ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በርእሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተጠናቀቁ ሦስት ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር በምትገኘው ርእሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በበጀተ ዓመቱ በደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት፡ በበጎ አድራጊ ኦርቶዶክሳውያንና በማኅበረ ካህናቱ የጋራ ትብብር የተጠናቀቁ ሦስት ፕሮጀክቶች በአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ተመርቀዋል፡፡
ከሦስቱ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውና በደብሩ ካህናት የአንድ ወር ደመወዝ ስጦታ የታደሰው የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት በብፁዕነታቸው ተመርቆ ለድጋሚ አገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡
ባለ ሳር ክዳኑ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የንጉሡን እልፍኝ ጨምሮ የእንግዳ መቀበያና ማረፊያ እንዲሁም የንጉሥ የግብር ማብያን ያካተተ እና 138 ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ቤተ መንግሥት መሆኑም ተገልጿል፡፡
ይህ ጥንታዊ ቤተመንግሥት ለበርካታ ዓመታት ዕድሳትና ጥገና ስላልተደረገለት ታሪካዊ ማንነቱን ከማጣቱ በፊት ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና ለአዲስ አበባ ባህል፡ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብ መልስ ባለመገኘቱ በደብሩ ሰባካ ጉባኤና በማኅበረ ካህናቱ የጋራ ትብብር ከሰባት መቶ ሽህ ብር በላይ በሆነ ወጭ ዕድሳት እንደተደረገለት በደብሩ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ጥበብ ምሥጋናው አዳሙ የቀረበው ሪፖርት ያመላክታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በ1870 ዓ.ም በዳግማዊ አፄ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ ብጡል መቃኞ ቤተ ክርስቲያኑ ተመሠርቶ በ1879 ዓ.ም ዋናው ቤተክርስቲያን እንደተሠራ የሚነገርለትን ደብር ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የመብራት፡ የቀለምና የምንጣፍ የውስጥ ዕድሳት በበጎ አድራጊ ኦርቶዶክሳውያን መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ጥንታዊው መንበርም ራሱን የቻለ ቤት በቅጥር ግቢው ውስጥ ተሠርቶለት በቅርስነት በክብር ተቀምጦ እንዳለ በጉብኝቱ ወቅት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ኪዳነ ማርያም ዮሴፍ በምጣኔ ሀብት ራስን የመቻልና የመለወጫ ምስጢሩ ልማት መሆኑን
ተገንዝበንና በጋራ ለማልማት ወስነን በደብሩ ስም ከሚተዳደረው 90 ሽህ ካሬ ቦታ ለልዩ ልዩ አገልግሎትና ለመኖሪያ ቤት የሚውሉ 11 ክፍል ቤቶች በ8 ወራት ውስጥ ሠርተን ለኪራይ ዝግጁ አድርገናል ይህም በዚህ ዓመት ካሳካናቸው ፕሮጀክቶች ሦስተኛው ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም በዚህ መንፈሳዊ ተግባር ውስጥ ባለመሰልቸትና ባለመድከም በገንዘብ፡ በሐሳብ፡በጸሎትና በልዩ ልዩ ሙያ አስተዋጾኦ የታሪክ አሻራቸውን ያኖሩትንና የደከሙትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
ያየነው ነገር እጅግ አስደናቂና አስደሳች ነው፡ንጹሐ ባሕርይ ለሆነው እግዚአብሔር ንጹሕ የማምለኪያ ሥፍራ ያስፈልገዋል ብላችሁ በዘመን ብዛት ያረጀውን ቤተ መቅደስ ያደሳችሁና የታሪክ ማማችን የሆነውን ቤተ መንግሥት ጥንተ ክብሩ የጠበቃችሁ ሁሉ ምሥጋና ይገባችኀል ያሉት ደግሞ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ናቸው፡፡
የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ተግባራዊ ሥራ በቃል ከመናገር በላይ መሆኑን ገልጸው ወደፊትም በዚሁ ሂደት እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ፡ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ኪዳነ ማርያም ዮሴፍ፡ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በርካታ ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናን ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ:- መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡- በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *