የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ 8ኛ ዓመት በዓለ ሲመት ተከብረ!!!

የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳስት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፡ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፡ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፡ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፡የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በርካታ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ካህናት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በጸሎት፡በዝማሬና ትምህርተ ወንጌል በድምቀት ተከብሯል፡፡

በመርሐግብሩ ላይ አጭር ሪፖርት ያቀረቡት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና የተከናወኑ ሐዋርያዊ ክንውኖችንና የልማት ሥራዎችን ገልጸው፡የዛሬው ክብረ በዓል የቤተ ክርስቲያን በዓል ነውና እንኳን ለዚህ ትልቅ ዕለት በሰላምና በጤና አደረስዎት ብለዋል፡ቀጣዩን በዓለ ሲመትም በተሻለ መልኩ ይከበር ዘንድ መልካሙን ዘመን ተመኝተዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳስት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ይህ ዓመት ቤተ ክርስቲያናችን በትልቅ መከራ ያለፈችበት በብዙ ወገኖቻችንም ላይ ሞትና የአካል መጉደል እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የሀብትና ንብረት ውድመት የደረሰበት ዓመት በመሆኑ ሁላችንም በሀዘን ውስጥ እንገኛለን ብለዋል፡፡

አያይዘውም በዛሬው ዕለት በማክበር ላይ የምንገኘው የቤተ ክርስቲያን በዓል ከተለመደው በተለየ መልኩ መሆኑንን ገልጸው፡ ለዚህ በዓል ተብሎ የተበጀተው በጀትም የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት እንዲውል መወሰኑንም አሳውቀዋል፡ በመጪውም ዐብይ ጾምም በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን በመርዳትና በመደገፍ ሱባኤውንና ጸሎተ ምኅላውን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *