ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጾመ ፍልሰታ መግቢያ አስመልክተው መመሪያዎችን አስተላለፉ

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጾመ ፍልሰታ መግቢያ አስመልክተው መመሪያዎችን አስተላለፉ።
ብፁዕነታቸው መመሪያዎችን ያስተላለፉት ለአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ቄሰ ገበዞች ነው።
“ለሁሉም ጊዜ አለው” የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል መነሻ በማድረግ ከ ነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 16 ቀን ወይም አስከ 21 ቀን የምንጾምበት ጊዜ ነው ብለዋል።
አያይዘውም ወደ ፈጣሪያችን አብዝተን የምንጸልይበት ፣ንስሐ የምንገባበት፣ የምንሰግድበትና የምናመሰግንበት የጾም ጊዜ ነው ሲሉ አውስተዋል።
ጾሙ ከእመቤታችንን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት የምናገኝበት ነው በማለት ገልጸዋል።
መዓልቱን በቅዳሴ ሌሊቱን በሰዓታት የምናሳልፍበት ወቅት መሆኑንም አውስተዋል።
በአድባራቱና በገዳማቱ ጾመ ፍልሰታን አስመልክቶ የሚደረጉ ሥርዓቶች ተመሳሳይ በሆነ መልኩ እንዲፈጸሙ አብራርተዋል።
ሰዓታት ፣ ኪዳን ፣ ስብሐተ ነግህ፣ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ ስብከተ ወንጌልና ቅዳሴ የሚገባበት ሰዓት በተዘረዘረው ቅደም ተከተልና በተመሳሳይ ሰዓት በአድባራቱና በገዳማቱ እንዲደርሱ መመሪያዎችን አስተላልፈዋል።
አያይዘውም የትምህርተ ወንጌል መርሐ ግብር ከሰኞ አስከ አርብ ባሉት ቀናት ከ5፡ዐዐ እስከ 5፡30 ባለው ጊዜ ውስጥ መነሻ ተደርጎ አስከ ቅዳሴ መግቢያ ሰዓት ድረስ እንዲሆን ገልጸዋል።
በተለይ በሁሉም አድባራትና ገዳማት የቅዳሴ ሰዓት መግቢያ 6፡15 መውጫ ደግሞ 9፡00 ሰዓት እንዲሆን ብፁዕነታቸው አጽንኦት ሰጥተው መልእክት አስተላልፈዋል።
በቅዳሜና እሁድ ቀናት ደግሞ የቅዳሴው ሥርዓት አስቀድሞ 11:00 ሰዓት መጀመር እንዳለበትም ጠቅሰዋል።
ከምንም በላይ ደግሞ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ምእመናኑን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ መንፈሳዊ አገልግሎት መፈጸም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ወቅቱ ሀገራችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸው ከምንጊዜውም በላይ ጾምን የምንጾምበት ወቅት ነው ብለዋል።
በዚህ የጾም ወቅት ብዙ ምእመናን ወደ ቤተክርስቲያን ስለሚመጡ ስብከተ ወንጌልን ጨምሮ እያንዳንዱ አገልግሎት ምእመኑን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲፈጸም አብራርተዋል።
መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ የሀገረ ስብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መርሐግብሩን መርተዋል።
የብፅነታቸውን ጥሪ አክብረው ለተገኙት ለክፍላተ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ ለአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ለቄሰ ገበዞች ምስጋና አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወ/ሐና ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጆችና የሥራ ኃላፊዎች፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎችና ቄሰ ገበዞች ተገኝተዋል።


ዘጋቢ፦ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ ፦መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published.