አዲሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሀገረ ስብከቱና ከክፍላተ ከተማ ሠራተኞች ጋር ትውውቅ አደረጉ

በትውውቅ መርሃ ግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡ “የእንኳን ደህና መጡ መልእክትም” ለክቡር ሥራ አስኪያጁ አስተላልፈዋል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በተደረገው ውይይት ሀገረ ስብከቱ ያሉበትን ዘርፈ ብዙና ውስብስበ ችግሮች፣ እንዲሁም ብለሹ አሠራሮችና የወደፊት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ይሆናሉ ተብለው የታሰቡት ለክቡር ሥራ አሥኪያጁ ተጠቁመዋል፡፡በየጊዜው ሥራ አስኪያጆችን እየተቀበለ መሸኘትን ልማዱ ያደረገው  ሀገረ ስብከቱ ከዚህ ደካማ ድርጊቱ በፍጥነት ታርሞ፤ ዘመኑን የዋጀና አመርቂ የሆነ ሥራ ሠርቶ ስሙን በክብርና አወንታዊ በሆነ መልኩ እንዲያስጠራ ለሥራ አስኪያጁ ጠንከር ያለ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

ጽ/ቤቱ በሥሩ ሰባት ክፍላተ ከተሞች ያሉት አንጋፋ ተቋም ቢሆንም አንዱም ክፍለ ከተማ የራሱ የሆነ ቢሮ መሥራት አለመቻሉ፣ ከሙዳይ ምጽዋት ገቢ በቀር የራሱ የሆነ የገቢ ማስገኛ ልማት አለመኖሩ ሀገረ ስብከቱ በልማት አማራጭ በኩል ምን ያህል ደካማ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ተነስቶ፤በአስተዳደር ረገድም ከሀገረ ስብከት ወደ ክፍላተ ከተሞች ፣ገዳማትና አድባራት የሚወርዱ መመሪያዎች በወቅቱ ካልተፈጸሙ እንዲሁም በሌላ መልኩ ከአድባራት ከገዳማትና ከክፍላተ ከተሞች ወደ ሀገረ ስብከቱ የሚመጡ ችግሮች በጊዜውና በሰዓቱ እልባት ካላገኙ ሀገረ ስብከቱ ከገባበት አጣብቂኝ የአስተዳደር ችግር ሊወጣ እንደማይችል ንግግር ያደረጉ ታዳሚዎች ጠቅሰዋል፡፡ 

የስብከተ ወንጌል እንቅስቀሴንም አስመልክቶ በተነሳው ሀሳብ ሀገረ ስብከቱ የሚጠበቅበትን እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑን ተገልጿል፤ በአዲሱ ሥራ አስኪያጅም ችግሩ  እንደሚቀረፍ አስተያየት ሰጪዎቹ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሁላችንም ከጎኖት ነን፣ እናግዞታለን፣ ይበርቱ፣ ይጠንክሩ በማለት የውስጥ ስሜታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡

በመጨረሻም ዋና ሥራ አስኪያጁ ባደረጉት ንግግር ለተደረገላቸው “የእንኳን ደህና መጡ” የትውውቅ መርሐ ግብር አመስግነው ሀገረ ስብከቱን አስመልክቶ የቀረበላቸውን አስተያየት በሙሉ ልብ እንደተቀበሉት ገልጸው ዘወትር የእናንተ ጸሎትና ድጋፍ አይለኝ ብለዋል፡፡ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ለወደፊት የውይይት መርሃ ግብሮችን አዘጋጅተን በሰከነ መልኩ ያሉትን ችግሮች በነቂስ በማውጣትና መፍትሔ በመስጠት እንዲሁም  ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ሀገረ ስብከቱን ከገባባት ችግር በጋራ ተረባርበን እናወጠዋለን ለዚህም ደግሞ እግዚአብሔር  ይረዳናል በማለት ተስፋን የሰነቀ ንግግር አድርገዋል፡፡በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላችሁ ጊዜው አሁን ነው ሀገረ ስብከቱን ሊጠቅሙ የሚችሉ የተለያዩ ጥናቶችን ማቅረብ ትችላላችሁ የሚል ጥሪም አስተላልፈዋል፡፡

ስለ ትናንትና መቆጨት አያስፈልግም ትናንትና አልፏልና፤ ዛሬን ግን ልናባክነው አይገባም ይልቁንም ልንጠቀምበት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሥራን ለነገ ማሳደር የስንፍና ምልክት በመሆኑ የተሰጠንን ሥልጣንና ጊዜያችንን በአግባቡ በመጠቀም እግዚአብሔርንም ሰዎችንም የሚያስደስት ሥራ ልንሠራ ያስፈልጋል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የሰው ኃይል፣ የእውቀት፣የገንዘብ፣ የክህሎት ችግሮች ስለሌሉብን አሁን ባለው የሰው ኃይልና ፋይናንስ ተጠቅመን ወደ ልማትና እድገት ጉዳና እንጓዛለን ለዚህም ደግሞ አንድነት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና መረዳዳት አማራጭ የሌላቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አበክረው አሳስበዋል፡፡

ክቡር ሥራ አስኪያጃችን በአዲስ አበባ ከተማ ርዕሰ መዲና ተወልደው እንደማደገዎትና በተለያየ ሐላፊነት በከተማዋ ባሉት ገዳማትና አድባራት እንደማገልገልዎት መጠን የሀገረ ስብከቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደሚያውቁት ጥርጥር የለንም፡፡ በመሆኑም የተሰጠዎትን ሐላፊነት በአግባቡ በመጠቀም ከአባቶች፣ ከሀገረ ስብከቱ የክፍል ሐላፊዎችና ሠራተኞች፣ከክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች በፍቅርና በአንድነት በመሆን እንዲሁም የተማሩ አካላትን በማሳተፍ፣የቤተክርሰቲያን የጀርባ አጥንት የሆነውን የስብከተ ወንጌል ከምንጊዜውም በላይ በማስፋፋት፣ ብለሹ አሠራሮችን በማስተካከልና ችግር አፈታቱን በማዘመን የሀገረ ስብከቱን ጥንተ ክብሩን እንደሚያስመልሱለት ሚድያ ክፍሉ ጽኑ እምነት አለው፡፡

                                      መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *