ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሊቀ ጳጳስ ዘኢሉባቡር (ከ1960 እስከ 2014 ዓ.ም.)

ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከአባታቸው ከአቶ ወልደ አምላክ ሁንዴና ከእናታቸው ወ/ሮ በላይነሽ በዲየ በቀድሞ ሸዋ ክፍለ ሀገር፤ በፍቼ ዞን በሙከጡሪ ወረዳ በበቾ ፋኒሊ ቀበሌ ልዩ ስሙ ደሴ በሚባል ቦታ በ1960 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በታላቁ የደብረ ሊባኖስ ገዳም የጀመሩት ብፁዕነታቸው፤ በገዳሙ ከሚገኘው አንጋፋው የመምህር ገብረ ማርያም ንባብ ቤት መሠረታዊ የግእዝ ንባብ፣ በደብረ ጽጌ ገዳም ከመምህር ልዑል ቅዳሴ ቤት ገብተው የግብረ ዲቁና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

በተጨማሪም ከየኔታ መርዓዊ ዜና ከቃል ትምህርት ጀምረው እስከ ዐቢይ ምዕራፍ ያለውን በማጠናቀቅ ጾመ ድጓና ድጓ የተማሩ ሲሆን፤ ከመምህር ወልደ ገብርኤል ዝማሬ መዋሥዕት እንዲሁም ከአቋቋሙ መምህር ከየኔታ በትረ ማርያም ክብረ በዓል፣ መዝሙርና አርባዕት፣ ወርኃ በዓልና መኃትው፣ ስብሐተ ነግህና ኪዳን ሰላም፣ ቅንዋትና አርያም በድጋሚ ዝማሬ መዋሥዕት በሚገባ ተምረው አጠናቅቀው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

በተጨማሪም ከመምህር ምሕረተ ሥላሴ የቅኔ ጉባኤ ቤት ቅኔ ተምረው የተቀኙ ሲሆን፤ በድጋሚ ከመምህር አምዴ ጉባኤ ቤት ገብተው ለሁለተኛ ጊዜ ቅኔ ተቀኝተው አገባቡን ቀጽለዋል፡፡

በታላቁ የደብረ ሊባኖስ ገዳም በመምህር ገብረ ኢየሱስ ስም በተቋቋመው የብሉያትና ሐዲሳት ትርጓሜ አዳሪ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት፤ በብሉይ ክፍል ገብተው ለስምንት ዓመታት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ 5ኛ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ የብሉይ ኪዳን ትርጓሜ ምክትል መምህር ሆነው አስተምረዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ለመንፈሳዊ ትምህርት ካላቸው ፍቅር ብሉይ ኪዳኑን እያስተማሩ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜንና መጽሐፍተ ሊቃውንት በዚሁ በገዳሙ ተምረው ተመርቀዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሚካኤል መዐርገ ዲቁናን በደብረ ጽጌ ገዳም የተቀበሉ ሲሆን፤ የአበውን ፍኖት በመከተል በታኅሣሥ 24 ቀን 1996 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ገዳም ሥርዓተ ምንኩስናን በመፈጸም በ1997 ዓ.ም. በጊዜው የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ዮሴፍ መዐርገ ቅስናን ተቀብለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው መንፈሳዊ ትምህርት ለመቅሰም ከነበራቸው ትጋት ባልተናነሰ መልኩ በአገልግሎታቸውም እጅግ ትጉህ፣ ምስጉንና ሰፊ አስተዋጽዖ ያበረከቱ አባት ነበሩ፡፡

ከሰጡት አገልግሎት በጥቂቱም÷ በፍቼ ሀገረ ስብከት በስብከተ ወንጌልና በትምህርት ክፍል ሓላፊነት፤ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ካሉ የአብነት ጉባኤ ቤቶች ለተወጣጡ ከ300 ያላነሡ ደቀ መዛሙርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን ተከታታይ ሥልጠና ሰጥተዋል።

በመንፈሳዊ የትምህርት መስክ ያላቸውን መክሊት ከግንዛቤ በማስገባት በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው እንዲያስተምሩ ታጭተው የነበረ ቢሆንም፤ የደብረ ሊባኖስ አባቶችና ደቀ መዛሙርት በገዳሙ እንዲቆዩላቸው በጠየቁት መሠረት በገዳሙ ቆይተው በመምህራቸው በመምህር ጥበቡ አስናቀ እግር ተተክተው ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በዋና መምህርነት አስተምረዋል፡፡

የብፁዕ አቡነ ሚካኤልን አገልግሎት፣ የትምህርት ዝግጅትና መንፈሳዊ ሕይወት ተመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ባደረገው ምልአተ ጉባኤ የኢሊባቡር ሀገረ ስብከተ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው እንዲሠሩ መርጧቸው ሐምሌ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከሌሎች 14 አባቶች ጋር ሥርዓተ ሢመታቸው ተከናውኗል፡፡

ብፁዕነታቸው በአገልግሎታቸው ትጉህ፣ ለመንጋቸው እጅግ የሚጨነቁና በተመደቡበት የኢሊባቡር ሀገረ ስብከት ለስማቸው ሐውልት ሆነው የሚመሰክሩ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል በሀገረ ስብከቱ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ አብያተ ከርስቲያናትን በማሳደስ ለአገልግሎት ምቹ ያደረጉ ሲሆን፤ በተጨማሪም ማኅበረ ምእመናንን እና በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር 14 የሚደርሱ የታላላቅ ካቴድራሎችና አድባራት ህንጻ ቤተ ክርስቲያንን አሳንጸዋል።

በሀገረ ስብከቱ በነበረው የአብያተ ክርስቲያናት በየሥፍራው አለመኖር ምእመናን የመካነ መቃብር እጦትን ጨምሮ መንፈሳዊ አገልግሎትን ለማግኘት መቸገራቸውን የተረዱት ብጹዕነታቸው፤ ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች 22 አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል በሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን የአብያተ ክርስቲያናት ብዛት ወደ 373 አሳድገዋል።

ብፁዕነታቸው በሀገረ ስብከቱ ያለውን የአገልጋይ ካህናት እጥረት እና የስብከተ ወንጌል ውሱን ተደራሽነትን መቅረፍን ዐቢይ ዓላማ በማድረግ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር በመቱ ፈለገ ሕይወት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም እና ካህናት ማሰልጠኛ ማዕከል የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ከየወረዳው የተወጣጡ 46 ደቀ መዛሙርት እንዲማሩ አድርገዋል።

በሀገረ ስብከቱ ላሉ ምእመናን ወንጌልን በአፋን ኦሮሞ ተደራሽ ለማድረግ አይነተኛ መፍትሔ መሆኑን የተረዱት እኚህ ደገኛ አባት፤ የካህናት ማሰልጠኛዎች እንዲጠናከሩ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ መሠረት ጥለዋል።

ከካህናት ማሰልጠኛው በተጨማሪ ሀገረ ስብከቱን በገቢ ለማጠናከር ግምቱ ከሰማንያ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ዘመናዊ ባለ 5 ፎቅ ሁለገብ ሕንጻ በማስገንባት ላይ ነበሩ።

ብጹዕ አቡነ ሚካኤል የመጻሕፍት ሊቅ በመሆናቸውና በትምህርት መስፋፋት ላይ በርትተው መሥራትን የሚመርጡ ስለነበሩ የካህናት ማሠልጠኛውን ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለማሳደግ የሕንጻ ግንባታን አስጀምረዋል።

ምእመናን በመንፈሳዊና በአስኳላ ትምህርት በሁለት በኩል የተሳሉ ሰይፍ እንዲሆኑ በማሰብም የአጸደ ሕጻናት እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በማሳነጽ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል አድርገዋል።

የሀገረ ስብከቱን ገቢ ለማሳደግ በመቱ ከተማ ሁለት ተጨማሪ ሕንጻዎችን በማስገንባት የቤተ ከርስቲያን መገለጫዋ የሆነውን የአካባቢ ጥበቃ በገቢ ማስገኛ አማራጭ እንደሚሆን በማቀድ የመናፈሻ ሥፍራዎችን በመቱ ከተማ በማደራጀት ተፈጥሮአዊ ሀብትን የማስጠበቅ ሥራን ሠርተዋል።

ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠማት የሰላም እጦት ወቅት በሀገረ ስብከታቸው ባሉ አድባራትና ገዳማት ጸሎተ ምሕላ እንዲደርስ በማድረግ የሰላም ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ሰላምን ይሰጥ ዘንድ ሲጸልዩ ቆይተዋል።

ዝም ብለው የሠሩት ሥራቸው ብዙ የሚናገርላቸው፣ እጅግ መንፈሳዊና ተሐራሚ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን መክሊት በብዙ አትርፈው በአደረባቸው ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በ54 ዓመታቸው በዕረፍተ ሥጋ ተለይተውናል።

የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች፣ የኢሉባቡር ሀገረ ስብከት ሓላፊዎችና ምእመናን በተገኙበት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተከናውኗል።

እግዚአብሔር አምላካችን የብፁዕ አባታችንን ነፍስ ለወዳጆቹ ቅዱሳን፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ባዘጋጀው መካነ ዕረፍት በክብር ያሳርፍልን፣ እኛንም ያጽናን!

በብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሊቀ ጳጳስ ሥርዓተ ቀብር ላይ የተገኛችሁትን ሁሉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም እናመሰግናለን፣ ከአባታችን በረከት ይክፈልልን!!

   ምንጭ :- የኢኦተቤ ቲቪ ፌስቡክ ገጽ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *