በቤቴል ደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በሰላም ለመፍታት ከስምምነት ላይ ተደረሰ

ቤቴል ደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በኮልፌ ቀራኒዮ ክርለ ከተማ የሚገኝ ሲሆን በሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ጽ/ቤት ሠራተኞች ከአከባቢው ምዕመናን ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ የአስተዳደር ሠራተኞች ቢሮ ለ3ቀናት ያህል ታሽጎ መቆየቱ ይታወቃል።
በዚሁ መነሻነት ዛሬ ሚያዝያ 21/2012 ዓ.ም መልአከ ሕይወት አባ ኀይለ ገብርኤል ነጋሽ (ቆሞስ)የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ በደብሩ በመገኝት ከካህናትና ከምዕመናን ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። ቤቴል ደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቀደም ብዬ አውቀዋለሁ ያሉት ስራ አስኪያጁ የዚህ ደብር ካህናትና ምዕመናን የስራ ኃላፊዎች ለሥራ ሲዛወሩ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ካህንና ምዕመናን አሁን ምን ገጠማቸው ብዬ ነው ዛሬ ወደ ዚህ የመጣሁት፣ ችግር መቼም ይኖራል፣ ችግር ያልነበረበት ዘመንም አልነበረም፣ ትልቁ ነገር የተፈጠረውን አለመግባባት እንዴት እንፈታዋለን በሚለው ላይ መነጋገር አለብን፣ ቤተ ክርስቲያን ካስቀደምን የማንሻገረው መከራ አይኖርም፣ የእኛ ውግንና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው በማለት ሰፊና ጥልቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመቀጠልም የደብሩ የካህናትና የምዕመናን ተወካዮች የቦታውን ችግር ለዋና ስራ አስኪያጁ በተወሰነ መልኩ ችግሩን አስረድተዋል፣ የሀብት ብክነት፣ የፋይናንስ አያያዝ ችግር፣ ውሱን የሆነው መሬት በአግባቡ ያለመጠቀም ሁኔታና በጠቃላይ በደብሩ የመልካም አሰተዳደር እጦት እንዳለ አስረድተዋል።
አያይዘውም የቤቴል ደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል ጉዳይ አሳስቦት በመካከላችን በመገኘት የችግሩ ተካፋይ ስለሆኑ ከልብ እናመሰግናለን፣ እኛም ቢሮዎችን ማሸጋችን አግባብነት እንዳልነበረው ተረድተናል በማለት የታሸጉ ቢሮዎችን ከፍተዋል።
በመጨረሻም በአስቸኳይ አጣሪ ልዑካን ወደ ቦታው በመላክ በሚቀርበው ግኝት ላይ በመመስረት አስፈላጊ ዕርምት እንደሚወሰድ ክቡር ስራ አስኪያጁ ገልጸው፣ ሁሉም ሰው ወቅቱን መረዳት አለበት፣ ዓለማችን አሁን የገጠማትን የኮሮና ወረርሽኝ ፈተና በጸሎት፣ እራስን በመጠበቅ ለተቸገሩት ወገኖች በመርዳት፣ በመራራትና ወደ ፈጣሪ ከልብ ማልቀስ ይገባናል፣ እግዚአብሔርም ምህረትን ይልክልናል በማለት አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *