ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ) የአ/አ/ሀ/ስ/ ዋና ሥራ አስኪያጅ የ2012 ዓ.ም በዓለ ሆሳዕናን አስመልክተው መልእክት አስተላፉ

ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ) የአ/አ/ሀ/ስ/ዋና ሥራ አስኪያጅ መልእክት ሲያስተላልፉ

ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት”ሉቃስ 19:41

ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንኳን ለ2012 ዓ.ም በዓለ ሆሳዕና በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ሲሉ መልእክታውን ያስተላለፉት ሥራ አስኪያጁ የ2012 ዓ.ም በዓል ሆሳዕና ስናከብር በዓለማችን የተከሰተውን የኮሮና(ኮቪድ-19) ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያመሰቃቀለ እንደሆነ በመገንዘብ ፈጣሪን አብዝተን በመማጸን እና የህክምና ባለሙያዎችም ሆኑ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚያስተላልፉትን መልእክት በመተግበር መሆን አለበት ብለዋል።
አያዘውም በአሁኑ ወቅት ብዙ ከተሞች በኮቪድ 19 ቫይረስ ስርጭት ምክንያት እየተዘጉ እንደሆነ ፣ ሰዎች በፍርሃት በር ዘግተው መቀመጥ የግድ የሆነበት ሰዓት መድረሳቸውን ፣ ቀባሪ ያጡ አስከሬኖች በሰልፍ ተጭነው እየሄዱ ያሉትን በማየት ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
በሀገራችን በኢትዮጵያም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መግባቱ ከተሰማ ዕለት ጀምሮ የበሽታው ስጋት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴችንን መገደብ መጀመሩን ገልጸው ገና ከመስፋፋቱና ብዙ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በህብረት ልንከላከለው ይገባል፣ ዛሬ የገጠመንን ፈተና ከልብ ወደ ፈጣሪያችን በንስሐ በመመለስ፣ ይቅር እንዲለን አብዝተን ከተማጸንን ቸሩ አምላካችን ምህረቱን ይልክልናል በማለት ክቡር ስራ አስኪያጁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።የክቡር ስራ አስኪያጁን ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ይቀርባል። መልካም ንባብ ፦

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን ።

እንኳን ለ2012 ዓ.ም. በዓለ ሆሳዕና በሰላም አደረሳችሁ!
“ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት” /ሉቃ. 19፡41 /

ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ ትምህርት ድውያነ ነፍስን ፣ በእጁ ተአምራት ድውያነ ሥጋን እየፈወሰ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር እንዳገለገለ ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል ። ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋነኛ ዓላማው ለቤዛነት ነውና በመስቀል ላይ ውሎ በደሙ ካሣ እኛን የሚያድንበት ጊዜ ቀረበ ። በሰሜን ገሊላ የነበረውን የመጨረሻውን አገልግሎት ፣ በምሥራቃዊው ኢያሪኮ የነበረውን የዘኬዎስ ቤት መስተንግዶ ፈጽሞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ሞት እንደሚጠብቀው ያውቃል ። ቅድስት ነፍሱን ለዕለተ ዓርብ ቤዛነት ሲጠብቃት ኑሯል ። ሄሮድስ ሊገድለው ሲሻ በሕፃንነቱ ወደ ግብጽ መሰደዱ ፣ ዲያብሎስ ከረጅም ተራራ ላይ ራስህን ወርውር ሲለው መገሠጹ ፣ አይሁድ ከተማቸው ከተሠራችበት ኮረብታ ሊጥሉት ሲሉ ተሰውሮ መሄዱ ለዕለተ ዓርብ ቤዛነት ቅድስት ነፍሱን መጠበቁ ነው ።

ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርገውን ጉዞ የጀመረው ከታላቁ ተራራ ከደብረ ዘይት ነው ። ከደብረ ዘይት መጀመሩ ደብረ ዘይት የጸሎት ተራራው ነበረ ። ወደ መሥዋዕትነት ሲሄዱ መጸለይ እንዲገባ ሊያስተምረን ነው ። ደብረ ዘይት የዓለምን ፍጻሜ ምልክት የተናገረበት የትንቢት ተራራ ነው ። የዘመንን ምልክት መጠየቅ እንዲገባ ሲነግረን ነው ። ደብረ ዘይት ተመልሶ የሚመጣበት ነው ። ምጽአትን ማሰብ እንዲገባን ሲያስተምረን ነው ። በደብረ ዘይት ወደ ሰማይ ያረገው በደብረ ዘይት ተመልሶ ይመጣል ። ደብረ ዘይት ከፍ ያለ ተራራ ሲሆን የኢየሩሳሌም ከተማን እንደ ተገለጠ ብራና ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ነው ።

ወደ ኢየሩሳሌም ቁልቁል የወረደው የታሰሩትን አህያና ውርንጫ ፈትቶ አምጡልኝ በማለት ነው ። እርሱ የታሰሩትን ፈትቶ የክብሩ መገለጫ ያደርጋቸዋል ። በኃጢአት ፣ በዲያብሎስ እስራት ያሉትን ፈትቶ የክብሩ መገለጫ ምድራዊ ኪሩብ ያደርጋቸዋል ። በአህያይቱና በውርንጫይቱ በአንድ ጊዜ ተቀመጠባቸው ይህም ተአምር ነው ። አህያይቱ ወይም እናቲቱ የብሉይ ውርንጫይቱ የታዳጊዋ የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ናቸው ። እርሱ በሁለቱም ኪዳናት ከብሯል ። በእስራኤል ባሕል ነገሥታት በአህያ ተቀምጠው ሲመጡ ዘመኑ ሰላም መሆኑን ያበሥራሉ ። በመስቀሉ ሰላምን ሊያደርግ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ተቀምጦ መጣ ።

ደቀ መዛሙርቱ ሲጀምሩ ፣ ሕዝቡ ሲቀበል ፣ በእናቶቻቸው እቅፍ ያሉ ሕፃናትም ሆሳዕና በአርያም እያሉ ዘመሩለት ። ልብሳቸውም በማንጠፍ ክብር ይገባሃል አሉት ፣ ዘንባባ በመያዝ ድል አድራጊ ነህ አሉት ፣ ሆሳዕና በአርያም በማለት አሁን አድነን በማለት ምስጋናና ልመና አቀረቡለት ። ጌታችንም ከዚህ ሁሉ ሕዝብ አሻግሮ ኢየሩሳሌምን አያት ። ከምስጋናው ዘልቆ የሚያልቁ የብዙ ሕዝቦች የሰቆቃ ድምፅ ተሰማው ። ከተማይቱን ባያት ጊዜ አለቀሰላት ። ጌታችን እንደ ሳቀ አልተጻፈም ፣ እንዳለቀሰ ግን ተጽፎአል ። ሁለት ጊዜ እንዳለቀሰ ሲጻፍልን አንዱ በአልዓዛር መቃብር ላይ ሌላው ለኢየሩሳሌም ያለቀሰው ልቅሶ ነው ።

ጌታችን እርሱን ማመንና መቀበል ያቃታትን ኢየሩሳሌም አሰበና በሰባ ዓ. ም. የሚገጥማትን ጥፋት በማሰብ አለቀሰላት ። ጌታችን አስቀድሞ አይቶ ያለቀሰበት ታሪክ ተፈጽሟል ። የሮማው የጦር ጀነራል ጥጦስ በደብረ ዘይት ተራራ በኩል አድርጎ ኢየሩሳሌምን ከበባት ሕዝቡም በከበባው በረሀብና በጥማት አለቀ ። በወርሐ ነሐሴ በ70 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ የተሠራው የዘሩባቤል መቅደስ ፈረሰ ። አንድ ሚሊየን አይሁዳውያንም አለቁ ። እስከ 1948 ዓ.ም. ድረስ እንደ ጨው ዘር በዓለም ሁሉ ተበተኑ ። ጌታችን የኢየሩሳሌምን የዛሬን ማማር ሳይሆን ፍርስራሽዋን አየ ፣ ሆሳዕና በአርያም የሚለውን የምስጋና ድምፅ ሳይሆን የሚታረዱትን ሕፃናት ድምፅ አደመጠ ፣ የከበቡትን ሳይሆን በዓለም ሁሉ የሚበተኑትን ቤተ አይሁድን አሰበ ። ስለዚህ አለቀሰላቸው ። መፍትሔ እያላቸው ተቸግረዋልና ።

ዛሬም የ2012 ዓመተ ምህረት የሆሳዕና በዓል በምናከብርበት ጊዜ ጌታችን ከአርያም ሁኖ በኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት በዓለማችን ላይ የተዘጉ ብዙ ከተሞችን እያየ ነው ። ጎዳናዎች ሰው አልባ ሆነዋል፣ሰዎች በር ዘግተው በፍርሃት ተከበዋል ፣ ቀባሪ ያጡ ብዙ ሬሳዎች በሰልፍ ሲሄዱ እያየን ነው ። በሀገራችን በሽታው መግባቱ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የበሽታው ስጋት በሃይማኖታዊ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ላይ ጥላውን አጥልቶ ምድራችን በጭንቀት ተውጣ እናቶች እንባቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ። ስለሆነም በጾምና በጸሎታችን የተጣላን ታርቀን ትንንሽ ምክንያቶቻችንን አስወግደን ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር በፍቅር ቆመን ከለመንነው እርሱ ያዝንልናል ። ፈጥነን ንስሐ ከገባንም ይምረናል ።
በመጨረሻም ለኢየሩሳሌም ከተማ እንዳዘነ ዛሬም ለተዘጉ ከተሞችና አገሮች ሁሉ እንዲያዝን እግዚአብሔርን በጸሎት እንለምነው ።
*ከባለሙያዎች በሚሰጠው ምክር ተጠንቅቀን ራሳችንን ከበሽታው እንጠብቅ።
*የአባቶችን ትእዛዝ አክብረን ቤተ ክርስቲያናችንን እናስከብር በማለት መልዕክቴን አጠናቅቃለሁ።
በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ
አቤቱ አሁን አድን!!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ።
መልአከ ሕይወት አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ)
. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *