የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ መመራቱን ተከትሎ የመጀመሪያውን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሊያካሄድ ነው

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ምሥረታን ታሪካዊ ደኃራ በተመለከተ በሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የመሪነት ዘመን እንደተጀመረና የኢትዮጵያው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልትመራና ልትተዳደር የምትችለው በሰበካ አስተዳደር ጉባኤ መሪነት መሆኑን በነበራቸው አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት አስበውና አቅደው አገልጋዮች ካህናትና በእምነቷ ሥር ያሉት ምእመናን የሚመሩበትንና የሚተዳደሩበትን የሰበካ አስተዳደር ጉባኤን አቋቁመውና የቃለ አዋዲን ሕግ በመንፈሳዊ ምሁራን አስረቅቀው ማለፋቸውን የታሪክ ሰነዶችና አበው ምስክሮች ናቸው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አካል የሆነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሁሌም በወርኃ ጥቅምት በሚካሄደው አጠቃላይ ዓመታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ተሳትፎው የጎላ ቢሆንም ራሱን ችሎ የራሱን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ግን ሳያካሄድ ቆይቷል።
ነገር ግን በዚህ ዓመት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወርኃ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ባካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለውን ብልሹ አሠራርና የመልካም አስተዳደር እጦት ለማስተካከል በጥልቀት ተወያይቶና ሕገ ቤተ-ክርስቲያኑን አሻሽሎ እንደሌሎቹ አህጉረ ስብከቶች ግልፅ በሆነና ያለማንም ጣልቃ ገብነት ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የመሪነት ዘመን ከየካቲት 19 እስከ 20/2013 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የሚካሄድ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሊያካሄድ ነው።
የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው በጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ላይ ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት የየክፍሉ ኃላፊዎች፣የሰባቱ ክፍላተ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች፣የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ምክትል ሊቃነ መናብርት የሚገኙ ሲሆን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ፣የልማት ሥራዎች፣አስተዳደራዊ ጉዳዮችና መሰል አጀንዳዎች በጉባኤው እንደሚዳሰሱ ይጠበቃል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ