ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የገና 2005ዓ.ም በዓለ ልደት ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

                                                                                                      በመ/ር ዘሩ እና ኃይሉ

abune_nathnael

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ ፣ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ ፣ በሕማም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት እንኳን ለ2005 ዓ.ም የጌታችን፣ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዐለ ልደት በሰላም አደረሳችኹ፡፡ ‹‹ወበዝንቱ ተዐውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነዎ ውስተ ዓለም ከመ ንሕየው ቦቱ፤ በእርሱ ቤዛነት እንድን ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮአልና፣ እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ፍቅር በዚህ ዐውቀናል፡፡›› /1ዮሐ.4÷9/

እግዚአብሔር ከፍጡራን ሁሉ የተለየና ከአእምሮ በላይ የኾነ መለኰታዊ ኀይል ያለው አምላክ በመኾኑ የባሕርዩን ጥልቅነት በምልአተ ማወቅ ፈጽሞ የማይቻል ቢኾንም እርሱ ራሱ በገለጸልን መጠን የተወሰኑ ነገሮችን እናውቃለን፡፡

እግዚአብሔር ለፍጡራን ያለው የፍቅር ባሕርይ እጅግ ጥልቅና የማይናወጥ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ በቤተ ልሔም የተወለደበት ቀን ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው›› ብሎ ምልአተ ፍቅሩን ካስረዳ በኋላ በማስረጃ ሲያብራራ ‹‹ቤዛ ኾኖ የሰውን ልጅ ያድን ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮአልና ፍቅሩን በዚህ ዐውቀናል›› ይላል፡፡እግዚአብሔር በልጁ መሥዋዕትነት ዓለምን ለማዳን ያደረገው ፍቅር ከሌላው ሁሉ የበለጠ በመኾኑ ልቆ ተነገረ እንጂ የእግዚአብሔር ፍቅር ከፍጡራን የተለየበት ጊዜ እንደሌለ ሁላችንም እናውቃለን፤ በስፋትም ልንገነዘብ ይገባል፡፡የእግዚአብሔር ፍቅር በዓለም ላይ በምልአተ ባይኖር ኖሮ ሰማይና ምድር እንደዚሁም በውስጣቸው የሚገኙ የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት በሙሉ ሕገ ተፈጥሯቸውንና ሥርዐተ ምሕዋራቸውን ጠብቀው መኖር ባልቻሉም ነበር፡፡ ሰዎችም ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ውሳጣዊና አፍዓዊ ምግብና ማግኘት ባልቻሉም ነበር፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ በመኾኑ ጥፋተኛውንና እውነተኛውን ሳይለይ ፍጡራንን ሁሉ በፍቅር ይመግባል፤ ይመራል፤ ይቆጣጠራል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር ምን ያህል ሰፊና ምሉዕ እንደኾነ እንገነዘባለን፡፡ እግዚአብሔር አንዳችም ሳያጎድልበት ሰው በራሱ የተሳሳተ ምኞት ከእግዚአብሔር ፍቅር ቢለይም የሰው በደል በእግዚአብሔር ፍቅር ይሸነፋል እንጂ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በሰው በደል ሊሸነፍ ከቶ የማይቻል ነውና የእግዚአብሔር ፍቅር የሰውን በደል ሲያሸንፍ በፍቅረ እግዚአብሔር ተሰባስበው የተገናኙ ሰማያውያንና ምድራውያን ፍጥረታት በአንድነት ‹‹ለእግዚአብሔር በሰማያት ክብር ተደረገ፣ በምድርም ሰላም ኾነ፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ ተሰጠ›› እያሉ በቤተ ልሔም ከተማ ዘመሩ፡፡ (ሉቃ.2÷14)

እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በፍቅር ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ በዛሬው ቀን በቤተ ልሔም ለዓለም የሰጠው ስጦታ እጅግ በጣም የላቀ ነው፤ ምክንያቱም ሌሎች ስጦታዎች ከፍጥረቶቹ የሚገኙ የፍጥረት ውጤት ስጦታዎች ሲኾኑ የቤተ ልሔም ስጦታ ግን አንድ ልጁን ነውና፡፡ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ያገኙትን ሀብት ማካፈል ይችሉ ይኾናል፡፡ ልጃቸውን አሳልፈው ለሌላ መስጠት ግን እጅግ የሚከብድ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ለሰው ድኅነት ሲባል አንድ ልጅን አሳልፎ መስጠት ከባድ ኾኖ አልተገኘም፡፡ በመኾኑም በዛሬዋ ዕለት በኾነው ነገር እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍጹም ፍቅር ምን ያህል እንደኾነ በሚገባ ለማወቅ ችለናል፤ ልብ እንበል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጸው፡-

  1.   የሰው ዘር በአጠቃላይ በአዳም በደል ምክንያት ለሞትና ለኃሣር እንደተዳረገ ሁሉ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት ምክንያት የሰውን ዘር ሁሉ ለማዳን፤
  2.   እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ታላቅ ነገር ቢኖር የእርስ በርስ መፋቀር እንደኾነ ለማስረዳት፤
  3.  በኃጢአት ምክንያት ያጣነውን በእግዚአብሔር መንግሥት በክብርና በዘላለማዊ ሕይወት የመኖር ዕድል ለማስመለስ ነው፡፡

በዛሬው ዕለት በቤተ ልሔም የተወለደው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለፍጹም ምሕረት ለማብቃት በመኾኑና ምሕረቱንም በብዛት ስላፈሰሰልን ከጌታ ልደት ወዲህ ያለው ዘመን ዓመተ ምሕረት፣ ማለትም የምሕረት ዘመን ተብሎ ይታወቃል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! እግዚአብሔር ይህን ያህል ከወደደን እኛም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል፤ ከልደተ ክርስቶስ የምንማረው ትምህርት ወገንን ሁሉ ማለትም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን የሰው ዘር ሁሉ መውደድና መርዳት ነው፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹መሥዋዕትነትን ያይደለ ምሕረትን እወዳለኹ፤ እነኾ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለኹ፤ እርሱም እርስ በርሳችኹ ትዋደዱ ዘንድ ነው›› ብሎ እንዳስተማረን በፍቅር እየኖርን ችግረኞችን መርዳት ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር መኾናችንን ሰውን በመውደድና በመርዳት መግለጽ ይኖርብናል፡፡ ባለንበት ዘመን በተለያየ ምክንያት እናትና አባትን ያጡ፣ የወገንን ፍቅርና ክብካቤ የሚሹ ብዙ የእግዚአብሔር ልጆች በየሰፈሩ አሉ፡፡ ለበዓል መዋያ ያዘጋጀነውን ኅብስተ በረከት ከተቸገሩት ሕፃናትና፣ የሚላስ የሚቀመስ ካጡ ወገኖች ጋራ በመኾን በኅብረት መመገብ ይገባናል፡፡ ይህን ስናደርግ በፍጹም ፍቅሩ የወደደንን እግዚአብሔርን በቤታችን ውስጥ እየጋበዝን እንደኾነ ርግጠኞች መኾን አለብን፡፡ ‹‹ተርቤ አብልታችኹኛልና ኑ ወደኔ›› የሚል ቃል ኪዳን እንዳለበትም እናስታውስ፡፡

በሌላ በኩል በልዩ ልዩ በሽታ ተይዘው መዳንን በመሻት በየሆስፒታሉና በየሰፈሩ የሚገኙ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ በእነዚህ ወገኖች አድልዎንና ማግለልን ሳናደርግ ማስታመምና አቅማችን በፈቀደ መጠን እነርሱን ለማገዝ መረባረብ ምሕረትን የሚያስገኝልን እንደኾነ መገንዘብ አለብን፡፡ ‹‹ብታመም ጠይቃችኹኛልና መንግሥተ ሰማያትን ትወርሱ ዘንድ ኑ ወደ እኔ›› የሚል ቃል ኪዳን እንዳለበትም አንዘንጋ፡፡ መማር የሚያስፈልጋቸው ነገር ግን አቅመቢስ በመኾናቸው በአልባሌ ቦታ ጊዜያቸውን የሚያባክኑ ወገኖችን ተገቢውን ርዳታ በማሟላት ብቁ ዜጋ ማድረግ ግዴታችን ነው፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! የኑሮ መጓደል በየትኛውም ክፍለ ዓለም ያለ ቢኾንም ሌት ተቀን ጠንክረው በመሥራታቸው በተሻለ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኑሮ የሚኖሩ ሀገሮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያንም አሁን በተጀመረው የልማት ጎዳና በመሮጥ ሁላችን ለሥራ ብቻ ከተሰለፍን ያሉብን ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተወገዱ፣ ሀገራችን እንደበለጸጉት አገሮች በልማት አድጋ፣ ሕፃናት በክብካቤና በዕውቀት የሚያድጉበት፣ አረጋውያንና አረጋውያት የተቸገሩ ወገኖች በማኅበራዊ ተቋማት የሚረዱባትና የሚከበሩባት፣ በሁሉም መስክ ዜጎች በደስታ የሚኖሩባት አገር ማድረግ እንደምንችል ጥርጥር የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድና ፍላጎትም ይህ ነው፡፡ስለኾነም የተጀመሩና ሊጀመሩ ተቃርበው ያሉ ግዙፋን ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች የአገራችንን የድኅነት ገጽታ በመቀየር፣ ከበለጸጉ የዓለም አገሮች ጎን በእኵልነትና በክብር እንድንሰለፍ የሚያደርጉ፣ የኅብረተሰባችንን የዘመናት ችግር በአስተማማኝ ኹኔታ የሚቀንሱ መኾናቸው የታመነ ስለኾነና በሥራም የተረጋገጠ ስለኾነ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ የልማት ሥራውን በየዘርፉ እንዲያፋጥን በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን ይስጥልን፤ ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ፤ አሜን!!

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

                 ታኅሣሥ 29 ቀን 2005 ዓ.ም