“ቤተክርስቲያናችን ከውስጥም ከውጭም እየተፈተነች ለመሆኗ ከሜዳው ተነሥቶ ፓትርያርክ ነኝ፣  ጳጳስ ነኝ  የሚለው መብዛቱ ትልቅ ማሳያ ነው”….ብፁዕ ወቅዱስ  አቡነ ማትያስ

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት  በዓለ ሢመታቸው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትእና በርካታ የመንግሥት ባለ ስልጣናት: አምባሳደሮች  የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት ተከብሯል።

ለበዓለ ሢመቱ የተዘጋጁ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ  ካቴድራል መምህራን ወረብ እና ቅኔ አቅርበዋል። የካቴድራሉ ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በተዋበ ክርሲቲያናዊ አለባበስ ደምቀው ዝማሬ አቅርበዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ በዓለ ሢመቱን አስመልክቶ መልእክት እንዲያሰተላልፉ  ተጋብዘው ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ በሚል መነሻ ቃል አባታዊ ምክር እና ሰፊ ትምህርት አስተላልፈዋል።

እኛ አባቶች እንድንደመጥ  ከፈለግን የሃይማኖት ቁመና ሊኖረን ይገባል መሀል ላይ ቁመን የምንጮህ መሆንም አለብን  ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ 500, 000 (አምስት መቶ ሽህ) ካህናት ባሏት ሀገር ሰላም ከሌለ ቆም ብለን በአባታዊ ማዕረግ ማሰብ ይገባናል ብለዋል።

ሰላምን ማስቀደም የህላዌ ዋስትና መሆኑን በመረዳት  ሰላም ከሌለም አዲስ ነገር መፍጠር ይቅርና ያለውን ማስቀጠል እንደማይቻል በማሰብ እኛ ብፁዓን ተብለን  የምንጠራ አባቶች እያንዳንዷ ንግግራችን በቃለ ወንጌል የተቃኝ እንዲሆን በሚል በአደራ ጭምር መልክት አስተላልፈዋል።

ቤተክርስቲያን በውስጥም በውጭም እየተፈተነች መሆኗን ለመረዳት ከሜዳ ተነስተው ፓትርያርክ ነኝ ጳጳስ ነኝ የሚሉ መብዛት ትልቅ ማሣያ መሆኑን አወቀን  ችግሩን  የምንፈታውም በማውገዝ ብቻ ሣይሆን ቁጭ ብሎ በመነጋገር እና ጊዜ በመስጠት ነው ብለዋል።

በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ መሪነት፣ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተራዳኢነት፣ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት እና ካህናት እንዲሁም መነኮሳት አስተባባሪነት ሥርዐተ ቅዳሴው ተከናውኖ በዓለ ሢመቱ እንደሚጠናቀቅ ከወጣው መርሐ ግብር ለመረዳት ችለናል።

     በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ

         ፎቶ በዋሲሁን ተሾመ

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ:-
1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et

2. ፌስ ቡክ ገጽ:- አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት/Addis Ababa Diocese

3. ቴሌግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese

4. ትዊተር :-www.Twitter.com/AddisDiocese

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published.