የማይናቅ ድርሻ ተወጥታለች፡፡ ይህን ማለት የሚያሰደፍረውም፡-

 • አስተምህሮዋ አንዱ ለአንዱ እንዲታዘዝ፤ በትሕትና እንዲኖሩ ፈረሃ እግዚአብሔር እንዲኖረው ከሱስ ከባዕድ ተግባር ራሱን እንዲጠብቅ እና መልካም ዜጋ እንዲፈጠር የሚያደርግ በመሆኑ ነው፡፡
 • ለረጅም ዘመናት በቄስ ትምህርት ቤት ትውልድን በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ለሓላፊነት የሚበቃ እና ጠንካራ ዜጋ ለምድረግ ከሥር ኮትኩታ በማስደግ ያደረገችው እሰተዋኦም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
 • እሰከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የግብረ ገብ ትምህርት ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን እንዲሰጥና በሥነ ምግባር የታነጹ ዜጎች እንዲኖሩ ያደረገችው አሰተዋኦ  ከፍተኛ ነው፡፡

በተለይም በዚህ በዘመነ ሉላዊነት /Globalization/ በተለያየ መልኩ የሥነ ምብናር ችግር እየገጠመው ያለውን ትውልድ፣ በተሻለ መለኩ ለመቅረጽ መንግሥት በኮሚሽን ደረጃ አቋቁም የሚታገልበትን ሙስና ከሥሩ የሚነቅል ሥራ ለመሥራት ቤት ክርስቲያን ካለባት ሓላፊነት አኳያ እያደረገችው ያለው ትውልድን በሥነ ምብባር የማነጽ ሥራ የሃይማኖቱ ግዴታ እንደሆነ ያመለክታል፡፡

፭∙ በጤና ጥበቃ ዘርፍ በመሳተፍ

ጤና ማለት የበሽታ አለመኖር ብቻ ሳይሆን የአንድ ሰው /ማኅበረሰብ/፣ አካላዊ /physical/፣ ሥነ ልቡናዊ /psychological/ ማኀበረሰባዊ /social/ አእምሮአዊ /mental/ እና ሃይማኖታዊ ደኅንነት / Spritual wellbeing /  ነው፡፡ አስከፊ በሆነ ድህነትና ችግር ውስጥ ላለ ኅብረተሰብ የጤና ችግር ትልቁን ቦታ የሚይዝ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ከሥጋ ሕመም ባሻገር የሚፈጥረው የአእምሮ ጭንቀት የአንድ ኀብረተሰብ ክፍልን ምርታማነትና ውጤታማነት እጅጉን ይጎዳል፡፡ ቤተ ክፍስቲያን የጤናውን ችግር ለመቅረፍ ያላትን አስተዋጽኦ የሚከተሉትን መዘርዘር/መጥቀስ ይቻላል፡፡

 • መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ደኀንነትን በመስጠት
 • አዕምሮአዊ ጤንነት እንዲኖር በማድረግ
 • ሥነ ልቡናዊ ጤንነት በመስጠት
 • ዘመናዊ ጤና ተቋማት ማስፋፋትና የመሳሰሉትን  

፮∙ በትምህርት ዘርፍ 

ባለአእምሮ ሰው በደማዊነት አእምሮው እያዘገመ እንዳይኖር በትምህርት ድንቁርናን አርቆ፣ ክፉና ደጉን ለይቶ በዕውቀት ዓለም እንዲኖር ልቡናን የሚያጠራና የሚወለውል፣ ማኅበራዊ ነጻነትን የሚጎናጽፍ ዕውቀት ማግኘት ያስፈልገዋል፡፡ ሥጋዊና መንፈሳዊ ዕውቀት በሰው ልጆች አእምሮ ተቀርጾ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ኢኮኖሚዊ ሕይወታቸውን ጥበብ በተሞላበት የአኗኗር ዘይቤ እንዲመሩ የዕውቀት በር መክፈቻ ቁልፍ ነው፡፡

የዚህም ዓላማ፣

ጊዜውን የሚዋጅ ንቃተ ኅሊናው የዳበረ ትውልድ ወይም ዜጋ ለመፍጠር ከቄስ ትምህርት ቤት እስከ ከፍተኛ ተቋማት ሥርዓተ ትምህርትን መቅረጽ እና መረጃ መሳሪያዎች ማዘጋጀት የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ፊደልን ከነአገባቡ ይዛ የዓለም የራሳቸው ፊደላት ካሏቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን መገለጫዋም የግእዝ ፊደላት ባለቤት መሆኗ ነው፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ውጭ ሀገራት የግእዝ ትምህርት በፋኩልቲ ደረጃ መቋቋም ለጥናትና ምርምር ዓይነተኛ እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከ1930ዎቹ በኋላ እንደ ትምህርት ሚኒስቴርነ ስታገለግል የቆየችው ቤተ ክርስቲያን የዘመናዊ ትምህርት ቤት በሀገራችን መስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ በኋላም ቢሆን የራሷ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ልጆችና ወጣቶች በሥነ ምግባር እየታነጹ፤ ለሕዝብና ለመንግስት የሚያገለግል አገር ወዳድ ዜጎችን በማፍራት በዘማናዊው ትምህርት ድርሻዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡

፯. ታረክን እና ጥበብን በመመዝገብ

ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ መነሻው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ብዙው ዓለም ገና የጽሕፈትን ጥበብ ገንዘብ ባላደረገበት ዘመን የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ከበግ፣ ከፍየልና ከልዩ ልዩ እንሰሳት ቆዳ ብራና ፍቀው፣ ቀለማትን በጥብጠው ብርዕ ቀርጸው የኢትዮጵያ ብሎም የውጭ ሀገራትን ታሪክ በመመዝገብ ለጥናትና ምርምር መነሻ ሆነዋል ማለት ይቻላል፡፡

፰.  የባህል አስተዋጽኦ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲን መሰረቷ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የምትሰብከውም ሃይማኖትን ከትውፊት፣ ትውፊትን ከሥርዓት፣ ሥዓትን ከባህል ጋር በማቀናጅት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲን በሥነ ምግባር ትምህርቷ በኢትዮፕያ ውስጥ ለሚደረግ መልካም ባህሎች መነሻ ናት፡፡ በዚህ መሰረት ቤተ ክርስቲያን ያላትን ባህላዊ አስተዋ    ጽኦ ለመመልከት ያህል እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡

 • በአንድ ማዕድ የመመገብ ባህል /የአመጋገብ ሥርዓት/፣
 • የአነጋገር ሥርዓት፣
 • የእንግዳ ተቀባይነት ባህል፣
 • አለባበስ/ ነጭ ልብስ፣ ወንድ የወንድን ሴት የሴት ወ.ዘ.ተ/፣
 • ጋብቻን የማክበር ባህል
 • የጀግንነት እና የሀገር ፍቅር ባህል፣
 • ተከባበሮ የመኖር  እና የአብሮነት ባህል፣ ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡