በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስለ ተሰበሰበው የሰው ኃይልና የንብረት ሀብት መረጃ አስመልክቶ ገለጻ ተደረገ

በሀገረ ስብከቱ ስለ ተሰበሰበው የሰውና የንብረት ሀብት አስተዳደር ሲስተም፣ የመዝገብ ቤት ፋይል አስተዳደር ሲስተም እና የእስቶክ አስተዳደር ሲስተም አስመልክቶ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ ተደርጓል::
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ፥ የሀገረ ስብከቱ የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ተገኝተዋል።
መረጃው ከአይቲና ዶክመንቴሽን፣ ከሚድያና ከሰው ኃይል ክፍል በተዋቀረ ኮሚቴ የተሰበሰበ ሲሆን ከመረጃው አሰባሳቢና ኮሚቴ አንዱ የሆኑት የሀ/ስብከቱ የሚድያ ክፍሉ ባልደረባ መ/ርሽፈራው እንደሻው ስለ ተሰበሰበው መረጃ ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርበዋል።
መምህሩ በማብራሪያቸው የመረጃውን ዓላማና ለሀገረ ስብከቱ ብሎም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያለው የጎላ ጠቀሜታ አብራርተዋል። መረጃው የሰው ኃይልና የንብረት ሀብት በተገቢ ሁኔታ ለማወቅ፣ ዘመናዊ አሰራርን ለመዘርጋት፣ ሁለገብ መረጃ በተፈለገ ሰዓት በፍጥነት ለማግኘት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለማስፈን፣ ፈጣን የሥራ እንቅስቃሴ እንዲኖርና ቤተ ክርስቲያኒቱ በአግባቡና በጥበብ ለማስተዳደር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የተሰበሰበው መረጃ ውጤታማ ቢሆንም በዚሁ ልክ መረጃው በሚሰበስቡበት ጊዜ ያጋጠሙዋቸው ችግሮች እንደነበሩ በማውሳት፣ ችግሩን ይቀርፋል ብለው ያስቀመጡዋቸውን የመፍትሔ አቅጣቻዎችን አብራርተዋል።
በመጨረሻም መረጃው በሰዓቱ ያሰገቡትን አመስግነው ላላስገቡት ደግሞ በፍጥነት እንዲያስገቡ አሳስበዋል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማም የተሰበሰበውም ሆነ የሚሰበሰበው መረጃ ለቤተ ክርስቲያን ያለው ጠቀሜታ የላቀ ስለ ሆነ ትኩረት ይሰጥበት ብለዋል። በዚሁ አያይዘውም አድባራቱና ገዳማቱ ፐርሰንቱ በአግባቡና በሰዓቱ እንዲያስገቡ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መረጃውን ለሰበሰቡትና ገለጻውን ላደረጉ መ/ር አመስግነዋል፤ በመቀጠልም ከእንግዲህ ወዲህ ዶክመንቱ አይጥ በላው ወይም ጠፋ የሚለውን ምክንያት እንደማይሠራ ገልጸዋል።
መረጃው ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ የሚጠቀም ነው፤ በአንድ አጥቢያ ምን ያህሉ አገልጋዮችና ተገልጋዮች፣ ሙያቸውና የትምህርት ደረጃቸውን በማወቅ ቤተ ክርስቲያኑን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚረዳ ሲሆን፣ ንብረቱ በተመለከተም የቤተ ክርስቲያን ንብረትና ቅርስ በአግባቡ ለመጠበቅ በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
ብፁዕነታቸው መረጃው ጊዜውን ዋጅተን ከዓለሙ ተወዳድረን ዘመኑን በሚፈቅደው መልኩ ቴክኖሎጂን ተጠቅመን ለመጓዝ የሚያስችለን አሠራር መሆኑን ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜናም ስለ ‹መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክስዮን ማኅበር› ገለጻ ቀርቧል፡፡ ‹መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክስዮን ማኅበር› በ102 አባላት የተመሠረተ ሆኖ ቤተ ክርስቲያናችን የራስዋን ሆስፒታል በማቋቋም ተከታዮችዋ በራስዋ ሆስፒታል ልታክም ይገባል በሚል መልካም ሓሳብ አክስዮን እየሸጠ የሚገኝ የጤና አገልግሎት ማኅበር መሆኑን በዶ/ር ዲ/ን ናትናኤል ተገልጸዋል።
ዶክተሩ የማኅበሩ ዓላማ በሀገራችን ጥራት ያለው ሕክምና፣ በርከት ያለ ገቢና የሥራ ዕድል እንደሚሰጥ አብራርተዋል። ይህ ታሳቢ በማድረግም ሁሉ አክስዮኑን በመግዛት ወደ ማኅበሩ እንዲቀላቀል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅም ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያንን በብዙ ዘርፍ የሚጠቅም ነው፤ እኛ ራሳችን በራሳችን ብንታከም መልካም ነውና ማኅበሩን ማበረታታት ይገባናል ብለዋል።

ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *