የቦሌ ክፍለ ከተማን ሥራ እዚሁ መጥቼ እሠራለሁ……ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ

(ነሐሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም )
(አዲስ አበባ÷ኢትዮጵያ)
የአዲስ አበባ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ሁለንተናዊ ዕድሳት ተደርጎለት ለምርቃት የበቃውን የቦሌ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ነሐሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በመረቁ ወቅት ያስተላለፉት መልእክት ነው፡፡
ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር ታሳቢ አድርጎ የተጀመረው ሁለንተናዊ ዕድሳት በአጭር ጊዜ በመጠናቀቁ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች፡ የመንግሥት ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የዛሬው በዓል “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ” የሚለው የሐዋርያው ቃል ተፈጽሞ የተመለከትኩበት ዕለት ስለሆነ ደስታዬ ወደር የለውም፡ የቦሌ ክፍለ ከተማን የሚመለከቱ ሥራዎቼንም እዚሁ መጥቼ እሠራለሁ ብለዋል፡፡
ይህ ቦታ የኪራይ ቤት ቢሆንም የሠራተኞችን የሥራ ተነሳሽነት ለመጨመርና ለተቋሙም የሚገባውን ክብር ለመስጠት መታደሱ አግባብ ነው፡ ለዚህ ዓላም ምንም ዓይነት ገንዘብ ሀገረ ስብከቱ ሳይደጉማቸው በመልአከ ብርሃን ሩፋኤል እና በሌሎች አጋሮቻቸው ትብብር መሠራቱን አውስተው አመስግነዋል፡፡
በቦሌ አየር ማረፊያ አካባቢ ለቦሌ ደ/ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል የጥምቀት ማክበሪያ
ከተሰጠው 41 ሽህ ካሬ ቦታ ላይ በአንድ ሽህ ካሬው ላይ የክፍለ ከተማው ጽ/ቤት ሕንፃ እንዲሠራም ፈቅደዋል፡፡
አያይዘውም ሁሉም ክፍላተ ከተሞች የራሳቸው ጽ/ቤት ኖሯቸው ሥራቸውን በተረጋጋ መልኩ እንዲሠሩ ለከተማ አስተዳደሩ የቦታ ጥያቄ እንደቀረበ ገልጸዋል፡፡
በየትኛውም ሁኔታ የሚሠራ ሰው ሊደገፍና ሊደነቅ ይገባዋል፡ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃንን የምናደንቃቸው ዛሬ በሠሩት ሥራ ብቻ ሳይሆን ትናንት የነበሩበትን የሰዓሊተ ምሕረት ማርያም ካቴድራልን እንዴት እንደለወጡት ስለምናውቅም ጭምር ነው ያሉት ደግሞ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ ናቸው፡፡
ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር ታሳቢ አድርጎ የተጀመረው ዕድሳት በክፍለ ከተማው ጽ/ቤት ሠራተኞች እና በክፍለ ከተማው ሥር በሚገኙ ገዳማትና አድባራት የገንዘብና የማቴሪያል ዕገዛ በአጭርጊዜ ውስጥ ተሠርቶ መጠናቀቁን
በቀረበው የሥራ ሪፖርት ተገልጿል፡፡
በብፅዕነታቸው ጥረት ለለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና በቅዱስ ያሬድ ስም ለሚከፈተው የካህናት ማሰልጠኛ መሥሪያ በተሰጠው 25 ሽህ ካሬ ቦታ ላይ በአጭር ሥራ እንደሚጀመርም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን በሥራው
የተሳተፉትን አካላት አመስግነው በዕለቱ ለተገኙት እንግዶቻቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ በኅልውና ዘመቻ ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በክፍለ ከተማ ሥር ከሚገኙት ገዳማትና አድባራት የተሰበሰበውን አንድ ሚሊየን ብር ተለግሷል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ለመልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን የማበረታቻ ሽልማት ሲሰጥ ክፍለ ከተማው ደግሞ ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ ላደረጉ ገዳማትና አድባራት የመጽሐፍ ቅዱስ እና የምስክር ወረቀት አበርክቷል ፡፡
የቤቱ ባለቤት ወ/ሮ ፀሐይ ደስታ ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የዕውቅና ሽልማት እና የግቢ ቁልፍ ተቀብለው በቤቱ ዕድሳት እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡ ሕይወታቸው እስካለ
ድረስ ቤቱን በተመጣጣኝ ኪራይ ቤተ ክርስቲያን እንድትጠቀምበት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
በምርቃት መርሐ ግብሩ የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ጨምሮ፡ የመንበረ ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፡የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፡ የጠ/ቤ/ክህነት፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና የክፍላተ ከተሞች የሥራ ኃላፊዎች፡ የክፍለ ከተማው ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃንና የክፍለ ከተማው ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ተጋባዥ ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ:- መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡- መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published.