ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ቤ/ክ ዓመታዊው የቅዱስ አማኑኤል ክብረ በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል

በዛሬው ዕለት ታኅሣሥ 28 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ፣ የአዲስ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ሃይማኖት ጸጋዬ ገ/ዮሐንስ፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መ/ገነት ቀሲስ በቀለ ዘውዴ፣ የካቴድራሉ ጸሐፊ መ/ሥርዓት እጓለ፣ የካቴድራሉ ካህናትና ዲያቆናት፣የካቴድራሉ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ዓመታዊው የቅዱስ አማኑኤል ክብረ በዓል በያሬዳዊ ዝማሬና በሥርዓተ ቅዳሴ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
ብፁዕነታቸው በካቴድራሉ በማለዳ በመገኘት በካቴድራሉ እየተሠሩ ያሉትን መሠረተ ልማቶች ጎብኝተዋል፤ አሠራሮችንም አድንቀዋል፤የካቲድራሉን አስተዳዳሪ መ/ገነት ቀሲስ በቀለ ዘውዴን የሥራ አመራር አመሥግነዋል፤ካቴድራሉ ሊያሠራው ላሰበውም የትምህርት ቤት ሕንጻ መሠረተ ድንጋይ ጥለው ኪዳን አድርሰዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የካቴድራሉ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ቁጥራቸው 5000 መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም ካቴድራሉ ወጣቶችን በቃለ እግዚአብሔር በማሳደግ ዙሪያ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ያመለክታል፤በምልክት ቋንቋም ለእግዚአብሔር ምሥጋና አቅርበዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት የሰጡት መልአከ ታቦር ኃ/ኢየሱስ “ሰማይ መሬትን ሆነ መሬትም ሰማይን ሆነ” (ሃይማኖተ አበው 85፥37) በሚል ርዕስ ተነስተው በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ለሰዎች ቢገለጥም ዓለም አልዳነም። ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከው፤ ክርስቶስም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ለዓለም ሁሉ ተገለጠ፤ ከርስቶስ ተወልዶ ለእኛ በመሞቱ ለ5500 ዘመን በበደል እስራት ውስጥ የነበርን ወደ እግዚአብሔር ቀረብን፣ ዲያቢሎስ ተሻረ፣የዕዳ ደብደቤያችን ተቀደደ፣የገነት በር ተከፈተ፣መሬት ሰማይን ሆነ ሰማይም መሬትን ሆነ ብለዋል። መሬት ሰማይን ሆነ ማለት በሰማይ ብቻ ሲቀርብ የነበረው ምሥጋና በቤተልሔም በምድር ቀረበ፤በሰማይ ያለው ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስት ድንግል ማርያም እጅ ታቃፈ፤ እንዲሁም ሰማይ መሬትን ሆነ ሲባልም በምድር ላይ የሰማዩ ምሥጋና ስለ ቀረበ ነው በማለት አመሣጥረው አስተምረዋል።
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መ/ገነት ቀሲስ በቀለ ዘውዴ ለዚች ዕለት በምሕረቱና በቸርነቱ ያደረሰንን እግዚአብሔርን አመስግነው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤የብፁዕነታቸውን መመሪያ ተቀብለን እንፈጽማለን፤የተጀመሩትንም መሠረተ ልማቶች በአፋጣኝ ለፍጻሜ እናበቃለን ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ” መልአኩም እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” (ሉቃ 2፥10-11) ላይ ያለውን መለኮታዊ ቃል መነሻ በማድረግ ሰፋ ያለ ትምህርት አስተላልፈዋል።
በዓሉን ለማክበር በዓላማ እስከመጣን ድረስ የመጣንበትን በዓል ዓላማ፣ ይዘትና ታሪክ ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል ብለዋል። አዳምና ሔዋን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የጥል ግድግዳ ነበር ። ነገር ግን እግዚአብሔር በምህረቱ ባለጸጋ ስለሆነ ይህ የጥል ግድግዳ በእኛና በእርሱ መካከል እንዲኖር ፈጽሞ ፈቃዱ ባለመሆኑ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል ወልድ በሞቱ ይህንን የጥል ግድግዳ ሊያፈርስ፣ ቤዛ ሊሆንልን፣ወደ በፊቱ ክብራችን ሊመልሰን፣ሊያድነንና ከእኛ ጋር ሊሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ። በጌታችን ልደት ሰውና መላእክት፣ምድርና ሰማይ ተገናኝተዋል ብለዋል፤ በዓሉም የደስታ፣ የፍቅር፣የአንድነት፣የሰላም መሆኑን ገልጸዋል።ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሁላችንም ብሎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎና ሞቶ አድኖናል፣ የጥል ግድግዳን አፍርሷል፣ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት በትንሣኤው ሕያዋን አድርጎናል ፣ከኃጢአት ሁሉ የሚያድን ፍጹም መድኃኒት በመሆኑም ኢየሱስ ተብሎ ተጠርቷል። ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ሲሆን ዓለም ለ5500 ዘመን በመድኃኒት እጦት ሲማቅቅ ቆይቶ ጌታችን በመወለዱ ፍጹም ፈዋሽ መድኃኒት አግኝቷል፤ አምነው ለሚቀበሉት ሁሉ ፍጹም ፈዋሽ መድኃኒት መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው አስተምረዋል።
በመጨረሻም የጌታችንን በዓለ ልደት ስናከብር የደስታችን ምንጭ ሊሆን የሚገባዉ እርሱ ራሱ ክርስቶስ መሆን እንዳለበት፣ ደስታችንንም በምሥጋና በጸሎት መግለጽ እንዳለብን፣ መንፈሳዊ ይዘቱ ላይ ማተኮር እንዳለብን፣ ቤት ያፈራውን ለሌሎች እንድናካፍል፣ በችግር ውስጥ ያሉትን በመጠየቅ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል። በሌላ መልኩ ነፍሳችንንና ሥጋችንን ከሚያረክሱ ነገሮች ከመስከር፣ከልክ በላይ ከመመገብ፣ ከመጨፈር ራሳችንን በመቆጠብ ማክበር እንዳለብንም ገልጸዋል።በቤተክርስቲያን በመገኘት በማስቀደስ፣ ሥጋዉና ደሙን በመቀበል ካከበርን በኋላ ሌላውን ሁሉ በልክ በማድረግ ማክበር ይገባናል ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው ለሕዝበ ምእመናኑ ቡራኬና ቃለምዳን ሰጥተው ወደ ሥርዓተ ቅዳሴ ተገብቷል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *