በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ ሰባቱ ክፍለ ከተሞች ሪፖርት አቀረቡ

                                         በሚድያ ክፍሉ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ፤ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወ/ሐና እና የሀገረ ስብከቱ ዋና ክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት በክፍለ ከተማ ሠራተኞች በአዲስ ቅጥር፣ ሽግሽግ፣ ዙሪያ የተደረገው ጥናት ሪፖርት ቀርቧል፡፡ የ7ቱ ክፍለ ከተማ ሠራተኞች በእነርሱ ሥር ያሉትን ገዳማትና አድባራት ላይ ባደረጉት ፍተሻ የተወሰኑት አዲስ ቅጥርን ፣ ሽግሽግን እንደፈፀሙ ገልፀዋል፡፡ እነዚህም አብዛኛው በኢ-ሕጋዊ መልክ እንደተፈፀመ ነው የተረጋገጠው፡፡ በተለይ ደግሞ በአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት በሚደረግ ቅጥር በጣም ውስብስብና ሥርዓት አልባ እየሆነ የሚሄደበት ሂደት ስላለ በደንብ ታይቶ  ጠንከር ያለ አሠራር እንደሚያስፈልገው ገልፀዋል፡፡ በአንዳንድ አብያተ  ክርስቲያናት ያሉት ሠራተኞች ብንናገራቸውም የሚሰጡን መልስ አግባብነት የሌለው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ አጥቢያ ላይ በተመሣሣይ ሥራ ላይ ሁለትና ከሁለት በላ የሆኑ ሰዎች መቀመጣቸው ሌላ ችግር መሆኑም ተደምጧል፡፡

በሌላ መልኩ ከእነዚህ ከላይ ለቀረቡት ተግዳሮቶች ምን ብናደርግ ነው መፍትሔ የምናመጣው የሚለው ሐሳብ ቀርቦ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተጠቁመዋል፡፡ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ሲተከል በሚመደቡት አገልጋዮች ላይ ትልቅ ጥንቃቄ ቢደረግ፣ የራሱ የሆነ ወጥ ሥርዓት ቢቀመጥ፣ እኩልነትና ፍትሓዊነት ያለው አሠራር ቢኖር ከክፍለ ከተማ ጀምሮ እስከ አድባራትና ገዳማት የሠራተኞች ዝውውር ቢደረግ፣ መምህራን ከቢሮ ሠራተኞች እኩል ክፍያ ቢከፈላቸው፤ ሀገረ ስብከቱ ከክፍለ ከተማ አድባራትና ገዳማት በጋራ እየተናበቡ በቅንጀት ቢሠሩ የሚሉትና የመሳሰሉትን የመፍትሔ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡

በመጨረሻም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ መመሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡ ከመመሪያዎቹ መካከል ክፍለ ከተሞች ለአድባራትና ገዳማት ስለ ሽግሽግ፣ አዲስ ቅጥርን በተመለከተ ጥብቅ የሆነ መመሪያ በደብዳቤ እንዲሰጡ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *