በዓለ ሆሣዕና

ከላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ)
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ታላለቅ በዓላት አንዱ የሆሣዕና በዓል ነው፡፡ ስለዚህ በዓል አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፤ ከትንቢቶቹም አንዱ እንደሚከተለው ተጠቅሷል፡፡ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያና በአህያይቱ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” (ትን. ዘካ. 9÷9)፡፡

በዚህም መሠረትነት ስለበዓሉ አራቱም ወንጌላውያን ጽፈዋል፡፡ ይህም፡- ማቴ. 21÷1-11፣ ማር. 11÷1-10፣ ሉቃ. 19÷28-40፣ ዮሐ. 12÷12-15 አራቱም ወንጌላውያን የጻፉት የበዓሉ ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፡፡ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ገና ማንም ያልተቀመጠባት አህያ ከውርንጫይቱ ጋር ታስረው ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማንም ስለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ አላቸው፡፡ የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፡፡ እነርሱም አህያዋንና ውርንጫዋን ሲፈቱ የአህያው ባለቤት አህዮቹን ስለምን ትፈቷቸዋላችሁ? አላቸው እነርሱም ለጌታ ያስፈልጉታል አሉ ወዲያው አመጡለት፡፡ የታሠሩትን ፈትታችሁ አምጡልኝ ማለቱ ሰው ሁሉ ከኃጢአት ማሠሪያ የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ ነው፤ ደቀ መዛሙርቱም ልብሳቸውን በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ጎዘጎዙ የዚህም ምስጢር ኮርቻ ይቆረቊራል ልብስ አይቆረቊርም የማትቆረቊር ሕግ ሠራህልን ሲሉ፤ አንድም ልብስ በአካል ያለውን ነውር ይሸፍናል አንተም ከባቴ አበሳ (በደልን የምትሸፍን) ነህ ሲሉ ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአህያዋና በውርንጭዋ ላይ በጥበብ በአንድ ጊዜ ተቀምጦባቸዋል ለእርሱ የሚሳነው ነገር የለምና፡፡ በአህያ የተቀመጠበት ምክንያት ደግሞ ቀድሞ ነቢያት ዘመነ ጸብዕ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው ይታያሉ፡፡ ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉና ዘመነ ሰላም ደረሰ ሲል ትንቢቱን ባወቀ አናግሯል ምስጢሩም በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም እሱም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝ አልታጣም ሲል ነው፡፡ ሲሄድም ሕዝቡ ልብሳቸውን በመንገድ አነጠፉ፡፡ እንኳንስ አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ነው፡፡ እንዲሁም ሕዝቡ ሕፃናቱ ሳይቀሩ ዘንባባ ይዘው የሚቀድሙትም የሚከተሉትም ሕዝብ “ሆሣዕና ለወልደዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር” (ለዳዊት ልጅ መድኃኒትን መባል ይገባዋል፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው) ሆሣዕና በአርያም እያሉ ያመሰግኑ ነበር፡፡ ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው፡፡ የዘንባባው ምስጢርም፡- አብርሃም ይስሐቅን ይስሐቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፣ እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፣ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ ዘንባባ ይዘው እግዚአብሔርን አመስግነዋልና በዚህ መሠረት ሕዝቡ፡- የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲሄድ ዘንባባ ይዘው አመስግነውታል፡፡ እንዲሁም ዘንባባ እሾኻም ነው ትምህርተ ኃይል፣ ትእምርተ መዊዕ አለህ ሲሉ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሲያመሰግኑ ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ መምህር ሆይ፡- ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ መልሶም እላችኋለሁ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግናሉ አላቸው፤ ድንጋዮች ሳይቀሩ ያመሰገኑበት ዕለት ነው፡፡

በዚህ መሠረት ይህ በዓል የምስጋና በዓል ነው፡፡ እኛም ፈጣሪያችንን ሁልጊዜ ማመስገን አለብን የተፈጠርነውም ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ነው፡፡ ስሙን ለመቀደስ ማለት ስሙን ለማመስገን ማለት ነው ክብሩን ለመውረስ ማለት ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ማለት ነው፡፡ የተፈጠርነው ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ስለሆነ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል፡፡ ምስጋናውም በፍጹም እምነት፣ በቅንነትና በንጹሕ ልብ መሆን አለበት፡፡ “እባርኮ ለእግዚአብሔር በኵሉ ጊዜ ወዘልፈ ስብሐቲሁ ውስተ አፋየ” (እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ ምስጋናውም ዘወትር በአፌ ነው) (መዝ. 33÷1)አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመስግነን መንግሥቱን ለመውረስ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም ቅዱሳን በአማላጅነታቸው ይርዱን፡፡

ለበዓለ ሆሣዕና ያደረሰን አምላክ ለብርሃነ ትንሣኤውም በሰላም ያድርሰን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *