የእመቤታችን የቅድስት ኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግሥ በእንጠጦ ሐመረ ኖኅ ቅ/ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በድምቀት ተከበረ

ዛሬ የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ/ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ ፣ የገዳሙ አስተዳዳሪ ጸባቴ አባ ወልደ ማርያም አድማሱ ካሳዬ(ቆሞስ)፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አለቆች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ክፍል ኃላፊዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና እጅግ በርካታ ምእመናን በተገኙበት በእንጠጦ ሐመረ ኖኅ ቅ/ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም የቅድስት ኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግሥ በድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ ሌሊት በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በሥርዓተ ማኅሌት፣ በብፁዕነታቸው እየተመራ ጸሎተ ኪዳን የደረሰ ሲሆን ጠዋት በመድረኩ በሊቃውንት “አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት” የሚልና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የአጫብር ዝማሬ በድምቀት ቀርቧል።

በመቀጠልም የገዳሙ አስተዳዳሪ ጸባቴ አባ ወልደ ማርያም አድማሱ ካሳዬ(ቆሞስ) በበዓሉ ለተገኙ ምእመናን እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ለበዓሉ በሰላም አደረሳችሁ በማለት ገዳሙ በመንፈሳዊና ማሕበራዊ ልማት እየተጋ መሆኑን ገልጸዋል፤ በተለይ ደግሞ ባለፋ ሳምንታት በቅዱስ ፓትርያርኩ ተባርከው የተመረቁ ህንጻዎች እንደ ምሳሌ አንስተዋል። ባለፈው ከተመረቁ ህንጻዎች አንዱ “ሐመረ ኖኅ ቤተ አብርሃም” መባሉን በማውሳት አሁን ደግሞ G+4 የአረጋውያን ማረፊያ ትልቅ ህንጻ ለመገንባት ማቀዳቸውንና በቅርብ ቀን ግንባታውን እንደሚጀምሩት ለምእመናኑ አብስረዋል።

በማያያዝም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከሌሎች ብፁዓን አባቶች በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሐመር ተገኝተው 630 ኢአማንያን አጥምቀው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን መልሰው እንደ መጡ በማብሰር በዛው ወደ መድረኩ ጋብዘዋቸዋል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅም “አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት፤ አዳምቼ ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነሽ” በሚል ርእስ በዓሉን በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት አስተምረዋል። አዳም ሲፈጠር ብቻውን ነበረ፣ አምላክ ግን አዳም ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም በማለት የምትረዳው ሔዋንን ከጎኑ አጥንት ፈጠረለት/ አመጣለት አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ሲል ሔዋን አላት፣ ሁለቱም በገነት ይኖሩ ነበር ነገር ግን መልካምን ሁሉ የሚጠላ ዲያብሎስ በነፍሳቸው ጥርጣሬን በመዝራት እንዳሳሳታቸውና በዚህ ምክንያት ከገነት እንደ ወጡ ለዚህ ዋና ምክንያት ደግሞ የእዚአብሔርን ትእዛዝ በማፍረሳቸው እንደነበረ አብራርተዋል።

እግዚአብሔር ግን በባሕርየ ፍቅሩ አዳምን አሰበው፤ ለዚህም ደግሞ አዳም ከገነት ሲሰደድ ተስፋው አንቺ ነሽ እንደተባለው እመቤታችንን ምክንያተ ድኂን በማድረግ በእመቤታችን ምክንያት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእርሷ ተወልዶ ዓለሙን ሁሉ አድኗል ብለዋል።

አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነሽ እንዳለው ተስፋውና ቃል ኪዳኑ ለሰው ልጆች ሁሉ ነው፣ እመቤታችን የሁላችን እናት ናት፣ ከእርሷ የተወለደው ጌታ የዓለም ሁሉ መድኃኒትነውና ብለዋል።

በመጨረሻም የስም አማኞች ብቻ ሳንሆን እምነታችን በተግባር የምንገልጽ፣ ሕጉንና ትእዛዙን የምንጠብቅ መሆን እንዳለብን በማሳስብ የቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎትና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን ብለው ወደ ቅዳሴ አምርተዋል።

ብፁዕነታቸው ሥርዓተ ቅዳሴውን በመምራትና በመቀደስ ምእመናኑን አቁሩበዋል። በዛውም በጸሎትና ቡራኬ ህዝቡን በመሸኝት የበዓሉን ፍጻሜ ሆነዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *