ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የዐብይ ጾም መግቢያን አስመልክተው አባታዊ መልእክት አስተላለፉ

ብፁዕነታቸው እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከደነገገቻቸው አጽዋማት መካከል አንዱ የዐቢይ ጾም ነው ፤ ዐቢይ የሚለው ቃል ትርጉሙ ትልቅ ማለት ሲሆን የጾሙን ታላቅነት ይገልጻል፤ ዐቢይ ጾም የተባለበት ምክንያት ጌታችን አምላካችን መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጾመውና ለተከታታይ ስምንት ሳምንታት ሳይቋረጥ የሚጾም ጾም በመሆኑ ነው፤ በእያንዳንዱ ሳምንት ውስጥ ያሉት እሑዶች የየራሳቸው የሆነ ስያሜ፣ ትርጉምና ልዩ ምሥጢር እንዳላቸው አብራርተዋል።

ጾም ማለት ከምግብና ከመጠጥ ለተወሰኑ ሰዓታት መቆጠብ ብቻ ሳይሆን አንደበትም ከሀሜት፣እጅም የሌላውን ከመውሰድ፣እግርም ወደ ክፉ ከመሄድ፣ኅሊናም መጥፎውን ከማሰብ፣ዐይንም የሚያሰናክሉ ነገሮችን ከማየት፣ጆሮም ምናምንቴ የሆነውን የዓለም ነገር ከመስማት ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 58 ላይ ስለ ጾም የተጠቀሰውን የእግዚአብሔርን ሃሳብ አንስተው እግዚአብሔር የማይፈልገውን ጾም ሳይሆን እግዚአብሔር የሚፈልገውን ጾም መጾም እንዳለብን አውስተዋል።

እግዚአብሔር የማይፈልገው ጾም በተጠቀሰው ምዕራፍ ላይ “እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፣ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ፣ እነሆ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ” ተብሎ መጠቀሱን አንስተዋል።

ከዚሁ ጋር አያይዘውም ስንጾም በቤታችን ውስጥ ያሉት ሠራተኞች ላይ የምንጮህና የምናሰቃይ ከሆነ፣ በድርጅታችን ውስጥ ያሉትን ሠራተኞች የሠሩበትን የጉልበታቸውን ዋጋ የምንነፍግ ከሆነ፣ለወንድማችን ጉድጓድ የምንምስ ከሆነ፣ ከቤተሰባችን ከጎረቤታችን ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር እየተጣላን የምንጾም ከሆነ እንዲህ አይነቱን ጾም እግዚአብሔር እንደማይፈልገው ገልጸው ይልቁንም እነኚህን ነገሮች በማስተካከል ትክክለኛውንና እግዚአብሔር የሚፈልገውን ጾም ልንጾም እንደሚገባ አብራርተዋል።

አክለውም እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም በዚሁ ምዕራፍ ላይ “የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? ” ተብሎ መጠቀሱን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በተሰጠን ጸጋ ሌሎችን በማገዝና በመርዳት፣የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጨነቁትን በመምከር፣የታሰሩትን በመጠየቅ፣ስለ ሀገራችን ፣ስለ ዓለም በመጸለይ ልንጾም ይገባል ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ