ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለ32 የአብነት ተማሪዎች  የዲቁና እና የቅስና ማዕርገ ክህነት ሰጡ!!

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሲኤምሲ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተገኝተው ለ31 የአብነት ተማሪዎች የዲቁና፣ ለአንድ ዲያቆን የክህነት ማዕርገ ሥልጣን ሰጥተዋል።

መጋቢት 09 ቀን 2014 ዓ/ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መልካም ፈቃድ በመ/ምሕረት በቃሉ ወርቅነህ የሀገረ ስብከቱ የትምህርትና የሥልጠና ዋና ክፍል ኃላፊ አስተባባሪነትና ፈታኝነት ከደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በደብሩ የድጓ መ/ር ዜናዊ  መለመዱ የተማሩ 39 ተማሪዎች፣ ከደብረ በረከት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ጠበብት ኤፍሬም ዳኘው የተማሩ፣ በሊቀ ትጉኃን አፈወርቅ መብራቴ የደብሩ ዋና ቁጥጥር አስተባባሪነት 34 ተማሪዎች በድምሩ 73 ተማሪዎች ተመዝግበው መቅረባቸው ታውቋል።

ከ73ቱ ተማሪዎች 47ቱ መመዘኛውን አሟልተው ለፈተና የቀረቡ ሲሆኑ 18 ከደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ 12 ከደብረ በረከትና 2 ከሌሎች ፈተናውን አልፈው በዛሬዎ ዕለት የዲቁና ማዕርግና የቅስና ሥልጣነ ክህነትን ተቀብለዋል።

በጸሎቱ ሥነ ሥርዓት የሐዋርያው የቅዱስ መልእክት ወደ ጢሞቴዎስ የተላከ 1ጢሞ. ምዕራፍ 3 እና የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ  21 ከቁጥር 15 ጀምሮ ተነቧል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ዲቁናና ቅስና ለተቀበሉት ተማሪዎች ከምእመናን ወደ ዲቁና  ከዲቁና ወደ ቅስና በመሸጋገራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የክህነት ጥሪው ከእግዚአብሔር ነው ያሉት ብፁዕነታቸዎ  ከእንግዲህ ወዲህ በመጽሐፉ የተነበበውን በመተግበር የምእመናን አገልጋዮች ናችሁ፣ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ገብታችኋልና በታማኝነት ማገልገል አለባችሁ ብለዋል።

በደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት የሐዲሳት፣ የቅዳሴና የጸዋትወ ዜማ በደብሩ ቋሚ መደበኛ መምህራን የሚሰጥ መሆኑን ተገልጿል።

በተያያዘም ደብሩ በተለየ መልኩ ለወንጌል አገልግሎት ትኩረት በመስጠት በየሳምንቱ ማክሰኞ ልዩ ጉባኤ ለሕዝብ የሚሰጥ ሲሆን  ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ በፆሙ ምክንያት የአንድነት ጉባኤ ዐውደ ወንጌል ዘተዋሕዶ ከመጋቢት 11 ጀምሮ እስከ መጋቢት 14/2014 ዓ/ም ስለ እግዚአብሔር አዳኝነት፣ ስለ ንስሐ፣ የፆሙ ጥቅምና በጎ ምግባርን ያካተተ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን የደብሩ ዋና ፀሐፊ መ/ር ዕዝራ ንዋይ ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ መጨረሻም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በደብሩ ተሠርቶ በማጠናቀቅ ላይ ያለውን ግዙፍ ዓለም ዓቀፍ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እና በደብሩ እየተሠሩ ያሉትን ልዩ ልዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ በፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርትና ሥልጠና ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ምህረት በቃሉ ወርቅነህ፣ የየካ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አሰኪያጅ መ/ምሕረት ዘካርያስ አዲስ፣ የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ መ/ሃይማኖት ጥዑመ ልሣን አዳነ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።

       በመ/ር ኪደ ዜናዊ
       በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ (ፎቶ)

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published.