1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየገዳማቱና አድባራቱ ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያለውን ት/ቤት አቋቁሞ ተማሪዎች መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበብ እንዲማሩ በማደረግ ላይ ነው ሥጋዊ ጥበብ የሚባለውም በቀደሙት አባቶቻችን አባባል ቀለም በጥብጦ፣ ብራና ፍቆ፣ ብዕርን ቀርፆ፣ መፃህፍትን መፃፍ፣ መጠረዝና መደጎስ እንዲሁም እርሻ ማረስ፣ ንግድ መነገድና የመሳሰለ ሲሆን እንደ ዘመኑ አባባል ደግሞ የቀለም ት/ቤቶችን አቋቁሞ /ከፍቶ በዘመኑ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እስከ ዮኒቨርሲቲ ያለውን ትምህርት መስጠት ማለት ነው በመሆኑም የኦ.አ.ሀ.ስ. ከሚያስተዳድራቸው ገዳማትና አድባራት መካከል የሚከተሉት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡

  1. የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1ኛና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት
  2. የደብረ ኃይል ቅድስ ራጉኤለ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት
  3. የምስካየ ሕዙናን መድሃኒዓለም 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት
  4. የማህደረ ብርሃት ቅድስት ልደታ ጤና ሳይንስ ዮኒቨርሲቲ ኮሌጅ
  5. የመንበረ መንግስ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ት/ቤት
  6. የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ት/ቤቶች ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ት/ቤቶች ናቸው፡፡

1.    የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት

በ1955 ዓ.ም. መስከረም 14 ቀን የማስተማር ሥራውን የጀመረው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በወቅቱ የተቀበላቸው የተማሪዎች 8 ብቻ ሲሆኑ እነዚህም መነኮሳትና ዲያቆናት ነበሩ፡፡ በ1956 ዓ.ም. ከ1ኛ እስከ 4ኛ ባሉ ቁጥራቸው 39 የሚደርሱ ተማሪዎችን ይዞ የመደበኛ ትምህርት ማስተማር ጀመረ፡፡ በዚያን ጊዜ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት “የኢትዮትያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት” በመባል ይታወቅም ነበር፡፡

ት/ቤቱን ለመክፈት ያስፈለገበት ዓላማም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦ ሲሆን  ዓላማውም ካህናትን ዘመናዊ ትምህርት ለማስተማር ነው በመሆኑም በወቅቱ ለነበሩ መነኮሳትና ዲያቆናት ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ በቀላሉ የተከናወነ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ የካቴድራሉ የበላይ አስተዳዳሪዎች ጥብቅ ቁጥጥር  እያደረጉ የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች ት/ቤት ገብተው እንዲማሩ ይደረግ ነበር፡፡

ቀደም ሲል ለቀሳውስት ፣መነኮሳትና ዲያቆናት ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦ የተቋቋመው የካቴድራሉ ት/ቤት አገልግሎቱን ወደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ የቤተክርስቲያኗ አንዱ ዓላማ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ሲሆን ልጆቻቸው እንዲማሩላቸው ይጠይቁ የነበሩ ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለክፍያ እንዲማሩ ሲደረግ በአካባቢ የነበሩ ጫማ ጠራጊዎች፣ መጽሔትና ጋዜጣ ሻጮች የትምህርት ዕድሉን እንዲያገኙ ተደርጓል።

ከዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት ጋር መንፈሳዊ ትምህርትም ይሰጥ ስለነበረ ት/ቤቱ ታዋቂነትና ዝና ያገኘው በጣም በፈጠነ ሁኔታ ነበር፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ሲጠቀስ የሚችለው ተማሪዎች በትምህርት ችሎታቸው፣ በትህትናቸውና በሥርዓት አክባሪነታቸው ተለይተው ስለሚታወቁ በቀላሉ የህብረተሰቡን ትኩረት እንደሳበ ይነገርለታል፡፡

የተማሪዎች ቁጥር ሲጨምርና ት/ቤቱም እያደገ ሲሄድ ተማሪዎች መጠነኛ ክፍያ እንዲከፍሉና የተሻለ የትምህርት አገለግሎት እንዲያገኙ ከህብረተሰቡ ጥያቄው በመቅረቡ በ1962 ዓ.ም. መጠነኛ ክፍያ-አምስት ብር-እንዲከፈል ተወስኖ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ትምህርት በክፍያ ሆነ፡፡የት/ቤቱ ፈላጊ ሕብረተሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱና ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በመሆኑ የተማሪ ቅበላ የሚከናወነው በየዓመቱ ኮሚቴ እየተቋቋመ ኮሚቴው በሚያወጣው የመቀበያ መስፈርት አማካይነት ነበረ፡፡

ት/ቤቱ መጀመሪያ ሲቆረቆር ይዞት የነበረው ቦታ አሁን ከካቴድራሉ ጽ/ቤት ጀርባ በነበሩ ክፍሎች ነበር፡፡ የተማሪ ቁጥር እያደገ ሲሄድ ደግሞ አሁን 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ያለበትን ቦታ ይዞ እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ 12ኛ ክፍል  በዚሁ ት/ቤት  የብሔራዊ ፈተና አስፈትኖ በወቅቱ በተደረገበት ተጽዕኖ ደረጃው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ባለው ደረጃ በቻ እንዲሆን ተደርጎ ነበር፡፡
በ1966 ዓ.ም. አብዮትን ተከትሎ የመጣው ሥርዓት በት/ቤቱ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ቢኖረውም በእርሾነት እንዲቆይና ለዛሬው ደረጃ እንዲደርስ የካቴድራሉ አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ከፍተኛ ጥረትና መስዋዕትነት መክፈላቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይኸም በመሆኑ ዛሬ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በሦስት የትምህርት ዕርከኖች ወይም ደረጃዎች ተደራጅቶ በርካታ ወጣቶችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ እነዚህም ት/ቤቶች፡-

  1. አፀደ ህፃናት
  2. የ1ኛ ደጃ ት/ቤት
  3. የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤቶች ናቸው፡፡

በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን እንደገና ማስተናገድ የጀመረው በ1ኛ ደረጃ ት/ቤት በ1996 ዓ.ም 9ኛ ክፍል በመክፈት ነበር በመቀጠልም በ1997 ዓ.ም. አዲስ ባሠራው ህንፃ የ2ኛ ደረጃና ኮሌጅ መሰናዶ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ት/ቤቱ ትምህርት ሚኒስተር ያወጣውን ሥርዓተ ትምህርት በመከተልና ባለ 3 ፎቅ የራሱ ህንፃ ገንብቶ ት/ቤቱን ከ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡በመሆኑም ት/ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ኮሌጅ መሰናዶ ድረስ ከ2,500 ያላነሱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ላይገኛል፡፡

ከትምህርቱ ጥራትም የተነሳ ተማሪዎች በሁሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያለፉ ስለመጡ የመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ በአዲሰ አበባ ከሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡በዚህም ምክንያት ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ት/ት ካቴድራሉን ብቻ ሳይሆን የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክርስቲያንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ት/ቤት ሆኗል፡፡

2.    የምስካየ ህዙናን መድሃኒዓለም ገዳም 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት

የምስካየ ህዙናን መድሃኒዓለም ገዳም 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤትከቀድሞው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት ቀጥሎ በ1974 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ት/ቤቱ ትምህርት ሚኒስተር ያወጣውን ሥርዓተ ትምህርት በመከተልና ባለ 4 ፎቅ የራሱን ህንፃ ገንብቶ ት/ቤቱን ከ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል የገዳሙ ት/ቤት በአሁኑ ሰዓት ከመዋዕለ ህፃናት እስከ መስናዶ ድረስ ከ2,000 ለሚያንሱ ተማሪዎች ጥራቱን የጠበቀ ት/ት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ከትምህርቱ ጥራትም የተነሳ ተማሪዎች በሁሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያለፉ ስለመጡ ት/ቤቱ በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ በአዲስ አበባ ከሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች እንደ አንዱ ለመሆንና ለመቆጠር በቅቷል በዚህም ምክንያት ት/ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ት/ት ገዳሙን ብቻ ሳይሆን የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክርስቲያንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ት/ቤት ሆኗል፡፡

3.    የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ት/ቤት

የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ት/ቤት በድብሩ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደርና ልማት ኮሚቴ እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ትብብር ሐምሌ 6 ቀን 1991 ዓ.ም ባለ 3 ፎቅ ህንጻ ተገንብቶ የመጀመሪ ደረጃ ት/ቤት የተከፈተ ሲሆን በ1997 ዓ.ም አሁን ወዳለው 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በማሳደግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ት/ቤቱ ወደ 2ኛ ደረጃ ተሸጋግሮ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን ማትሪክ ሲያስፈትን በመሰናዶ ደረጃ ደግሞ ከ11 እስከ 12 ክፍል ያሉ ተማሪዎችን በማስተማር ብዙዎቹ ጥሩ ነጥብ እያመጡ ዩኒቨርስቲ በመግባት ላይ ይገኛሉ በአሁኑ ጊዜ 1ኛ ደረጃውም ሆነ 2ኛ ደረጃው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙና ታዋቂ ከሆኑት ጥቂት ት/ቤቶች መካከል የሚጠቀስ ሆኗል፡፡

4.    የመንበረ መንግስ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ት/ቤት

የመንበረ መንግስ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ት/ቤት በ1998 ዓ.ም ተመስርቶ ከመዋዕለ ሕፃናት አስከ 10 ክፍል ድረስ የመደበኛ ትምህርት ለህብረተሰቡ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

5.    የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ት/ቤት

የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ት/ቤት በ1999 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍቶ ከ1ኛ እሰከ 8ኛ ክፍል ድረስ በማስተማር ላይ የሚገኝ ት/ቤት ነው

6.    ሌሎችም ለጊዜው ያልተጠቀሱ ነገር ግን በቀጣይ የሚጠቀሱ አሉ::