የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የ12 አቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች እድሳት ሊያካሄድ ነው

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እድሳቱን የሚያካሂደው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ነው።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ ለእድሳት መርሐ ግብሩ አንድ ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ ሀገረ ስብከቱ በአገራችን የተለያዩ ችግሮች ሲገጥሙ መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል።
የ12 አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን እድሳት ለማከናወን ሙሉ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም ጠቅሰዋል።
ሀገረ ስብከቱ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር የበጎ ፈቃደኝነት ሥራዎች ላይ እንደሚሳተፍም አብራርተዋል።
ሀገረ ስብከቱ ከምእመናን ከሚያገኘው ገንዘብ መልሶ ለምእመናን የሚሆኑ የልማት ሥራዎችንና የኢኮኖሚ ድጋፎችን ማድረጉ የሚበረታታ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ለመስጠት ርኅሩኅ ልብ ያስፈልጋል” ብለዋል።
” እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና “(ማቴ 7:12) የሚለውን መለኮታዊ ቃል በመጥቀስ ለሌሎች መልካም ማድረግ የተቀደሰ ሥራ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢኮኖሚ አቅመ ደካማ ለሆኑት ካለን ላይ አካፍለን መስጠት መንፈሳዊ ግዴታችን ነው ብለዋል።
ባልጀራን እንደ ራስ በመውደድ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ መንፈሳዊ ደስታና የአእምሮ እርካታ ይሰጣል ሲሉ ጠቅሰዋል።
ብፁዕነታቸውም ለአንድ አቅመ ደካማ እናት በየወሩ ሁለት ሺህ ብር ለአንድ ዓመት የሚሆን 24 ሺህ ብር ከራሳቸው ድጎማ አድርገዋል።
የቤቶቹ እድሳት እስኪከናወን ለተቀሩት ለአስራ አንዱ አባ ወራና እማ ወራ ለእቃ ማጓጓዣና ለእገዛ የሚሆን ለእያንዳንዱ 1800 ብር ልገሳ ተደርጓል።
ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱ ይህንን እገዛ ሲያደርግ የመጀመሪያው አይደለም ብለዋል።
ከዚህ በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጽ/ቤት በቀድሞው ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጊዜ አስር ሚሊዮን ብር ለተማሪዎች ምገባና ለትምህርት መሣሪያ መሟላት ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
አክለውም በትግራይና በቤንሻንጉል በተከሰቱት ችግሮች ምክንያት ለተጎዱት ማሕበረሰብ ሀገረ ስብከቱ አስራ አምስት ሚሊዮን ብር እና ሌሎችንም ድጋፎችን ማድረጉን አውስተዋል።
የእድሳት መርሐ ግብሩን ብፁዕነታቸው አስጀምረዋል።
በቦታው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሥራ ኃላፊዎችና የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት የመንግሥት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *