በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አስተባባሪነት የተዘጋጀው የምሥጋና እና ዕውቅና መርሐግብር ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በቃሊቲ ጥምቀተ ባህር ማክበሪያ ደማቅ በሆነ መልኩ ተከናወነ

የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የጥምቀተ ባሕር ማክበሪያ ሥፍራ በተዘጋጀው መርሐ ግብር የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተስማ፡ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች፡ የክፍለ ከተማው የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰሎሞን፡ የክፍለ ከተማው አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በልዩ ልዩ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና ቀርቧል፡ ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሽልማትና የምሥክር ወረቀትም ተሰጥቷል፡
የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ ባደረጉት አጭር ንግግር መርሐ ግብሩ የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ በ2013 ዓ.ም የበዓለ ጥምቀት አከባበር ላይ በጉልበታቸው፡በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው እንዲሁም ያለችግር በሰላም እንድናከብር
በሰላምና ጸጥታው ዘርፍ ብዙ ለደከሙና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አገልጋይ ካህናት፡የሰ/ት/ቤት ወጣቶች አንድነት፡ለጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች እንዲሁም ለክፍለ ከተማው ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤትና ለአካባቢው ፖሊስ ኮሙኒቲ ጽ/ቤት ምሥጋና ለማቅረብና ዕውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ መርሐ ግብር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እንደነ ሳሎ ደ/ፀ ቅዱስ ጊዮርጊስና እና ቱሉ ዲምቱ ደ/ሰ/ቅ/ጊዮርጊስና ቅ/ሚካኤል የመሳሰሉ ጥንታዊና ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት በስፋት የሚገኙበት ክፍለ ከተማ መሆኑን ገልጸው፡ ወደፊትም የወንጌል አገልግሎቱን ከማስፋት ባሻገር ለገዳማትና አድባራቱ ጥንታዊነት የሚመጥንና ደረጃውን የጠበቀ የቢሮና የኪራይ ሕንጻ ለመገንባት በእንቅስቃሴ እንደሚገኝ አሳውቀዋል፡፡
የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ተወካይ መ/ብ ሙላት ክበቤ”የእንኳን ደህና መጡ ምስጋና አቅርበው፡ የተጀመረው ለውጥ እውን
ይሆን ዘንድ አስቸኳይ መልስ ለሚሹ ጉዳዮች
በተለየ ሁኔታ የባለ ጉዳይ ቀን እንዲመቻች፡ሁሉም የጥምቀተ ባህር ማክበሪያ ሥፍራዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያገኙ ዘንድ ለሚደረገው ጥረት በቂ ድጋፍ እንዲሰጥና በየቦታው ለሚነሱ የሰበካ ጉባኤ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ ይሰጣቸው ዘንድ አሳስበዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ብሩህ አእምሮ፡ሰፊ ሀብትና መሬት እንዲሁም አኩሪ ገድልና ታሪክ እያለን ማደግ አልቻልንም፡ምክንያቱም የመመሰጋገን
እና አንዱ የአንዱን ሥራ የማድነቅ ልምድ ስለሌለን ነው፡ዛሬ ግን ይህ በእናንተ ዘንድ ተተግብሮ ስላየሁት ኮርቻለሁ፡ ይህ ቦታ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበትም ቢሆን የእኛ ንብረት ሆኗል አሁን ግን በዚህ ቦታ ላይ ልማት አልምተን የአካባቢውንማኅበረሰብ በመደገፍ ማኅበራዊ ኃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል ያሉት ደግሞ የሀገረ ስብከቱ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ናቸው፡፡
በመጨረሻም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በክፍለ ከተማው አስተባባሪነት በተዘጋጀው የምሥጋና መርሐ ግብር ደስ መሰኘታቸውን ገልጸው ወደፊትም እንደዚህ ዓይነት መልካም ልምዶች እንዲቀጥሉ ሲሉ አባታዊ መመሪያና መልእክትም አስተላልፈዋል።


ዘጋቢ:- መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ:- በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ