የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ዓመታዊ ክብረ በዓል፣ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ተከበረ

ጥር 04 ቀን 2013 ዓ/ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የምዕራብ አውስትራልያ ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ ፣ መ/አሚን ቆሞስ አባ ላ/ማርያም የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መ/አሚን ቆሞስ አባ ኃይለ መለኮት፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አለቆች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና እጅግ በርካታ ምእመናን በተገኙበት በደ/ነ/ቅ/ዮሐንስና መ/ጎ/ቅ/ማርያም ቤተክርስቲያን በዓሉ በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉ ሌሊት በሥርዓተ ማኅሌት፣ በብፁዕነታቸው እየተመራ በጸሎተ ኪዳንና በቅዳሴ የተከበረ ሲሆን ጠዋት በመድረኩ በሊቃውንት “ውእቱ ቃል ኃደረ ላዕሌነ፥ ወተወልደ እምኔነ” ያ(ይህ) ቃል በእኛ አደረ፣ ከእኛ ተወለደ” ብለህ የነገርከን ወልደ ነጎድጓድ ፈክር ለነ (ተርጉምልን) የሚልና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የአጫብር ዝማሬ በድምቀት ሲቀርብ በመ/ር ዘለዓለም ወንድሙም “እመኬ ፈቀድኩ የሀሉ እስከ ሰቦ እመጽእ፣ እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ”(ዮሐ 21፥22) በሚል ርእስ መነሻነት ዕለቱን በተመለኸተ ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ቀርቧል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መ/አሚን ቆሞስ አባ ኃይለ መለኮት ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንትና መላ ምእመናን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ወደ መድረኩ ጋብዘዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፡ በዓሉ የዮሐንስ ወንጌላዊው በዓለ ዕርገቱ ወይም መሰወሩ የምናከብርበት በዓል ነው ካሉ በኋላ ዮሐንስ ከዓሳ አጥማጅነት የተጠራ፣ እሱም ዓለሙን ንቆ ሁሉንም ትቶ የእግዚአብሔር አገልጋይ በመሆን በወጣትነቱ ስለ መንግሥተ ሰማያት እየሰበከ ሰዎችን ወደ መንግሥተ ሰማያት ያጠምድ ዘንድ የተጠራ፣ አገልግሎቱን ያከበረ ሐዋርያና ነገረ መለኮትን በርቀትና በጥልቀት በመመርመር ምሥጢረ ሥላሴ፣ የእግዚአብሔርን ህልውና የገለጠ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው መሆኑን አብራርተው አስረድተዋል።
ብፁዕነታቸው ቅዱስ ዮሐንስ ነገረ እግዚአብሔርን እየገለጠ በእውነት የተመላለሰ፣ ቅድስናን በቃልና በተግባር ያስተማረ ቅዱስ ስለ ሆነ እኛም “ዝክረ ጻድቅ ይሄሉ ለዓለም፣ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል” የሚል ቃል በማክበር ቅዱስ ዮሐንስን እያስታወስንና እየዘከርን ነው ካሉ በኋላ የቅዱስ ዮሐንስና የቅዱሳን ሁሉ ፍኖት ተከትለን ሰባኪውም ተሰባኪውም በእውነት በመመላለስ በዘመናችን በቅድስና ልንኖር ያስፈልጋል ብለዋል።
በመቀጠልም የሐዋርያትን በዓል ስናከብር መንፈሳቸው በእኛ ላይ እንዲያድርና እንደነርሱ በቅድስና እንድንመላለስ ያስፈልጋል ብለው እግዚአብሔር በዮሐንስ በረከት ይባርከን ዘንድ፣ ዮሐንስ የገባበት እንድንገባ የአምላካችን መልካም ፈቃድ እንዲሆን በጸሎታቸው አምላክን ተማጽነዋል።
በመጨረሻም መርሐ ግብሩ በብፁዓኑ ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎትና ብራኬ ፍጻሜ ሆነዋል።


ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *