“በዓሉን ስናከብር በጦርነት እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን በማሰብ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን ልናረጋግጥ ይገባል”… ብፁዕ አቡነ ሄኖክ

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ጠባቂ የ2015 ዓ.ም በዓለ ልደትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

የመልእክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል።

“ዮም በርህ ሠረቀ ለነ ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ ማኅፀነ ድንግል ፆሮ “(ዛሬ ብርሃን ወጣልን ፤ ሰማይ እና ምድር መሸከም የማይችሉትን የድንግል ማኅፀን ተሸከመው
“(ቅዱስ ያሬድ)

በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ምዕመናንና ምዕመናት

ደካማ ባሕርያችንን ተዋሕዶ ሰው የሆነ፤በሥራው ጌትነቱን የገለጠ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ፳፻፲፭ ዓ.ም በዓለ ልደቱ በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ።

የሰው ልጅ ከአምላኩ የተሰጠውን ትዕዛዝ በመተላለፍና ፍፁም ታዛዥነትን ወደ ጎን በመተው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ በሆነ መልኩ የገባበትን ስህተት ተከትሎ በሰው ፍጥረት ሁሉ ላይ የመጣው ሞት በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን የሞት ማሰሪያው ተቆርጦ ጠፋ የሰው ልጅም በክርስቶስ ኢየሱስ መወለድ ነጻ ሆኖ በላዩ ተጭኖበት የኖረው የዲያብሎስ ቀንበር ጠፍቷል ፤ ተደምስሷል።

መድኅነ ዓለም ክርስቶስ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል እንደተባለ የሰው ልጅ በኃጢአቱ ምክንያት ተሰነካከለ ፣ ትዕዛዙን ባለመስማት ከገነት ተሰደደ ፤ ነገር ግን ሰውን የሚወድ ደረሰልን (ሃ.አበው) ።

ሰውን ሰው ማዳን ስለተሳነው በመልአክ ወይም በነቢይ ሳይሆን ፤ እርሱ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ አድኖናል።

የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው ፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው።(፩ ቆሮ.፲፭ ፥፵፯) እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ በአዳም ምክንያት የመጣብን ሞት በሁለተኛው አዳም ተደምስሶ ነጻ ወጥተናል ይኸውም ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ ከመሬት መሬታዊ ሳይሆን ከሰማይ በመሆኑ ነው።

የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች ምዕመናን እና ምዕመናት

የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን እጅግ የሚደንቅ ልዩ ምስጢር ነው።

የማይታመም እርሱ ከመለኮቱ ሳይለይ የሚታመም ሥጋን ተዋሕዷል።

ዳግመኛም በሉዓላዊ ዙፋን የሚኖር ታላቁ እና ገናናው አምላክ በጎል ተጣለ ፤ ሥጋን ከመዋሐዱ አስቀድሞ የማይዳሰስ ወልድ ዋሕድ እርሱ ዛሬ ሥጋን ተዋሕዶ ተዳሠሠ።

እጅግ በሚያስደንቅ መልኩ የኃጢአትን ቁራኝነት የሚያጠፋ እርሱ በጨርቅ ተጠቀለለ !

በመሆኑም እነዚህን እና የማይመረመሩ የእርሱን ሥራዎች በመመልከት ከፍለን የማንጨርሰው ውለታ ያለብን በመሆኑ ምስጋና እና አምልኮን ልናቀርብለት ይገባል።

በዚህም ስሙ ድንቅ መካር ፥ ኃያል አምላክ፥የዘላለም አባት ፥የሰላም አለቃ የተባለ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ እና ሕይወትን የሚሰጥ አምላክ መሆኑን ልንረዳ ያስፈልጋል።

የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች ምዕመናን እና ምዕመናት

ቅዱስ መጽሐፍ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም አለቃ መሆኑን ይነግረናል በመሆኑም እኛም ክርስቶሳውያን ስለሆን በሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እና በጦርነት እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን በማሰብ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን ልናረጋግጥ ይገባል።

በመጨረሻምይህንን የጌታችን እና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በምናከብርበት ጊዜ የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣በጦርነት ቀጠና ውስጥ የቆዩ ወገኖቻችንን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን

አባ ሄኖክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ጠባቂ

ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ