በጉራጌ ሀገረ ስብከት በእዣ ወረዳ የሚገኘው የመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል እና አባ ሳሙኤል ገዳም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ

በጉራጌ ሀገረ ስብከት እዥ ወረዳ በገጨ ቀበሌ የሚገኘው የመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል እና አባ ሳሙኤል ገዳም በብፁዓን አባቶች ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ተመርቆ በዛሬው ዕለት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፡፡
በአንድ ኦርቶዶክሳዊ ባለሀብት መሬት ሰጭነት የተመሠረተው አዲሱ ገዳም የመሠረት ድንጋዩ ከተጣለ ከ6 ወራት በኋላ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱ በቀረበው ሪፖርት ተገልጿል፡፡
በአካባቢው ምእመናን እና በአንድ ባለሀብት የጋራ ትብብር በከፍተኛ ፍጥነት ተሠርቶ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው ይህ ገዳም በወረዳው ከሚገኙ ገጨ ኪዳነ ምህረት፡አትርፎ ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ ለሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ አገልግሎት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ አብራርተዋል፡፡
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ወቅቱን የተመለከተ ሰፊ ትምህርተ ወንጌል በብፁዕ አቡነ እንጦንስ ተሰጥቷል፡፡
በዕለቱ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ቅዳሴ
ቀድሰው ለምእመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን አቀብለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት የመድረክ ትምህርትም በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ አንድ ገዳም ሠርቶ መጨረስ ቆራጥነትን የሚጠይቅ ተግባር ነውና በዚህ መልካም ተግባር የተሳተፋችሁ ሁሉ ምሥጋና ይገባችኀል ብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የምሥራቅ ሽዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፡የምዕራብ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፡የአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ሕይወት አባ ወ/ኢየሱስ ሰይፉ፡የጉራጌ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ ሠራተኞች እንዲሁም በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ:-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
የመረጃው ምንጭና ፎቶ፡- መልአከ ሕይወት አባ ወልደኢየሱስ ሰይፈ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *