“ሳይንስ ከመጽሓፍ ቅዱስ በታች ነው” ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሁለተኛው ዓመቱ ጠቅላላ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው እያካሄደ መሆኑን ከሰዓት በፊት መዘገባችን የሚታወስ ነው። ጠቅላላ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ከሰዓት በኋላም ቀጥሎ ውሏል።

ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብር “ቤተ ክርስቲያንና ስትራቴጂያዊ አመራር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሥልጠና በሊቀ ትጉኃን በድሉ አሰፋ ዓለማየሁ ቀርቧል።

ሥልጠናው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት የተዘጋጀ መሆኑን ተገልጿል።

ሥልጠናው አመራርን በተመለከተ ብዙ ሐሳቦችን የዳሰሰ ሲሆን በስትራቴጂያዊ አመራር፦ ፕሮግራም፣ የድርጊት መረሐ ግብር፣ ዕቅድ፣ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ፣ መሪ ዕቅድ እና ስትራቴጂያዊ አመራርን ያቀፈ መሆኑን ተብራርቷል።

ስትራቴጂያዊ አመራሩ ያስፈለገበት ምክንያትም በቤተ ክርስቲያኑ ፈጣንና ቀልጣፋ የሆነ አሠራር እንዲኖርና ውጤታማ ሥራ በአግባቡ እንዲሠራ የሚረዳ መሆኑን ተገልጿል።

ከክፍል አንድ ሥልጠና በኋላ፡ በቀረበው ሥልጠና መሠረት ጥያቄዎችን ተነስተው መልስና ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱም፡ ቤተ ክርስቲያናችን አመራርና አስተዳደርን በተመለከተ የኦርቶዶክስ ሊቃውንት ትምህርት መሠረት በማድረግ መሪ ዕቅድ በማዘጋጀትና በዕቅዱ በመምራት ለሌሎች ምንጭና ምሳሌ መሆን እንዳለባት ተገልጿል።

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የአመራር መነሻው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን በመግለጽ አመራርን በተመለከተ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል።

ብፁዕነታቸው ስልታዊ አመራር በሙሴ ነው የሚጀምረው፤ ሌሎች እሱን ነው ሳይንሳዊ ያደረጉት ብለዋል።

ከዚህ በመነሳትም “ሳይንሱ ከመጽሓፍ ቅዱስ በታች እንጂ በላይ አይደለም” በማለት ቤተ ክርስቲያን ያላትን የአመራርም ሆነ የአስተዳደርን ጥበብና ሀብትን በአግባቡ ልትጠቀምበት ይገባል ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ሊ/ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የሰባቱ ክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጆችና ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃነ መናብርት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው አንግዶች ተገኝተዋል።

ጠቅላላ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ነገም ይቀጥላል …

ዘገባ በመ/ር ኪደ ዜናዊ

ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published.