የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከትናንት እስከ ዛሬ ለሀገር ግንባታ ያበረከተችው አስተዋጽኦ የማይተካ ሚና እንዳለው የሚገልጽና መልካም አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚያትት ሥልጠና በልደታ፥ ቂርቆስና አዲስ ክፍለ ከተማ ተሰጠ!

በአራዳና በአቃቂ ክፍላተ ከተማ በተከታታይ ሲካሄድ የቆየው የ39ኛው የሰበካ ጉባኤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከትናንት እስከ ዛሬ ለሀገር ግንባታ ያበረከተችው አስተዋጽኦ የማይተካ ሚና እንዳለው የሚገልጽና መልካም አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚያትት ስልጠና ዛሬም በልደታ፥ ቂርቆስና አዲስ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት አስተባባሪነት በደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ቀጥሎ ውሏል።
በዛሬው ዕለት መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም መ/ር አካለወልድ ተሰማ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፥ ላዕከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ፣ መ/ብርሃን ሳሙኤል ደምሴ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ፥ የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ምክትልና ጸሐፊ፥ የልደታ፥ ቂርቆስና አዲስ ከፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ(ቆሞስ) ፥ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በአዲስ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኙ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ዋና ጸሐፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሒሳብ ሹሞች፣ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች፥ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች እና የእስታስቲክስ ሠራተኞች በተገኙበት በልደታ፥ ቂርቆስና አዲስ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት አስተባባሪነት በደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተካሂዷል።
ክቡር መ/ር አካለወልድ ተሰማ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሥልጠናው አስመልክተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሥልጠናው በሀገረ ስብከቱ በኩል በተደረገ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መነሻነት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገረ ስብከታችን አየተሰጠ ያለ ሥልጠና ስለ ሆነ ታሪካዊ ስብሰባ/ሥልጠና ነው ብለዋል። ከዚህ ጋር አያይዘውም ከጉባኤተኛው የሚገኘው ሓሳብ ለሀገረ ስብከቱ መልካም የሥራ ለውጥ ትልቅ ሚና ስለሚኖረው ገንቢ የሆነ ሐሳባችሁን እንድታጋሩን እንፈልጋለን ብለዋል።
መርሐ ግብሩ በመ/ብርሃን ሳሙኤል ደምሴ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ እየተመራ በመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ምክትል የሆኑት ሊቀ ስዩማን ወልደ ሰንበት አለነ “መልካም አስተዳደር በቤተክርስቲያን አስተምህሮ” በሚል ርእስ ዳሰሳዊ ጽሑፍ ቀርቧል። ዳሰሳዊ ጽሑፉ የመልካም አስተዳደር ምንነት፥ የመልካም እረኛ ተልእኮ እና በርከት ያሉ መልካም እረኛ የሚያካትታቸው ጉዳዮችንና የመልካም አስተዳደር እጦት የሚያስከትለው ችግር ዳስሰዋል።
በመቀጠልም ሊቀ ካህናት ቁሙላቸው ደርሰህ በመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ጸኃፊ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አደረጃጀት የተዘጋጀ የገንዘብና ወጪ ቅጽ ቀርቦ ማብራርያ ተሰጥቶበታል።
በማስከተልም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ግንባታ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ከትናንት እስከ ዛሬ የሚል ዳሰሳዊ ጽሑፍ በላዕከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ቀርቧል። በዳሰሳዊ ጽሑፉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና አስተዳደር፥ ፊደል፥ ካላንደር፥ የማኅበራዊና የመንፈሳዊ፥ የግብረ ገብነት ትምህርት ወዘተ አዘጋጅታና አሰናድታ በማቅረብ ሀገርን እንደ ሀገር እንድትቀጥል ያደረገችው አስተዋጽኦ የማይተካ ሚና መጫወትዋን ተብራርቷል።
ከዚህ በተያያዘም ስለ ሀገርንና ነገሥታት ዘወትር በጸሎት እየተጋች ሀገርን እንደ ሀገር ሊስቀጥላት የሚችል በመሠረተ ልማት፣ በኢኮኖሚው ዘርፍና ለሰላም ዘብ በመቆም ያበረከተችውን አስተዋጽኦም ዘመን የማይሽረው ሚና መሆኑን ተገልጿል።
ሥልጠናው ካለቀ በኋላ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን፡ ከተሳታፊዎች ሥልጠናው መዋቅሩን ጠብቆ ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ለሁሉም ቢሰጥና ችግሮችን ለመፍታት ከበላይ አካላት ውይይት ቢደረግ ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሥልጠናው ችግሮች ባሉበት ቦታ እየተለየ ቢሰጥ የሚል አስተያየትም ቀርቧል።
በመጨረሻም የዕለቱ የአቋም መግለጫ ተነብቦ መርሐ-ግብሩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ መ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *