ስለተሻሻለው የሕገ ቤተ-ክርስቲያን ድንጋጌ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ራሱን ስለቻለበት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ቅዱስ ሲኖዶስ በወከላቸው ብፁዓን አባቶች በኩል ገለጻ ተደረገ

ህዳር 1 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና በርካታ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች እና ሠራተኞች እንዲሁም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለአሻሻለው ሕገ ቤተ-ክርስቲያንና ራሱን ስለቻለው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት ገለጻ ተደርጓል ።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙትና አጭር ንግግር ያደረጉት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በወርኃ ጥቅምት በተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለውን ብልሹ አሠራርና የመልካም አስተዳደር እጦት ለማስተካከል ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት ተወያይቶና ሕገ ቤተ-ክርስቲያኑን አሻሽሎ እንደሌሎቹ አህጉረ ስብከቶች ግልፅ የሆነ አሠራር በመዘርጋትና ያለማንም ጣልቃ ገብነት ራሱን በቻለ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ ከወሰነ በኀላ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅንም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ መድቧል፣ ዛሬ ወደዚህ የመጣነው በየሚዲያው ከሚናፈሰው ስሁት ዜና ወጥታችሁ ትክክለኛውን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አሠራር ለእናንተ ግልፅ ለማድረግ ነው፣ ስለሆነም ይህንን እውነት በሚገባ ተረድታችሁ የተመደቡላችሁን ብፁዕ አባት አክብራችሁ እየተመካከራችሁና እየተግባባችሁ በጋራ እንደምትሰሩና ሀገረ ስብከቱን እንደምትለውጡ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል::

በመቀጠልም የጅግጅጋ እና የምሥራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ከአሁን በፊት በአዲስ ሀገረ ስብከት ሲፈጸሙ የነበሩ ብልሹ አሠራሮችን ስንመለከትና ስናዝን ቆይተናል አሁን ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ሀገረ ስብከቱ ራሱን እንዲችል በመደረጉ በተጠያቂነትና በግልፅነት ይሰራል ለሌሎች አህጉረ ስብከቶችም መልካም አርዓያ ይሆናል ብየ አምናለሁ፣ ለዚህ የተሻለ ለውጥ ደግሞ የእናንተ በየደረጃው ያላችሁ የሥራ ኃላፊዎች ሚና ትልቅ ነውና ራሳችሁን አዘጋጅታችሁ ከተመደቡላችሁ አባት አጠገብ ቁሙ፣ በነገርም ሁሉ እርዷቸው በማለት መልእክታቸውን ሲያስተላልፉ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ደግሞ ቤተ-ክርስቲያን በውስጥ እና በውጪ ብዙ ጫና እንዳለባት ይታወቃል፣ እነዚህን የሁለትዮሽ ጫናዎች በመቀነስም ሆነ በማስወገድ ደግሞ ከእኛ ብዙ ይጠበቅ ነበር እኛ ግን ቤተ ክርስቲያንን ልንጠቅም ይቅርና ራሳችንም ሸክም ሆነንባታል፣ ከዚህ ውድቀታችን እነነሣ ነገ ለሚመጣው ትውልድ የምናስረክባትን ቤተ ክርስቲያንም ዛሬ ላይ እናስተካክል በማለት ጠንካራ መልእክት አስተላልፈዋል::

በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የሆነው ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፣ የእርሡን ፈቃድ ለመፈጸም ደግሞ ዝግጅ ሆኛለሁ ይህንን ሀገረ ስብከት መምራት በእጅጉ ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ ሆኖም ግን መንፈሳዊ ትጥቄ አጥብቄ ከብፁዓን አበው አባቶቼና ከእናንተ ጋር በመመካከርና የእግዚአብሔርን እርዳታ በመጠየቅ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠኝን አደራ እወጣለሁ፣ በየደረጃው ያላችሁ የሥራ ኃላፊዎችም ሳንፈራራና ሳንራራቅ በልካችን ተቀራርበን ሀገረ ስብከታችንን ሁልጊዜ ከሚነሳበት መጥፎ ስም ነፃ እናወጣዋለን፣ በማለት ቃል ገብተዋል::አያይዘውም የቅዱስ ሲኖዶስን ትእዛዝ አክብረውና በቦታው ተገኝተው የቅዱስ ሲኖዶስን አቋምና ውሳኔ ለታዳሚዎቹ ግልፅ ያደረጉትን ተወካይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትንም አመስግነዋል::

ወደፊት በሚኖረን ጊዜም በእያንዳንዱ የሀገረ ስብከታችን ጉዳዮች ዙሪያ በጥልቀት የምንወያይበትን መድረክ እናዘጋጃለን እስከዚያው ግን ጸሎታችሁና ደገኛ ሐሳባችሁ እንዳይለየኝ በማለት አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል::

መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ

1 reply
  1. Kesis Biruhtesfa Siyoum
    Kesis Biruhtesfa Siyoum says:

    ዘገባዉ ጥሩ ነዉ፤ ነገር ግን የሃገረ ስብከቱ ነዋሪ ምዕመናን እና ምኁራን ጥሪ ይደረግላቸዉ እና ችግሩን እና መፍትሄዉን መወያየት ይሻላል፤ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ከተፈለገ አይድበስበስ !

    Reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *