የኦርቶዶክሳዊ አገልግሎታችን ልዕልና እንመልስ በሚል ርእስ የጽሁፍ ዳሰሳ ቀረበ

በዛሬ ዕለት በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አዳራሽ፣ የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣  የሀ/ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሐዋርያዊ ተልእኮና ስብከተ ወንጌል መምሪያ ምክትል ኃላፊ፣ የሀገረ ስብከቱ ክፍል ኃላፊዎች፣ የየካና ቦሌ ክፍላተ ከተማ አስተዳዳሪዎች፣ ስብከተ ወንጌል ኃላፊዎችና ሰባክያን በተገኙበት በመ/ር ግርማ ባቱ የተዘጋጀ የኦርቶዶክሳዊ አገልግሎታችን ልዕልና እንመልስ በሚል ርእስ የጽሁፍ ዳሰሳ ቀርበዋል።

በዝግጅቱ በአገልግሎታችን ዙሪያ የሚስተዋሉ ወቅታዊ ችግሮችን በመዳሠሥ ከቀደሙ የስኬት ታሪኮቻችን የሚመነጩ የመፍትሔ አሳቦችን ለመጠቆም ነው በማለት የቀደመ በጎ ታሪካችን እንመልስ የሚል መልክት ያዘለ ነበር።  ከቀደሙ ስኬቶች መነሻቸውን አድርገው የሚሠሩ የማንሠራራት ሥራዎች የእርግጠኝነት ጥያቄ ከማስነሣት ይልቅ ከፍተኛ የሥነ ልቡና ስንቅ/ብርታት ይሆናሉ በማለት 13ኛው ክፍለ ዘመን “ማንሠራራት እንደ ምሳሌ ጠቅሷል።

 ያኔ የነበረ ከፍታ/ልእልና የማወቅ ቁልፍ ጥያቄ እንዳለበት መዘንጋት አያስፈልግምም ብሏል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምትገለጽባቸው መንገዶች አንዱም የትምህርት የአገልግሎትና የአስተዳደር ብቃት ነበራት ሲሉም እይታቸው አስቀምጧል። የትም ክፍለ ዓለም የሌለ የሁለት ኪዳናት ጥምረት፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሥሪትና በወቅቱ የነበረ የኢትዮጵያ አንድነት ምስጢር ሳያደንቁና ሳያወሱም አላለፉም።

በተጨማሪም ጥንታዊው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በማንሳት የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ (ባኮስ)፥ የቅዱስ ፍሬምናጦስና የተሰዓቱ ቅዱሳን ዓበይት አስተዋጽኦዎች በማውሳት የምሥረታ፥ መደራጀትና መሥፋፋት ዘመን (ከአንደኛው እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን) የነበረ የስብከተ ወንጌል ሁለንተናዊነትንና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርን ምንነት ያሳየ ፈር ቀዳጅ እንደነበረ፣ በወቅቱ ወንጌልን በመላዋ ኢትዮጵያ በሌሎች ግዛቶችም ጭምር እንደተስፋፋ ጠቁሟል።

በተጨማሪም በወቅቱ የተሠሩና ከዓበይት አስተዋጽኦዎች የተወሰኑ ጠቅሷል። ከነሱም የተወሰኑት ሥራዎች፡

 ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጻፍ በመተርጎም በሠፊው ማሠራጨት፣ ገዳማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማበራከት ፣ በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግሥት ጋር ለጋራ ጥቅም መሥራት፣ ኢትዮጵያዊ ርዕዮተ ዓለም መፍጠርና ማሥረጽ ፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ፥ ታላቅነትና ግርማ መሠረት የሆነ ሥራ መሠራቱ፣ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ከአማናዊ ምስጢራቱና ሁለንተናዊ ነገረ ድኅነቱ፣ ታሪክ ከሙሉ የማንነት ግንባታ መሠረታዊ ባሕርያቱ፣ መንፈሳዊ መሠረት ያለው ሥልጣኔ፣ ቋንቋ ከነሙሉ ሚናው፣ ትምህርት ከነሙሉ ዘይቤና ባሕሉ፣ ሥነ ጽሑፍ፥ ኪነ ጥበብ፥ ኪነ ሕንፃ፣ አገራዊ ስሜትና ፍቅር ያደጉበት ዘመን እንደነበረ አብራርቷል።

የአክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ (ሊቀ ጠበብት) ፅሑፍም በመጥቀስ፣  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከማንም ሐዋርያ ደም ንጹሕ ኾና ያለጸብና ክርክር እምነትን ተቀብላ በሙሉ ኢትዮጵያ ከጠረፍ እስከጠረፍ ስብከቷን አስፋፍታ የምግባርና የሃይማኖት አልማዝ የሆኑትን ፍቅርንና ትሕትናን መተዛዘንና መተባበርን እየሰበከች በመንፈሳዊ ክንፍ ትከንፍ ነበረች ሲሉም በዳሰሳዊ ጽሑፋቸው ገልጿል።

በመጨረሻም ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት እንደ መፍትሔ ብለው ከወሰድዋቸው ነጥቦች፡ –

መንፈሳዊነት ክርሰቲያኑ በሚኖርበት ባህል ታሪክና እና ትውፊት ውስጥ ትክክለኛ ማንነትን በማንፀበረቅ የተሻለ ሆኖ የሚገኝበትን አቅምና የሚያገኝበት ከፍተኛው የሰው ልጅ ደረጃ ነው፤ ሁሉን አቀፍና ለሁሉ ደራሽ አገልግሎትን ማጠናከር አለብን ብሏል።

ምን ማድረግ አለብን በሚለው ነጥብም፡

ዘመንን መዋጀት ከእኛ ካህናት የሚጠበቀው ትልቁ ቁምነገር ነው።  ̋ ቀኖቹ ከፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ̋ (ኤፌ 5፣16)፤ የቤተ ክርስቲያንን ባሕርያት አስተምህሮዋን፥ ባህሏንና ትውፊቷን የጠበቀ አገልግሎት ማቅረብ መቻል፤ ለትችቶችና ለብዙዎች መሠናከል ምክንያት ከሆነው ሥነ ምግባራዊ ድክመታችን ታርመን ሌሎችን መቅረጽ ወደምንችልበት ደረጃ ማደግ አለብን። ምእመናንን ባሉበት ሁኔታ ውስጥ መከታተል የሚችል አገልግሎት መቅረጽ አለብን በማለት ምክራቸውን ለግሷል።

የምዕራቡ ዓለም ተፅዕኖዎች መዋጋት አለብን ያሉት የጽሑፉ አቅራቢ፣

የምዕራቡ ዓለም የተለያዩ ተጽእኖዎች በተለያየ መልኩ ወደ ባህላችን እየተሰገሰጉ ነው። እነዚህ ሁሉ የተመለከትናቸው ቀስቃሾች በአገራችንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው አድናቂና ተከታይ አላቸው።  ጋብቻን የተመለከተ አስተሳሰብ፥ ጾታዊ ጉዳዮች፥ ተፈጥሮአዊ ክብር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሠዋል፣ ኢትዮጵያን የተመለከተ አንድ ጥናት ፍቺ 45% መድረሱን ይጠቁማል ሲሉ አብራርቷል።

ከእኛ የሚጠበቀው እጅግ ብዙ ነው ካሉ በኋላም፤ የዓለምን አሳብ ሁሉ የሚያፈርስና የላቀ፥ በመንፈሳዊነት የተገራ ዕውቀት ያስፈልገናል። እጅግ አሳሳቢ የሆነ የግንዛቤ እጥረትና የአቅም ማነስ የቤተ ክርስቲያናችንን ገጽታ ጎድቷል። ተደራሾችም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው።የዚህ ችግር መንስኤ ብዙ ስለሆነ ማጥራት ያስፈልጋል። በዕውቀት ዙሪያ የሚታየው ችግር ለስብከተ ወንጌል የሰጠነውን ዝቅተኛ ግምት ያሳያል።የሰባኬ ወንጌልነት ግልጽ መሥፈርት የለንም፤ይህም አሁን የሚታዩ የደረጃ መውረድ ችግሮች በግልጽ እንዲታዩ አድርጓል።የትምህርት ጭብጦች በግለሰብ ፈቃድ ላይ መመሥረታቸው በየዐውደ ምሕረቱ የተለያየ ሐሳብ እንዲንጸባረቅ መንገድ ከፍቷል ብሏል።

 አገልግሎታችንን በሠፊው ዕይታ ከዐውደ ምሕረትም በዘለለ ማሰብና ልዕልናን መመለስ ይቻላል ያሉት መምህሩ እንዲህ ካደረግን ደግሞ የአገልግሎት መስፋት በአገልጋዮች መካከል መፈላለግን ያመጣል። ለምእመናን ቤተ ክርስቲያን እንደ መከታ የምትቆጠርበትን ሁኔታ ይመልሳል።ትምህርት ቤቶችን ማብዛትና ማስፋት፥ የሕጻናት ማሳደግያ፥ አረጋውያን መጦርያ ፥ የምክር አገልግሎት መስጫ፥ ልማትን በአዲስ ቅኝት ይዞ በመቅረብና የሥራ ዕድልን በመፍጥር የቤተ ክርስቲያናችንን ተሰሚነት መመለስ ይቻላል በማለት ፅሑፋቸውን አጠናቋል።

ከተሰብሳቢዎቹም የተወሰኑ ጥያቄና ስለ ጽሁፉ የድጋፍና የይቀጥል ሐሳቦችን ቀርበዋል።

በአጠቃላይ የቀረበው ዳሰሳዊ ጽሑፍ እጅግ ጠቃሚ ነው፣ መነቃቃትን ይፈጥራል፣ እንዲህ ዓይነት ዳሰሳዊና ጥናታዊ ጽሑፎች በየወቅቱ ቢቀርቡ መልካም ነው እንላለን። በተለይ ወቅታዊ የሆነና መሠረታዊ የቤተክርስቲያን የሚዳስስ፣ የችግሩ መንስኤና መፍትሔ ከነ በቂ ማስረጃና እስረጂ ጥናት ታክሎበት ቢቀርብ፣ የመፍትሔ አቅጣጫዎችም በበሰለና ዘለቄታ ባለው መልኩ ተጠቁመው ለሚመለከተው አካል ቢቀርቡ መልካም ነው እንላለን።

ከሚድያ ክፍል

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *