የአዲስ አበባሀገረ ስብከት በሱማሌ ክልል በተፈጸመው የጭካኔ ግድያና የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎ አስመልክቶ ከገዳማትና አድባራት የሥራ ሓላፊዎች ጋር ውይይት አደረገ

                                                                     በ/ር ሣህሉ አድማሱ

በሀገራችን በምሥራቃዊ በሱማሌ ክልል በጅግጅጋ እና በሌሎች የአካባቢው ወረዳዎች በሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያነጣጠረ አሕዛባዊ ጥቃት ምክንያት ወገኖቻቸውን በሞት ላጡ እና ጭካኔ በተሞላበት ጭፍጨፋ አካላቸውን ለተጎዱት ምዕመናን ወቅታዊ ዕርዳታ ለመለገሥና በጥቃቱ በእሳት የተቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያናት መልሶ ለመገንባት አስፈላጊው እርዳታ እንዲደረግ በማሰብ ሀገረ ስብከቱ ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራትን የሥራ ሓላፊዎች ጋር ነሐሴ 22 ቀን 2010 ዓ.ም ለግማሽ ቀን የቆየ የውይይት ሥራ አከናውኗል፡፡

ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንደገለፁት ወገኖቻቸውን በሞት ላጡ እና ጭካኔ በተሞላበት ጭፍጨፋ አካላቸውን ለተጎዱት ምዕመናን ከሀገረ ስብከቱ ካዝና ብር 4 ሚሊዮን ወጭ አድርጎ የሰጠ ሲሆን በተጨማሪም እርዳታውን ከፍ ላመድረግ በማሰብ በሁሉም ገዳማትና አድባራት እንደየገቢያቸው መጠን ከካዝናቸው ወጭ አድርገው እንዲሰጡ በሀገረ ስብከቱ በኩል ስኩላር ድብዳቤ እንተጸፈ ብፁዕነታቸው አክለው ገልጸዋል፡፡የገዳማቱና የአድባራቱ የሥራ ሐላፊዎችም ከሀገረ ስብከቱ የተላለፈውን መመሪያ ተግባራዊ እንደሚደርጉ ስምምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ  ጠቅላይ ቤተ ክህነት ካቋቋማቸው የዕርዳታ  አሰባሳቢ ኮሚቴዎች መካከል አንዱ የሆኑትና የሲኤሚሲ ቅዱስ ሚካኤል ደብር አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ዘካርያስ ሐዲስ ሰሞኑን ጅግጅጋ እና በአካባቢው በሚገኙ ወረዳዎች ሂደው በአብያተ ክርስቲያናቱ መቃጠል፣ በምዕመናን የግፍ ግድያና ከባድ የአካል ጉዳት ዙሪያ በዐይናቸው የተመለከቱትን ለጉባኤው አስረድተዋል፡፡ መልአከ ምሕረት አክለው እንደገለፁት አሠቃቂ ጥቃት የፈጸሙት የጥፋቱ መልእክተኞች ጥፋቱን ካደረሱ በኋላ የተቀመጡበት ተሽከርካሪ (መኪና) ተገልብጦ ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል፡፡ መልአከ ምሕረት አክለው እንዳብራሩት እግዚአብሔር የእርምጃ አጸፋውን ወዲያውኑ እንዳከናወነ ያሳያል ብለዋል፡፡

የውይይቱ የትኩረት አቅጣጫ የተመሠረተው በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል በኩል ተዘጋጅቶ የቀረበው  ቪዲዮ በአስረጅነት እንደተገለፀው በርካታ ካህናትና ምዕመናን በሰይፍ ተሰይፈዋል፡፡ በእሳት ተቃጥለዋል፣ የንብረት ዝርፊያ ተፈጽሟል፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት የቤንዚን ነዳጅ እየተደፋባቸው ለቃጠሎ ተዳርገዋል፣ የምዕመናን መኖሪያ ቤቶች በእሳት ወድመዋል፣ የሆስፒታል አልጋዎች በቁስለኞች ተጣበዋል፣ ክርስቲያኖች ሴቶች ተደፍረዋል፣ ባሎቻቸውና ልጆቻቸው የሰይፍ እና የእሳት ራት ሆነው የቀሩባቸው እናቶች ዐይኖች በዕንባ ተሞልቷል፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች ከቃጠሎ በተረፉት አብያተ ክርስቲያናት ግቢ ውስጥ ወልደው ተኝተዋል፡፡

ከአሠቃቂው የግድያ፣ የድብዳባ እና የቃጠሎ ድርጊት በኋለ በተከናወነው ጥናት መሠረት አሕዛቡ በተለያዩ ቡድናዊ አደረጃጀት ለእኩይ ድርጊታቸው የተጠቀሙት የተንኮል ስልት የመጀመሪያው ቡድን የክርስቲያኖችን ቤት ለይቶ በማጥናት የምልክት ቀለም መቀባት፣ ሁለተኛው ቡድን የዘረፋ ተግባር መፈጸም፣ ሦስተኛው ቡድን የግድያ ሥራ ማከናወን፣ አራተኛው ቡድን ክርስቲያን ሴቶችን መድፈር፣ አምስተኛው ቡድን አብያተ ክርስቲያናትን እና የክርስያኖችን ቤት ማቃጠል ሲሆን ሁሉም ቡድኖች እኩይ ሥራቸውን ከፈጸሙ በኋላ የሤራው ጠንሳሽ ለሆነው ክፍል ሪፖርት ማቅረብ ነበር፡፡ በቀረበው የቪዲዮ መረጃ እንደተገለፀው ጥፋቱ እንዲፈጸም ለጥፋት ኃይሎች ከሤራ ጠንሳሾቹ በኩል መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

የአሠቃቂውን የግድያ፣ የእሳት ቃጠሎ እና የጭፍጨፋ ቪዲዮ የተመለከቱ የገዳማቱና የአድባራቱ የሥራ ሐላፊዎች በመሰብሰቢያ አዳራሹ ውስጥ በዕንባ ተራጭተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተሰብሳቢዎቹ ቁጭት የተሞላበት ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ከቀረቡት የሐሳብ ነጥቦች መካከል የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ታካሚ ምዕመናን የአልባሳት፣ የገንዘብ፣ የመጠለያ እርዳታ በተቋቋመው ኮሚቴ በኩል ሊላክላቸው እንደሚገባ፣ የአእምሮ ቁስለኞች የሆኑትን ከቦታው ድረስ በመሄድ የማጽናናት ተግባር መፈጸም፣ የእርዳታው መጠን ከፍ እንዲል፣ ሁሉም ሠራተኛ የወር ደመወዙን እንዲለግሥ፣ ገዳማትና አድባራት ከካዝናቸው ወጪ አድርገው ተጨመሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ በየገዳማቱና በየአድባራቱ የሚሰራጨው የመታሰቢያ ካርድ ለምዕመናን እንዲሸጥ ብርቱ የቅስቀሳ ሥራ እንዲሠራ በማለት ሰፋ ያለ ውይይት ከተደረገ በኋላ የእርዳታ ማሰባሰቡ ሥራ በተሻለ ሁኔታ እንዲጠናከር ለማድረግ ከሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሁለት ሁለት ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ የተወሰነ ሲሆን የኮሚቴዎቹም አደረጃጀት የሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ መሪዎች የኮሚቴው አካል እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም ከሰባቱም ክፍላተ ከተማ ገዳማት እና አድባራት አንድ አንድ ሰው ተጨማሪ ኮሚቴ ሆኖ እንዲመረጥ ተሰብሳቢ ጉባኤው በመስማማቱ

  1. ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቃሊቲ ገብርኤል ቤ/ክ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም አባ ገ/ሚካኤል
  2. ከላፍቶ ክፍለ ከተማ መ/ር በቃሉ የላፍቶ መድኃኔዓለም ቤ/ክ አስተዳዳሪ
  3. ከቦሌ ክፍለ ከተማ ሊቀ ብርሃናት ተክለማርያም የቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም ቤ/ክ አስተዳዳሪ
  4. ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ሊቀ ማእምራን ለይኩን የደብረ ይድራስ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ አስተዳዳሪ
  5. ከአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ መልአከ አርያም አምደወርቅ የጽርሐ አርአያም ቅ/ሩፋኤል ቤ/ክ አስተዳዳሪ
  6. ከአዲስ /ልደታ/ክፍለ ከተማ መልአከ ገነት አባ ገ/ሥላሴ የደብረ መዊእ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ አስተዳዳሪ
  7. ከየካ ክፍለ ከተማ መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ኢየሱስ የኮተቤ ቅዱስ ገብረኤል ቤ/ክ አስተዳዳሪ ተመርጠዋል፡፡

በመጨረሻም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተጀመረው የነፍስ አድን ጥሪ እጅግ ታላቅ ሐላፊነት እንደመሆኑ መጠን ለዕርዳታ ማሰባሰብ ሥራ ሐላፊነት የተጣለባቸው የኮሚቴ አባላት በትጋት፣ በቅንነት እና በታማኝነት የተጣለባቸውን ከባድ ሐላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡

እንደዚሁም ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶችና ምዕመናንም አቅማቸው የፈቀደውን ያህል የገንዘብም ሆነ የሐሳብ ድጋፋቸውን ሊያደርጉ ይገባቸዋል እንላለን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *