” ቅድምያ ከሁሉም በላይ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ላይ መሥራት ያስፈልጋል” ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቅድምያ ከሁሉም በላይ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ መልእክት አስተላለፉ።
ብፁዕነታቸው መልእክቱን ያስተላለፉት በቦሌ ቡልቡላ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤ/ክ በመገኘት አዲስ እየተገነባ የሚገኘውን ግዙፉን ሕንጻ ቤ/ክን በጎበኙበት ነው።
በግንባታ ላይ የሚገኘው ሕንጻ ቤተክርስቲያን 5200 ካሬ ላይ ያረፈ ስለመሆኑም ተገልጿል።
ብፁዕነታቸው ቤተክርስቲያኑ ሊሠራ ላቀዳቸው G+2 እና G+3 ሕንጻዎችም የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
G+2 ሕንጻው ለቢሮ አገልገሎት የሚውል ሲሆን G+3 ሕንጻው ደግሞ ለቤተክርስቲያኑ ገቢ ማስገኛ እንደሚውል ተገልጿል።
ብፁዕነታቸው ለቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ለመልአከ ጽዮን አባ ገብርኤል ወ/ዮሐንስ (ቆሞስ) በጥቂት ወራት ላሳዩት የመልካም አስተዳደር ውጤት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በሕንጻ ኮሚቴው፣ በሰበካ ጉባኤውና በምእመናን መካከል ያለውንም ኅብረት አድንቀዋል።
ከዚህ በፊት በቤተክርስቲያኑ በመገኘት የነበረውን የአስተዳደርና የልማት ሥራዎችን እንደጎበኙ ብፁዕነታቸው አውስተዋል።
አያይዘውም በጊዜው አስተዳደራዊ ችግሮች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
ሀገረ ስብከቱም ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ጠንካራ የአመራር ልምድ ያላቸውን አባት መልአከ ጽዮን አባ ገብርኤል ወ/ዮሐንስን (ቆሞስ) ለቤተክርስቲያኑ እንደመደበ ገልጸዋል።
በመሪና በተመሪ መካከል ፍቅር፣ አንድነትና ሰላም ካለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ይህ በግንባታ ላይ የሚገኘው ሕንጻ ቤተክርስትያን ምስክር ነው ብለዋል።
ቅድምያ ከሁሉም በላይ ፍቅር፣ አንድነትና ሰላም ላይ ከተሠራ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት አይከብድም ሲሉም አብራርተዋል።
አቶ አምዴ እና አቶ ፀሐይዬ የተባሉ ሁለት አባቶች ከመጀመሪያ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ሲመሠረት ጀምሮ ላደረጉት አስተዋጽኦ የካባ ሽልማት ከብፁዕነታቸው ተቀብለዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፣ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ የሀገረ ስብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፣ መልአከ ምሕረት በቃሉ ወርቅነህ የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊና የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን አባ ገብርኤል ወ/ዮሐንስ (ቆሞስ) ተገኝተዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *