“ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ ዓመት እስከ ዓመት ስቅለት ነው”….ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ስቅለቱ ዛሬ በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም የከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ በተገኙበት ታብታተ ሕጉ ከመንበረ ክብራቸው ወተው ሕዝበ ክርሲቲያኑም ከአፍ እስከገደፉ በሞላበት ተከብሮ ውሏል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ  ረፋድ ላይ በአቃቂ ቃሊቲ አካባቢ በሃይማኖቱ ምክንያት የተሰዋውን ወጣት ቤተሰቦችን ለማጽናናት እና በጸሎተ ፍትሐቱም ላይ ተገኝተው እንደመጡ ጠቅሰው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ እና መፈናቀል ሊቆም ይገባል ብለዋል።

አክለውም ብፁዕነታቸው ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን በስሜት ሳይሆን በትዕግሥት የአባቶቻቸሁን ምክር እየሰማችሁ ብትሄዱ ከአሳሳቾች ትጠብቃላችሁ ሲሉ መክረዋል።

በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የዕለቱን ትምህርት እንዲሰጡ የተጋበዙት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ዕለቱን በተመለከተ ጥዑም ትምህርት ሰጥተዋል።

የጲላጦስን ፍርድ አንስተው አንድም ጥፋት አላገኘሁበት ብሎ መመስከሩ ግሩም እና የክርስቶስ እውነተኛ አምላክነት የመሰከረበት እኔዲሁም ይህ ምስክርነት ከአይሁዳውያን ወገን ወይንም ከሐዋርያት ቢሆን ኑሮ ያን ያህል አይደንቅም ነበረ ብለዋል።

ብፅዕነታቸው በዋናነት  ክርስቶስ የሞተለት ሰው አሁን በኢትዮጵያ በየቀኑ እየተገደለ ነው አሁንም ክርስቶስ እየተሰቀለ ነው ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ ዓመት እሰከዓመት ስቅለት ነው ሲሉ እንባና ሳግ እየተናነቃቸው ነበረ።

የካቴድራሉ መምህራን ወረብ ያቀረቡ ሲሆን የደብሩ ሰንበት ትምሀርት ቤት ዘማርያንም በለኒ መሐርኩከ የሚል ዝማሬ በነጫጭ አልባሳት ደምቀው አቅርበዋል።

የዕለቱን መርሐ ግብር የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከገነት ቆሞስ አባ ተክለማርያም አምኜና የደብሩ ስብከተ ወንጌል ኃላፊ ልሳነ ክርስቶስ መምህር ጳውሎስ ሰይፈሥላሴ መርተውታል።

በበዓሉ ላይ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሣሙኤል ታፈሰ እና መጋቤ አዕላፍ ፀጋዬ ደበበ ተገኝተው  ለቤተመቅደሱ ዕድሣት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የካባ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ማስታወሻ፦የአቃቂ ቃሊቲውን ሰማዕት ዘመድኩን አማረን የተመለከተ ልዩ ዘገባ ይዘን እንደምንመለስ ከወዲሁ እናሳውቃለን።

በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ
ፎቶ በዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *