በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን 37ኛው የሰበካ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ተጀመረ

                                                                                  በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጉባኤው የተጀመረ ሲሆን ስብሰባው በጸሎት ወንጌል ተከፍቷል፡፡
“ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ምክር ሰናይት ለኲሉ ዘይገብራ ውስብሓትሁኒ ይነብር ለዓለም” የሚለው የዳዊት መዝሙር ልብሰ ተከክህኖ በለበሱ ዲያቆናት በዜማ ቀርቧል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ቀዳማዊ ፣ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ የተገኙ ሲሆን በመርሐ ግብሩ መሠረት
በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 18 ቁጥር 18 ላይ የተፃፈው “በስሜ አንድም ሁለት ሆናችሁ ብትሰበሰቡ እኔ በመካከላችሁ እገኛለሁ” የሚለው ቃል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፣ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በንባብ ተነቧል፡፡ፓትርያርኩ ባስተላለፉት መልክትም ቤተክርስቲያኑቱ በሰላም በፍቅርና በሀገር ግንባታ የበኩሏን እየተወጣች እንደሆነ ገልጸዋል።
በመቀጠልም ሰላም ለክሙ ኦ ማኅበራኒሁ ለክርስቶስ እለተገባዕክሙ ውስተ ዛቲ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት፣ ቀሳውስት ወዲያቆናት ወማኅበረ ምዕመናን የሚል ያሬዲዊ ወረብ በማህደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተዘምሯል፡፡
ከዚህ በኋላ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተክህነተ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በክልል ትግራይ የደቡባዊ ማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጠቅላላ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ብፁዕነታቸው በታላቁ ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት “ዮም በዛቲ ዕለት አስተጋብአነ በመንፈስ ቅዱስ ከመንንግር ሠናይቶ ወከመንዘከር አበዊነ እንዘ ናረትዕ አእጋሪነ ውስተ ፍኖተ ሰላም” በሚል የመጽሐፍ ቃል ንግግራቸውን በመጀመር ባቀረቡት ሰፊ እና ጥልቅ ሪፖርት በዘንድሮው 37ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ልዩ የሚያደርገው ከሃያ ሰባት ዓመታት በኋላ በውጭ ሀገር የነበሩ ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደሀገራቸው ተመልሰው የቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነትና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሕደት በተፈጸመበት ማግስት የሚካሄድ በመሆኑ ነው፡፡


ይህ ብዙ የተደከመበት ታሪካዊ የቤተ ክርስቲያን አንድነትና የቅዱስ ሲኖዶስ ውህደት እውን እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስን ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮችን እና ቅዱስ ሲኖዶስን ወክለው በተሾሙ በጥቂት ወራት ውስጥ ታሪክ የማይረሳው የቤተክርስቲያናችን የአንድነት ባለውለታ በመሆን የበኩላቸውን ሃላፊነት የተወጡ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅድስት ቤተክርስቲያንና በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ስም አመስግነዋል፡፡በመቀጠልም ከቤቶችና ሕንፃዎች ይገኝ ከነበረው ገቢ ከሦስት እጥፍ በላይ ለማሳደግ መቻሉን፣ የጨረታ ሥርዓትን በመከተል በበጀት ዓመቱ ሁለት ባለ 10 ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃዎች በ1000 እና በ480 ካሬ ሜትር ስፋት ቦታዎች ላይ እየተገነቡ የሚገኙ መሆኑን፣ ለብፁዓን አባቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ 13 ዘመናዊ መኪኖች በጠቅላይ ቤተ ክህነት በጀት ተገዝተው በሥራ ላይ የዋሉ መሆናቸውን፣ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ ላይ 15 ኤጲስ ቆጶሳት በአንብሮተ ዕድ መሾማቸውን፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ 22 ሠራተኞችን በዕድገት፣ 34 ሠራተኞችን ደግሞ በዝውውር መድቦ ማሠራቱን ተሻሽሎ የታተመው ቃለ ዓዋዲ 50 ሺህ ኮፒ ለአህጉረ ስብከት መሠራጨቱን፤
የሰሜን ወሎ፣ ሲዳማ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ስላሌ የተደራጀና ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር በመከተላቸው በአርአያነት መጠቀሳቸውን፣አንዳንድ አህጉረ ስብከት የባንክ ገቢ ወጪ ሒሳብ በየወሩና በየዓመቱ የማይዙ መሆኑን፣ በሞዴል 64 ገቢ የተደረገ ገንዘብ ወደ ባንክ ገቢ ሳይደረግና ሳይወራረድ ወይም ሳይመለስ ለረጅም ዓመት በካዝና እየተንከባለለ መቆየቱን፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ያልፈቀደውና ያላጸደቀው የደመወዝ ጭማሪ መደረጉን፣የሕንፃ ግንባታ፣ የመኪና ግዢ ያለጨረታ መከናወኑ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚሰጡ የዕርምት እርምጃዎች አለመተግበራቸው፣በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በበጀት ዓመቱ ቃለ ዓዋዲን ጨምሮ 466,351 የተለያዩ የኅትመት ውጤቶች ታትመው በሥርጭት ላይ መዋላቸውን፣ በበጀት ዓመቱ ከወጪ ቀሪ 7,844,365.00 ካለፈው በጀት በንጽጽር 279,540 መመዝገቡ፣ በወቅቱ መፍትሔ መስጠት ባለመቻሉ በተለያየ አቅጣጫ የአስተዳደር ክፍተት፣ የሃብት ብክነት እየተከሠተ፣ ጽ/ቤቶች እየታሸጉ፣ አስተዳዳሪዎችና የጽ/ቤት ሠራተኞች እየተባረሩ፣ ሕዝቡም በአስተዳዳሪዎች እየተማረረ ፍትሕ ፍለጋ በአንዳንድ ቦታዎች ሰላማዊ ሰልፍ እየወጣ ሰብአዊ መብት ጸረ ሙስና ኮሚሽን እና በመሳሰሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አቤቱታ በመቅረቡ በሀገሪቱ ሚዲያዎች ሳይቀር እየተወቀስን የምንገኝ መሆኑን፣ ብፁዕነታቸው ባቀረቡት ሰፊ ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት የተጠቆመ ሲሆን ብፁዕነታቸው አክለው ለጉባኤው ባቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ፡-
ሀ/ በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም ዙሪያ ያለችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ሊያሳድግና አንድነቷንና ሃይማኖቷን ሊጠብቅ፣ ምእመኖቿን ሊያስደስትና መልካም አስተዳደርዋን ሊያጎለብት የሚችል ሰፊ መሪ ዕቅድ በአስቸኳይ እንዲዘጋጅ ቢደረግ፣


ለ/ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የፋይናንስ፣ የንብረትና የሰው ኃይል አስተዳደር ደምብ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንዲውል ቢደረግ፣
ሐ/ የቤተ ክርስቲያናችን ሕልውና መሠረት በሆኑት በአብነት ት/ቤቶች፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በገዳማት፣ በስብከተ ወንጌል፣ በሰንበት ት/ቤቶችና በውጭ ግንኙነት ሥራዎች መሠረታዊ የሆነ ለውጥና ተጨባጭ ውጤት የሚያመጡ የአሠራር ፖሊሲዎችና ደምቦች እንዲዘጋጁና ወደ ሥራ እንዲገባ ቢደረግ፣
መ/ በመላ ሀገሪቱና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመሬት ይዞታዎች በአግባቡ ለምተው ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ይውሉ ዘንድ አንድ ገዢ እና ወጥ የሆነ የልማት ፖሊሲ ወጥቶ ወደ ሥራ ቢገባ፣
ሠ/ ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ዙሪያ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ያሏት ሲሆን በነበረው የአባቶች መለያየት ምክንያት የውጭ፣ የግል እና የሀገር ውስጥ ወዘተ በሚል ጎራ ተለያይተው መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
ረ/ አሁን ግን ምስጋና ለእግዚአብሔር ይድረሰውና ሁላችንም ወደ አንድነት ስለመጣን በውጭ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስና በእናት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር ሆነው የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲጠናከር እንደየሀገራቱ ሕጎችና ደንቦች ሊያሠራ የሚችል መተዳደሪያ ደንብና መመሪያ ወጥቶ፣ የተልዕኮተ ሐዋርያት ማስፈጸሚያ ተቋም ተደራጅቶ ዓለም አቀፍ ሥራዎች እንዲያከናውኑ ቢደረግ፣
ሰ/ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ገዳማት፣ አድባራት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋይ ካህናት፤ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምእመናን እንዳሏት ይታወቃል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሁሉ የንዋየ ቅድሳት አቅርቦት የሚያገኙት ከግል ነጋዴዎችና ከእምነቱ ተቃራኒዎች ነው፤ ይህንን ሁኔታ ከመሠረቱ ለማስተካከልና ቤተ ክርስቲያናችንን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ልዩ ልዩ የንዋየ ቅድሳት ማምረቻ ማእከላት ተቋቁመው ሥራ የሚጀመርበት ጥናት ቢካሄድ፣ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ አሠራር ለውጥ በወሳኝ መልኩ ማምጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህንን ለውጥ ማምጣት ሳንችል ቀርተን ባለው የድንግዝግዝ አሠራር የምንቀጥል ከሆነ አደጋው ለቤተ ክርስቲያናችን የከፋ ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት ያለብን አይሆንም፡፡


በመሆኑም “ወእመሰ ኰነነ ለሊነ ርእሰነ እምኢተኰነነ ምስለ ዓለም” እንዳለው ቅዱስ ጳውሎስ እኛው ራሳችን የቤት ሥራችንን ሠርተን ማስተካከል ስንችል፣ በአንጻሩ ሳንችል ከቀረን በእግዚአብሔርም፣ በታሪክም፣ በሰውም ወቀሳው ከባድ ይሆናል፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው አሁን ያለንበት ወቅት የለውጥ ወቅት ነውና “ጎረቤት ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ” የተባለውን ብሂል ወስደን ከዛሬ ጀምሮ በቀጥታ ወደ ፈጣን የአሠራር ለውጥ ብንገባ ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ራሳችንን ማዳን የምንችልበት ዕድል ሰፊ ነው በማለት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርታቸውን በማቅረብ ከሰዓት በፊት የነበረው የስብሰባ መርሃ ግብር በጸሎት ተዘግቷል፡፡

1 reply
  1. መ/ ጌታቸው ወልደሐና
    መ/ ጌታቸው ወልደሐና says:

    በቅድሚያ ልዑል እግዚአብሔር የተለያዩትን አባቶች አንድ አድርጎ ስላሳየን እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁ።
    በመቀጠልም እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ይባርክ። ከጉባኤው መልካሙን ለመስማት ያብቃን።

    Reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *