በቦሌ ቡልቡላ ፈለገ ዮርዳኖስ ቅዱስ ሚካኤል እና አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ችግኝ ተከላና የእርዳታ መርሐ ግብር ተካሄደ

❖ ገዳሙን የአንድነት ገዳም ለማድረግ ታቅዷል፤
❖ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳሙ የማጠናከር ድጋፍ ያደርጋል ።

የቡልቡላ ፈለገ ዮርዳኖስ ቅዱስ ሚካኤል እና አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ብዙ ዋሻዎች ያሉት ፈዋሻ ጸበል የፈለቀበት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለ ልዩና ድንቅ መንፈሳዊ ቦታ ነው።

ግንቦት 19/09/2012 ዓ.ም በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በገዳሙ በመገኝት ለመናንያን መነኮሳትና በገዳሙ ተጠግተው ለሚኖሩ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የደረሰባቸውን ጫና ለመቋቋም እንዲችሉ የምግብ እህል ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ራሳቸውንና ቤተ ሰቦቻቸውን ከበሽታው እንዲከላከሉ ሰፊ ትምህርት ተሰጧቸዋል።

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ መጋቤ ብርሀናት አባ ተክለ ያሬድ ተክለ ጎርጎርዮስ የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት መምሪያ ዋና ኃላፊና መልአክ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ በቦታው ተገኝተው ገዳሙን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን በገዳሙም ችግኝ ተክለዋል።

ክቡር መልአክ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ በወረርሽኙ ምክንያት ገዳሙ ችግር እንዳይገጥመው ሀገረ ስብከቱ የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፣ አያይዘውም በዚህ ትልቅና ሰፊ ገዳም የነገ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚወጡበት የመንፈሳዊ የትምህርት ማዕከል እንዲሆን ታስቦ እየተሰራ መሆኑን አሳዉቀዋል።

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትልቁ የአንድነት ገዳም ሆኖ እንዲቀጥል እየተሠራ መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

የዘገባው ምንጭ ፦ የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግኑኝነት ዋና ክፍል ነው

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *