የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ያለፈውን የበጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትንና የመጪውን የበጀት ዓመት ዕቅድ እየገመገመ ይገኛል

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ያለፈውን የ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትንና የመጪውን የ2014 ዓ.ም የበጀት ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ በመገምገም ላይ ይገኛል።
በአዲስ አበባና በጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መመሪያ ሰጭነት ከሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የግምገማ መርሐ ግብሩ በመካሄድ ላይ ነው።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ እንዲመራ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በኃላፊነት ወደ ሀገረ ስብከቱ ከመጡ ጀምሮ ለዕቅድ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በዕቅድ እንደተከናወኑ ተገልጿል።
በብፁዕነታቸው መመሪያ ሰጭነትም ለሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ በተጨማሪም ለሰባቱ ክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጆችና የሥራ ኃላፊዎች ዕቅድን በተመለከተ “የዕቅድ ዝግጅት እና አፈጻጸም እንዲሁም ክትትልና ግምገማ” በሚል ርዕስ ታህሳስ 13/2013 ዓ/ም በባለሙያ የተደገፈ ሥልጠና መሰጠቱ የሚታወስ ነው።
ከሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች መካከል፦ የዕቅድና ልማት፣ የሂሳብና በጀት፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ፣የሰው ኃይል አስተዳደርና የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ ሪፖርትና ዕቅድ እንዳቀረቡ ተገልጿል።
ቀሪዎቹ የዋና ክፍል ኃላፊዎችም በቀጣይ ባሉት ቀናት ውስጥ እንደሚያቀርቡ ተነግሯል።
የቀረቡት ሪፖርቶች፦ በበጀት ዓመቱ ታቅደው የተፈጸሙ እና ያልተፈጸሙ ተግባራትን፤ ያጋጠሙ ችግሮችንና እና የተወሰዱ መፍትሔዎችን ያካተቱ መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡
የ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ስኬታማና ውጤታማ እንደሆነ ከቀረቡት ሪፖርቶች መረዳት ተችሏል።
ለመጪው 2014 ዓ.ም የበጀት ዓመት የታቀዱ ዕቅዶችም ለሀገረ ስብከቱም ሆነ ለቤተክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተጠቁሟል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
የዜናው ምንጭ፦ የሀገረ ስብከቱ አይቲና ዶክመንቴሽን ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ር ዘሩ ብርሃኔ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published.