ስብከተ ወንጌል

“ሑሩ ውስተ ኩሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት” ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንግልንም ለፈጥረት ሁሉ ስበኩ

ወንጌል፡- ወንጌል የሚለው ቃል “ዩአንጌሊዎን” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው በግእዙ ቋንቋ ብሥራት ይባላል፡፡ የግሪኩም ይሁን የግእዙ ትርጉም የምሥራች ማለት ነው፡፡

ወንጌል በሚል ቃል የተጠራው የመድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዜና ልደቱና ትምህርቱ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት የሠራው የአድኅኖት ሥራ ሁሉ ወንጌል ተብሏል፡፡
ወንጌል ከላይ እንዳየነው የምሥራች ሲሆን የልዑል አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ መወለዱን ስለሚያበሥር ነው፡፡ “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” ሉቃ 2፡10

በዚህም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ጸጋ ወደ ቀደመ የልጅነት ክብሩ እንደተመለሰ ሲያስረዳ እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች በማለት መልአኩ ለኖሎት አበሰራቸው ከዚህ የበለጠ የምሥራች የሚባል ምን አለ? የተወለደው የሁሉ መድኃኒት ነውና ሰውን ሁሉ አዳነ ይህ ለእኛ ከደስታ ሁሉ በላይ ደስታ ነው በምንም ዋጋ የማይተመን እግዚአብሔር ለእኛ የተሰጠበት የምስራች ቃል ነው፡፡ እንግዲህ ስብከተ ወንጌል ሲባል የወንጌል ትምህርት ሲሆን ይህም የምስራችን ቃል ላለተበሠሩ ማብሠር፣ ላልተሰበኩ መስበክ፣ ላልሰሙ ማሰማት ፣ማስተማር ፣ማስረዳት ፣ማሳማን ፣በቃለ ወንጌል አምነው ጸንተው እንዲኖሩ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ከተሰጣት የአገልግሎት ሥራ ሁሉ ቀዳሚም ደኃሪም የምስራቹን ቃል መስበክ ነው፡፡ ቀጥሎ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በማስተዋል እንመልከት፡፡

“እንዲህም አላቸው ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ያመነ የተጠመቀም ይድናል” ማር 16፡15
“ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላዓለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው” ማር 16፡8
“የወንጌል ሰበኪነትን ሥራ አድርግ አገልግሎትህን ፈጽሞ” 2ጢሞ4፡5 “በጊዜውም አለጊዜውም ወንጌልን ስበክ”

 

የስብከተ ወንጌል ዓላማ

ወንጌልን የማስተማር ዓላማው ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡ ወንጌል በመጀመሪያ የተሰበከው በባለቤቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ማቴ 4፡17 ሉቃ 8፡1/ በመቀጠልም ከላይ እንደተገለጸው የቃሉን ትምህርት እየሰሙ የሚሰራውን የማዳን ሥራ እያዩ ያስተማራቸውን ደቀመዛሙርቱን ለዚህ ምስክሮች እንደሆኑ በአንደበታቸውም የምስራቹን ቃል እንዲሰብኩ በሕይወታቸው ሁሉ የሚመሰክሩበትን የዕውቀትና ጥንካሬ መንፈስ አጎናጸፋቸው ሉቃ 24፡47 – 53 እነሱም እንዲህ እያሉ መሰከሩ፡፡

“ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን” 1ዮሐ 1፡1 እንዳሉትም፡-

  • ጆሮአቸው የሰማውን ቃለ ወንጌል ሰበኩ፤
  • ዓይናቸው ያየውን የማዳኑን ሥራ መሰከሩ፤
  • በእጆቻቸው የዳሰሱትን ሁሉ አረጋግጠው ተናገሩ፡፡

በዚህ የወንጌል ስብከታቸው ልባቸው የተነካ ሰማዕያን ወንድሞች ሆይ እንድንድን ምን እናድርግ አሉአቸው የሐዋ ሥራ 2፡37፣16፡30
ከጨለማ ወደ ሚደነቀው ብርሃን የሚያወጣውን የምስራቹን ቃል ከሰሙ በኋላ ሐዋርያትን ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ ምንስ መሥራት ይገባናል ብለው ሰሚዎቹ መጠየቃቸው የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ከሐዋርያቱ ጋር አብሮአቸው ይሠራ እንደነበር ማስረጃ ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅ/ማርቆስ “እነሱ ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ ጌታም ከእነሱ ጋር አብሮአቸው ይሠራ ነበር በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር” በማለት እንደጻፊው /ማር16፡20/ በዚሁ ሁኔታ የቃሉ ባለቤት የተናጋረውን ልበ አእምሮ እያበራ የሰሚውን እዝነ ህሊና እየከፈተ የምስራቹ ቃለ ወንጌል ለሁሉም ደረሰ በዘባነ ኪሩብ የሚመሰገነው ልዑል አምላክ በጎል የተወለደው ሰዎችን ለማዳን በመሆኑ ታላቅ ደስታን አጎናጸፈ“ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና” ቲቶ 2፡11

ስለሆነም ሐዋርያቱም ከነሱ ቀጥለው በወንጌል አገልግሎት ላይ የተሾሙ ሁሉ በቃለ ወንጌል እያሳመኑ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ አገለገሉ፡፡

 

ስብከተ ወንጌል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ወንጌልን በሁለት መንገድ ትሰብካለች እነዚህ የስብከተ ወንጌል ዓይነቶች ሕይወትና ዕውቀት ናቸው፡፡

1.    በዕውቀት

ከአበው ሐዋርያት ጀምሮ የተምሮ ማስተማርን ፈለግ በመከተል የወንጌሉን ሙሉ ዘርዓ ቃል በአእምሮአቸው ሰሌዳ በመጻፍ ትርጓሜውን በርቱዕ አንደበታቸው የሚተነትኑ ምሁራንን በማፍራት የዕውቀት ማኅደር መሆኗ ይታወቃል ፡፡ እነዚህ ምሁራኖቿ የሚናገሩ መጻሕፍት ናቸው ፡፡ ከእነዚህ የሚቀዳው የትርጓሜ ወንጌል ምሥጢር ሌላውን የወንጌል ደቀመዝሙር ይወልዳል ይህ አንዱ ትልቁ የወንጌልን ምሥጢር በከፍተኛ ትርጓሜ ደረጃ የመተንተን የማስረዳት መንገድ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ቀለል ባለ አገላለጽ ለሰሚዕ አእምሮ በሚመጥን ደረጃ ሆኖ ከሕይወታቸው ጋር እያዛመዱ የምስራቹን ቃል መስበክ ነው ለዚህ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምሁራኖቿ የበለጠ የክህሎት ማበልጸጊያ መንፈሳዊ ከሌጆችን በማቋቋም አሠልጥና የክህሎት ምስክር ሰጥታ የሰለጠኑትን በመላው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በዓለም ዓቀፍ ሁሉ አሰማርታ እየሠራች ትገኛለች፡፡

2.    የሕይወት ስብከት

በሕይወት መስበክ በዕውቀት ከሚሰበከው በላይ ሌላውንም ያሳምናል የሕይወት ስብከት ስንል ጾረ መስቀሉን በሕይወት ትክሻ ተሸክሞ ክርስቶስ ለሁሉም የተቀበለውን መከራ ማሳየት ነው፡፡ ሐዋርያው “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራልን” እንዳለው /2ቆሮ4፡11፣ ቁላ1፡24/ የዓለምን የሞቀ የደመቀ ካባ ከመልበስ የጣመ የላመ ከመጉረስ የሕይወትን መስቀል ተሸክሞ እንደ ወንጌል ቃል በእግዚአብሔር መንግሥት ከፀሐይ ሰባት እጅ በርቶ ለሌላው ማብራት /ማቴ 13፡43/ ነው፡፡

እንግዲህ በዚህ የሕይወት ሰብከት ወንጌሉን በቃል ሳይሆን በሕይወት የረተጎሙ ብዙ ቅዱሳንና ቅዱሳት በማህጸኗ ተጸንሰው ተወልደው ፍሬአቸውን አበርክተዋል፡፡ ለዚህ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን እና ኢትዮጵያን በደንብ አድርጎ መመልከት በጆሮ ከሚሰሙት በላይ ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡ በወርቃማ የሃይማኖታዊ ቀለም የተጻፉ ገዳማቶቿ ሕያዋን ምስክሮቿ ናቸው፡፡ ዓለም ያለውንና የነበረውን በዘመንዮሽ ቁሳዊነት እየለወጠ የራሱን ማንነት እያጣ ባለበት በአሁኑ ዘመን እንኳ የእስዋ ገዳማት የወንጌል ቃል የሕይወት ትርጉም አንባዎቿ ናቸው፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያዊቷ /ብሔራዊቷ/ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን በወንጌል የተመሰረተች ቃለ ወንጌልን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር /በሕይወት/ የምትሰብክ ሕያዊት ቤተክርስቲያን ናት፡፡

 

ስብከተ ወንጌል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት

አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚመራቸው ከ160 በላይ የሆኑ ታላላቅ ካቴድራሎች፣ ገዳማትና አድባራት ያሉት ሲሆን ሀገረ ስብከቱ የሀገሪቷ ዋና ርዕሰ ከተማ በሆነችው ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሥራውም እጅግ ሰፌ ነው፡፡
ሀገረ ስብከቱ የቤተክርስቲያኗን መሠረታዊ የወንጌል ስብከት አገልግሎት ለማከናውን እንዲቻል ካሉት ትላልቅ መምሪያዎች አንዱ የስብከት ወንጌል መምሪያ ነው በዚህ መምሪያ አስተባባሪነት ደግሞ በ160 አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ እጅግ ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል በተለይ ባለፉት ዓመታት የስብከተ ወንጌል የኅብረት ጉባኤ በመባል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መስራችነት በሀገረ ስብከቱ ሙሉ አስተተባባሪነት በመላዋ አዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት መርሐግብሮች

  1. የየዕለት ጉባኤያት ዘወትር ከ11 – 1፡00 የሚካሄዱ
  2. የወርኃዊያን ልዩ ጉባኤያት በልዩ ዝግጅት የሚካሄዱ
  3. የወርኀዊያን ጉባኤ በዓላት በልዩ ዝግጅት የሚካሄዱ
  4. የዓመታውያን  ጉባኤያት በዓላት በልዩ ዝግጀት የሚካሄዱ  ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ሌሎችንም የተለያዩ የስብከተ ወንጌል ልዩ ጉባኤያት በማዘጋጀት ሀገረ ስብከቱ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እያስተባበረ፣ እየመራና እያሠራ ይገኛል፡፡

ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምን መደረግ አለበት

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ማጠናከር መሆኑ የታወቀ ነው፤ በተለይ ለአገልግሎት መቃናት በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት አገልግሎቱ በሚጠይቀው የሙያ ብቃት መምህራንን በመመደብ፤ አቅምን ያገናዘበ በቂ በጀት በመበጀት፤ ለሥራው አስፈላጊ ማቴሪያሎችን በማሟላት፤ አገልግሎቱ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ እንዲሰጠው ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
የደረስንበት ዘመንና እየተቀበልነው ያለው ጊዜ በሁሉም ዘርፍ በግሎበላይዜሽን አስተሳሰብ ጥላ ውስጥ እያስባገን ስለሆነ ሰዎች በማዕበሉ አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ የወንጌሉን ቃል በምልዓት መስበክ አእምሮአዊ ሚዛናቸው ወዳልሆነ አካሄድ እንዳያጋድል ማድረግ የቤተክርስቲያኒቱ እና የሀገረ ስብከቱ ሃይማኖታዊ ኃላፊነት ነው፡፡