የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

የትምህርቱ አስፈላጊነት( የጥናቱ አስፈላጊነት)

 • የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የእምነቱ መሠረትና መነሻ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን በሚገባ ለማወቅና ለመረዳት እንዲሁም ለሌላውም ለማሳወቅና  ለማስረዳት ስለሚያስችል፤
 • መጽሐፍ ቅዱስን በግልም ሆነ በማህበር ስናነብና ስናጠና ዋና ሀሳቡንና ትርጉሙን በቀላሉና በቶሎ እንዲገባን ሊያደርግ የሚያስችል በመሆኑ፣
 • በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ በቂ መረዳትና ችሎታ እንዲኖር፣ የአጠናን ዘዴዎችን ከአወቁ በኋላ መልስ ለመስጠት የተዘጋጀን እንድንሆን፣
 • የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ስብከትና ትምህርት ሲሰጡ በምንማርበትና በምንሰማበት ጊዜ እየተረዳንና እየገባን በፍጥነት መከታተል እንችላለን፡፡
 • በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነሱ ማንኛውንም ጥያቄ ለመመለስ ከማስቻሉም በላይ ለሌሎች ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለመመስከር እና ለማስተማር እንድንችል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚገባ ያስተዋውቀናል፡፡ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዲኖረን ያለማምደናል፡፡

የትምሕርቱ ዓላማ( የጥናቱ ዓላማ)

 • መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው የፍቅር ምልክት እንደመሆኑ መጠን ዓላማው ሰዎችን የመጥቀምና ሕይወትን የሚሰጥ የፍቅር ዓላማ ነው፡፡
 • በዓለም ላይ ያለውን የአለፈውን የአሁኑንና የወደፊቱን ሁኔታ የሚታየውንና የማይታየውን ድርጊት እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ማስረዳት፣
 • የእግዚብሔር ሐሳብ እና የእግዚአብሔርን የፍቅር ሥራ እቅዱን፣ ፈቃዱን ለሰው ማሳወቅ
 • ሰዎችን ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንዲያምኑና አምነውም በደሙ ሕይወት እንዲሆንላቸው መግለጽ፡፡ ዮሐ.2ዐ-30
 • የመዳንን መንገድ ማሳወቅ ፣  ዮሐ.6፡4ዐ ፣አቆሮ 1፡21    ዮሐ.2ዐ፡31
 • ለሐጢአተኞችና ለጻድቃን የሚከፈለው ዋጋ ማሳወቅ
 • የመጽሐፍ ቅዱስን ዓላማ ማስተማር  ዮሐ.2ዐ፡31
 • አጠቃላይ መግቢያ መስጠት እንዴት፣ በእነማን፣ የት አካባቢ እንደተጻፈ ማሳየት
 • 81 መጽሐፍት አጠቃላይ ሁኔታ ስም፣ ይዘት፣ ወዘተ… ማስጠናት
 • በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ አውቆ ለመመለስ ማስቻል
 • በቅዱስ መጽሐፍ መመሪያ እና ሥርዓት ለመኖር ማሳየት
 • መጽሐፍ ቅዱስ የፍቅር ምልክት ስለሆነ ሰዎች ሁሉ ተፋቅረው እግዚአብሔርን በመውደድ ለቃሉም በመታዘዝ የክብር ትንሳኤና ዘለዓለማዊነት፣ በተስፋ እንዲጠብቁ ይገልጻል፣ ያነቃቃል፡፡

መግቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ እስከዛሬ በዓለም ካሉት መጻሕፍት ይልቅ እጅግ ታላቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህም ረጅም ዘመናት በመቆየት በዓለም ላይ ተወዳጅ ከመሆኑም በላይ ብዙ አንባቢዎችን በማግኘት ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ሌሎችን መጻሕፍት ብናነባቸው እውቀትን ከመስጠት የሚያልፉ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለሰዎች ሕይወት ብርሃንና መንገድ ነው፡፡‹ እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስ ነው፡፡ ሕይወትም ነው፡፡› እንዳለ ዮሐ. 6፡63 ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ለጊዜው አንብበን የምንተወው መጽሐፍ አይደለም፡፡

ምክንያቱም፡- መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትና ሃይማኖት መመሪያ እንደመሆኑ መጠን የቤተ ክርስቲያን ልጆች አማንያን ሁሉ ይልቁንም አገልጋዮች በሚገባ ሊያውቁት ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሥራቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን ፍጹም አምላክ ቢሆንም ደግሞም ፍጹም ሰው ነውና በልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሊማር ት/ቤት ገብቶ እንደነበረ ‹ ተአምረ እየሱስ‹ የተባለው የቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ይናገራል፡፡ በሉቃ.2፡48 ላይ እንደተገለጸው ገና በአሥራ ሁለት ዓመቱ ከመምሕራን ጋር በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ጥያቄ ሲጠይቅ ለሚጠይቁት መልስ ሲሰጥ መጻሐፍትንም ሲጠቅስ የሚሰሙት በማስተዋሉና በእውቀት መመለሱ ሁሉንም አስገርሞአል፡፡ ጌታ በጥበብና በቁመት በሞገስም ያድግ እንደነበረ ተጽፏል፡፡ ሉቃ.2፡52፡፡

በማስተማር ዘመኑም ቢሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ ለሚሰሙት በቂ ትምህርት ለሚጠይቁትም አጥጋቢ መልስ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም አስቀድሞ የጽሑፍን ጥበብ ለሰው ልጆች የገለጸው አምላካችን እግዚአብሔር በሄኖክ ዘመን የፊደላትን መልክ በሰማይ ሰሌዳ ላይ አሳየ፡፡ ዘፍ.4፡26፡፡ ከዚያም በኋላ የሰው ልጆች የፊደላትን መልክ ለይተው ማወቅና ማጥናት በሕሊና የሚመላለስ ሀሳብ በአፍም የሚነገር ቃል እንዳይረሳ በመጽሐፍ ተጽፎ የታወቀ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ባገኘው ትውልድ በሄኖክ ዘመን ለሰው ልጆች ጽሕፈትን አስተማረ፡፡ ኩፋ.5፡22-24፡፡ ሁሉን በጊዜው ገልጦ ያሳየ አምላክ በስጋ ተገልጦ ሰው ሆኖ በሚመላለስበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡     ‹መጻሕፍትን ካላመናችሁ ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?› ዮሐ. 5-47፡፡ ላይ በማለት እምነት በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት መሆኑን ገልጿል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በኋላ እንኳን በኤማሁስ መንገድ ለተገለጠላቸው ሁለቱ ቀደመዛሙርት ባለማስተዋላቸው ከገሰጻቸው በኋላ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ያለውንና የተነገረውን ተርጐሞላቸዋል፡፡ ለሐዋርያትም ቢሆን መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከተፈላቸው፡፡ ሉቃ.24-27፡፡
ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ  እየተመሩ ቅዱሳን ሰዎች የጻፉት ስለሆነ ስሕተት የሌለበት መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡ ይህንንም ታስተምራለች፡፡ እግዚአብሔር በቅዱሳን ሰዎች ላይ አድሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲጽፉ ምስጢርንና እውቀትን ከሚገልጽባቸው መንገዶችና ዘዴዎች መካከል፣

1ኛ. ቃል በቃል፡- ባርያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እርሱ በቤቱ ሁሉ የታመነ ነው፡፡ እኔ አፍ ለአፍ በግልጽ እናገረዋለሁ፡፡ በምሳሌም አይደለም፡፡ ዘኁ.13፡7-8

ልበ አምላክ ዳዊትም፡-የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ፡፡ 2 ሳሙ.23፡2፡፡

2ኛ.  በሕልም፡- ዮሴፍም ሕልምን አለመ ለወንድሞቹም ነገራቸው፡፡ ዘፍ.37፡5፡፡

3ኛ.  በራዕይ፡- በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ በራዕይ እገለጽለታለሁ፡፡ ዘኁ.12፡6

ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ፡፡ 2.ጴ.ጥ.1.21

4ኛ. በመጽሐፍ እንዲጽፉ፡-በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፡፡ በኋላየም የመለከትን ድምጽ የሚመስል ትልቅ ድምጽ ሰማሁ፡፡ የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ለአብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ፡፡ ራዕ.1፡1ዐ፡፡ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ እንዲህ ከሆነ ቅዱስ መጽሐፍ በቅዱሳን ሰዎች እንደተጻፈ ቢነገርም በራሳቸው ሀሳብ ወጥተው ወርደው አመንጭተው ሳይሆን በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመርተው ጽፈዋቸዋል፡፡ ብዙ ሊቃውንትም የሚስማሙበት አንድ የሚሆኑበት ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ሥራ መለኮታዊ ነው ይላሉ፡፡

ይህም ማለት የሰዎች ቃልና የሀሳባቸው ፍሬ ሳይሆን እግዚብሔር መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ከናፍር ያናገራቸው በሰዎች ብዕር ያጻፋቸው ናቸው ማለት ነው፡፡ ኢሳ.34፡16፣ ኤር.36 በሌላ አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ዓይነት ደራሲ(አዘጋጅ)አለው፡፡ ሰው ሁለተኛው ደራሲ ሲሆን መጀመሪያውና ዋናው ደግሞ በእያንዳንዱ ደራሲ ላይ አድሮ ያሳሰበ፣ የመራ ያመለከተ እንዲሁም በእውቀትና በጥበብ ተሞልቶ የገለጠ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ከዚህ የተነሳ ልዑል እግዚአብሔር የፈለገውን እንዲጽፍ፣ እንዲናገር ሰዎችን የሚያነሳሳ መሆኑ ከታወቀ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት የራሱ የእግዚአብሔር እስትንፋስ እና ቃል ናቸው፡፡ ይህም ኦሪት፣ ነቢያት፣ ጽሕፋት እንዲሁም ሐዋርያት በወንጌላቸውና በመልእክታቸው በሰፊው ጽፈዋል፡፡ ነገ.2፡8-16፡፡ ነህ.8፡ኤር.25፡1-23  2ጢሞ 3፡17፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው የሰዎች ድርሻ ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን በጽሑፍም ሆነ በቃል ማስተላለፍ ሲሆን በሁለተኛ ደራሲነታቸው በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በቅርፀት፣ በጽሕፈት የመጣላቸውንና የተገለጠላቸውን ቃል አስተውሎና ጠንቅቆ በመያዝ እንዲሁም በተሰጣቸው እውቀት በጽሑፍ በማስተላለፍ አስተዋጾ አላቸው፡፡ ከዚህ በቀር ለመናገርም ሆነ ለመጻፍ እግዚአብሔር የገለጠላቸውን እንጂ ከራሳቸው አመንጭተው እግዚአብሔር እንዲህ አለ በማለት አይናገርም፡፡ ኤር.1፡7፡፡ ሕዝ.2፡7፣ አሞ.3፡7፣ 1ነገ 22፡7፡፡

ምክንያቱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተውና ተነድተው መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉ ሰዎች ከተለያዩ የሥራ መስክ የተጠሩ ናቸው፡፡ ከዚህም  ሌላ በተለያዩ ዘመንና በተለያዩ አህጉር የኖሩ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹም አይተዋወቁም ነበር፡፡ ሆኖም የጻፉአቸውን መጻሐፍት የጻፋቸው አንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ቃሉም ሆነ መልእክቱ ፈጽሞ አይጋጭም፡፡(አይጣላም፡፡)

ጸሐፊዎች በችሎታቸውና በእውቀታቸው የተለያዩ ሆነው ሳለ በእግዚአብሔር መንፈስ የጻፉአቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ግን ዋና ሀሳብና መልእክታቸው አልተለያየም፡፡ በዚህም ምክንያት እኛ ለሕይወታችን መመሪያ መጽሐፍ ቅዱስን የበላይ አድርገን ተቀብለነዋል፡፡ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን ይባላል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትን በውስጡ የያዘ የእግዚአብሔር የቃሉ መዝገብ ነው፡፡ በተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት በኋላ ዘመን በአንድነት ተሰባስበው የሚገኙበት መጽሐፍ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም በአንድነት እርስ በእርሳቸው ሳይፋለሱ የሚናገሩት ለሰው ልጆች የተላለፈውን የእግዚአብሔርን መልእክት ነው፡፡

ስለዚህ ከልጅነታችን ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን መማር፣ ማወቅ፣ ማጥናትና ማስተዋል እንደሚገባ እንረዳለን፡፡ ሐዋርያት ያስተምሩ የነበረውም ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጥቀስ ነበር፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና፡፡ ሮሜ.15፡4

ስለሆነም ለማንኛውም ትምህርት መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ ከሕጻንነታችን ጀምሮ ማወቅና ማጥናት አለብን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በተማረውና በተረዳው ነገር ጸንቶ እንዲኖር ከመከረው በኋላ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡ የሚችሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደሚያውቅ መስክሮለታል፡፡ 2ኛ ጢሞ.3፡114-15 ራሱም ቅዱስ ጳውሎስ የሚያነባቸው ቅዱሳን መጻሕፍት ነበሩት፡፡ 2ኛ.ጢሞ.4፡13፡፡

ነገር ግን ቅዱሳን መጻሕፍትን ስንማርም ሆነ ስናጠና በመንፈስ እንጂ በሥጋ መሆን የለበትም፡፡ በሥጋዊ ስሜት መጻሕፍትን መመርመር ሕይወት አይገኝበትም ‹እናንተ መጻሕፍት የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ ጌታ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ.5፡39›

ስለዚህ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመንፈስ ሆነን እግዚአብሔር በሚሰጠው ማስተዋል መርምረን በሕይወታችን እየተረጐምን እንደ መጻሕፍት ሁሉ እኛም ስለጌታችን ልንመሰክር ይገባናል፡፡ በዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ሁሉን ለይተን እንድናውቅ የሚረዳንን ጽሑፍና እውቀት አምላካችን ይስጠን አሜን፡፡