የካህናት አገልግሎት፣ ኃላፊነትና ተግባር

የካህናት ኃላፊነትና ተግባር ቀድሞ መጻህፍተ ህግጋት ሳይጻፉ በብሉይ ሆነ በሐዲስ ኪዳን ከዘመነ አበው ጀምሮ እንደየዘመኑ አፈጻጸሙ ይለያይ እንጂ ሰፊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በመሠረቱ ክህነት፣ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ፣

 • በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ማገልገል፣
 • የአምልኮ ሥርዓት መፈጸምና ማስፈጸም፣
 • ሕዝብን መጠበቅና መምራት፣
 • ስለ ራስ፣ ስለ ሕዝብና ስለ ሀገር ጸሎትና መሥዋዕት ማቅረብ፣
 • ሕዝብን መጠብቅና መምራት፣

ማስተማር፣ በአጠቃላይ የእግዚአብሔር እንደራሴ መሆን ሕዝብን ለማገልግልና ለመጠበቅ፣ ሕዝባውያን ወይም ምዕመናን ሊፈጽሙዋቸው የማይችሉትን አገልግሎቶች ለማበርከት ከእግዚአብሔር ለተጠሩና ለተመረጡ ሰዎች የሚሰጥ መንፈሳዊ ኃይል እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ክህነት ከምንጩ ከመሰረቱና ከመገኛው፣ ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ሆኖ ሰማያዊና ምድራዊ መግቦትን ያካተተ ሐላፊነት ነው፡፡ ግብረ 6፡1-7፡፡ 20፡28፡፡ 1ኛ ጢሞ/4፡16፡፡ ጴጥ፡ 5፡2-4፡፡

ክህነት ለዚህ ታላቅ ሐለፊነት ለተዘጋጀና ለተጠራ ሰው የተሰጠ ሥልጣን ከሆነ፣ ካህንም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ይጠብቅና ያገለግል ዘንድ ከእግዚአብሔር የተጠራ እንጂ በሰው ልዩ ፍላጎትና ኃይል የሚሾም አለመሆኑን ማወቅና መረዳት ለአገልግሎቱም መዘጋጀት ግዴታ ነው፡፡

ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ወአንትሙኒ ጽንዑ ከመእብን መንፈሳዊ ወኩኑ ታቦተ መንፈሳዌ ለክህነት ቅድስት ወንጽሕት ከመታቅርቡ ወታዕርጉ መሥዋዕተ መንፈሳዌ ዘይሰጠወክሙ እግዚአብሔር በእደዊሁ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡፡›› ….ማለት፣ ‹‹እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መስዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ፡፡›› ያለው፣ 1ኛ ጴጥ፣ 2፡5-6፡፡

እንግዲህ ረዘም ያለ ታሪክ ያለውን ክህነታዊ የትምህርት አገልግሎት፣ በዘመነ አበው፣ በዘመነ ኦሪትና በዘመነ ሐዲስ በሚል ርእስ ለይተን አጠር ባለ መልኩ እንደሚከተው ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

1.    የክህነት አገልግሎት በዘመነ አበውና በዘመነ ኦሪት፡፡

በዘመነ አበው የክህነት አገልግሎት በቤተሰብ ሐላፊ አማካይንነት ይከናወን ነበር ማለትም አንድ ሰው የቤተሰብ ሐላፊ በመሆኑ ብቻ መስዋትን የማቅረብ ሥልጣን ሲኖረው በዘመነ ኦሪት ግን የክህነት አገልግሎት፣ በተለዩና ለዚህ አገልግሎት በተጠሩ ሰዎች ብቻ የሚከናወን ሆነ፡፡ ከኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 14 ላይ እንደምንረዳው፣ የሰላሙ ንጉሥ መልከ ጼዴቅ ስለ አሻሿሙ ምሥጢርና በዘመኑ ይፈጸም ስለነበረው የክህናት አገልግሎት ሥርዓት በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የተጻፈ መረጃ ባይኖርም፣ የልዑል እግዚአብሔር ካህን፣ የሰያሜ ካህናት የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ እንደቀረበ ግን እንረዳለን፡፡ ዘፍ፡ 14፡17-20፣ መዝ፡109/110፡4፡፡፣ ዕብ፡5፡6፡6፡20፡7፡1-22፡፡

መልከ ጼዴቅ ለአብርሃም የሰጠውን በረከት ስንመለከት ዛሬ ካህናት ለምዕመናን ለሕፃናት ለእናቶች የሚሰጡት በረከት ምን መሆን እንዳለበት እንድናስብ ይጋብዘናል፣ ከጦርነት ማግስት በረከት ያገኘው አብርሃምን ስናስብ ዛሬ ሰላም አጥተው ዕድገታቸው በሚቀጭ ሕፃናት፣ ደህንነታቸው ለማይጠብቅ እናቶች የምናቀርበው በረከት ምን እንደሚሆን እንድናጤን ያስገድደናል፡፡
ከላይ በተገለጸው መልኩ ያገለግል በነበረው በሥርዓተ አበው ምትክ ሥርዓተ ኦሪት በተሰራ ጊዜም ለክህነት አገልግሎት የሚመረጡ፣ ነውረ ሥራ የሌለባቸው (ያልተገኘባቸው) የአሮን ልጆችና የልጅ ልጆች ሆኑ፡፡ ዘሌ፡21፡16-24፡፡

የካህናተ ኦሪት፣ መደበኛ ሐላፊነት ተግባር፣ መስዋዕትን ማቅረብ ሆኖ፣ የበዓላት አከባበር ሥርዓትን መጠበቅና ማስጠበቅ፣ መጻሕፍተ ኦሪትንና ነቢያትን ማንበብና መተርጎም ቋሚ ሥራቸው ነበር፡፡
ካህናተ ኦሪት፣ የሕዝቡን ንጽሕናና ጤንነት ማስጠበቅም ከአገልግሎታቸው ዘርፍ አንዱ ነበር፡፡
1ኛ. ዘዳ፣ 28፡1-5፡፡            2ኛ. ዘኁ፡15፡40፡፡
3ኛ. ዘኁ፡18፡5             4ኛ. ዕዝ፡2፡63፡፡
5ኛ. 2ኛ፡ዜና፡መ፡15፡3፡፡        6ኛ. ኤር፡18፡18፡፡
7ኛ. ሕዝ፣ 7፡26፡፡            8ኛ. ሚክ፡3፡11፡፡

ካህናተ ኦሪት ሊቃነ ካህናትና ሌዋውያን በሚሉ ዐበይት መደቦች የሚከፈሉ ሲሆን፣ የሥራ መደባቸውም እንደየምድባቸው የሚከፋፈል ይሆናል፡፡
ካህናተ ኦሪት ሓላፊነታቸውና ተግባራቸው ከሁሉ የከበደ እንደሆነ ቢታወቅም ከጊዜ በኋላ ግን ዓላማቸውን ለውጠው በሰማያዊ ክብር ፋንታ ምድራዊ ክብርን ሽተው (ታይታ) ለተርእዮ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ሆነው ተገኝተው ስለነበር መድሐኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ዓለም በይቅርታ በጎበኘበት ወቅት የጸሐፍትንና የፈሪሣውያንን ከንቱነትና ግብዝነት ተመልክቶ በስምንት ዓበይት ነጥቦች መስሎ ወቅሶአቸዋል፡፡ ማቴ 23፡13-36፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ክህነታዊ ግዴታቸውን ወይንም የኖላዊነት ሓላፊነታቸውን ባልተወጡ ፈሪሣውያን ተግሣፁን በዚህ ሥእላዊ መግለጫ አሳየ እንጂ፣ ቀደም ሲል ሥርዓተ ኖሎት ሲጓደል፣ ሕዝቡ በመንፈሳዊም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወቱ ሲበድል እግዚአብሔር በተለያዩ ወቅቶች ካህናቱን ገሥጾአል፡፡ በነቢዩ በሕዝቅኤል የተነገረውን ቃል ስንመለከት ‹‹የማሠማርያዬን በጎች ለሚያጠፋና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው ይላል እግዚአብሔር፡፡ ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለማይጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል፡፡ በጎቼን በትናችኋል አባራችኋልም፣ አልጎበኛችኋቸውምም፡፡ እነሆ የሥራችሁን ክፋት እጎበኝባችኋለሁ ይላል እግዚአብሔር፡፡›› የሚል ሆኖ ስናገኘው፣ በሕዝቡና በካህናቱ መካከል ያለውን የመግቦትና የኖላዊነት ሥራ ሲጓድል የእግዚአብሔር ተግሣጽ ምን ያህል እንደሚበረታ እንረዳለን፡፡ ሕዝ፡34፡1-16፡፡

የካህናት ሓላፊነትና ተግባር በአዲስ ኪዳን

ከዚህ በላይ የተመለትነው የካህናተ ኦሪትን የክህነታዊ አገልግሎት አፈጻጸምን በአጭሩ ነበረ፡፡ ቀጥሎም የካህናተ ወንጌልን ጥሪ፣ የሥራ ሓላፊነትንና ተግባርን እንመለከታለን፡፡
የካህናተ ሐዲስ ሥልጣን እንደ ካህናተ ኦሪት በዘር የሚወረስ፣ በይገባኛል የሚገኝ መብት ሳይሆን አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ከማይሰፈር ብዕሉ ለሰው ልጅ በሰጠው ጸጋ መሰረት ጥሪውን ተቀብለው ለሐዋርያዊ አገልግሎት ለሚሰለፉ ሰዎች የተሰጠና የሚሰጥ፣ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ እናውቃለን እናምናለን፡፡ ሢመተ ክህነት ከሊቀ ካህናት ከኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የተሰጠ ጸጋና ሰማያዊ በረከት በመሆኑ፣ ድኅነተ ነፍስን ማስገኘት ካልተቻለው ከካህናተ ኦሪት የተለየ፣ ለካህናተ ኦሪት ያልተሰጠ ኃይልና ሥልጣን የተገኘበት ሰማያዊ ሐብት ነው፡፡

ካህን፣ ጠባቂ፣ መምህር፣ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም የእግዚአብሔር አገልጋይ፣ የሕዝብ መሪ አስተማሪ ኖላዊ መንፈሳዊ አባት ሆኖ የዓለምን ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመጥራት የተሰለፈ የእግዚአብሔር ሕግ አስፈጻሚ በመሆኑ ሓላፊነቱ ነፍስን የመጠበቅ ሓላፊነት ብቻ አይሆንም፣ በደዌ ሥጋ የሚፈርሰውን የእግዚአብሔርን ሕንፃ መጠበቅም ሓላፊነቱ ነው፡፡
ካህናት፣ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡ የሚለውን አምላካዊ አዋጅ ለመፈጸም ሥልጣን የተሰጣቸው የእግዚአብሔርን መንጋ ለመጠበቅ እንዲሰለፉ፣ ደዌ ሥጋንና ደዌ ነፍስን እንዲፈውሱ፣ ሙታነ ሥጋንና ሙታነ ነፍስን እንዲያስነሱ፣ አጋንንትን እንዲገዙ ኃይልና ሥልጣን የተሰጣቸው የክርስቶስ እንደራሴዎች፣ ይሕይወት ጎዳና መሪዎችና የመንግስተ እግዚአብሔር በረኞች ናቸው፡፡ ማቴ፡19፡19፡፡ 18፡18፡፡ 28፡19፡፡

ዛሬ የዚህ ሥልጣን በረከት ባለቤቶች የሆኑ፣ በዚህ ጸጋ የበለጸጉ ካህናት መንፈሳዊ ኃይላቸውን በሰው ሕይወት ላይ በሰለጠኑት ደዌያት ላይ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፣ ዛሬ በሰው ልጅ ድኅነት ላይ ማነቆ ሆኖ የሚታየው የኋላ ቀርነት ቀንበር ፈቺዎች እንዲሆኑ በተስፋ የሚጠበቁ የእግዚአብሔር መንጋዎች (የምእመናን) በረከት ናቸው፡፡ መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ዓሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ፣ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልንና ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ የእግዚአብሔርንም መንግስት እንዲሰብኩና ደዌዎችንም እንዲፈውሱ ላካቸው፡፡ ተብሎ መጻፉን እናውቃለንና ነው፡፡ ሉቃ፡ 9፡1-2፡፡

ካህናተ እግዚአብሔር ሰይፈ መንፈስ ቅዱስን አንግበው ቃለ ወንጌልን ተጫምተው ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ሊወጉ የተሰለፉ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው፡፡ ካህናት፣ በእግዚአብሔር ጥበብ የሠለጠኑ ሆነው ደዌ ሥጋንና ደዌ ነፍስን የሚፈውሱ የምዕመናን ሐኪሞች ናቸው፡፡  ወደ ዓለም የሚላኩት ካህናት ዓላማቸውን ለማስፈጸም ክህነታዊ አገልግሎታቸውን የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ ጥበብና የውሃትን ገንዘብ ማድረግ እንዳለባቸው ተነግሮአቸዋል፡፡ ‹‹ወናሁ አነ እፌንወክሙ ከመአባግዕ ማእከለ ተኩላት፣ ኩኑ እንከ ጠቢባነ ከመአርዌ ምድር ወየዋሃነ ከመርግብ ተብሎ ተጽፏል፡፡ መቴ፡10፡1፡፡ ሉቃ 10፡3፡፡

ይህን ታላቅና ከባድ ኃላፊነት የተሸከመ ካህን፣ በተኩላዎች መካከል ገብቶ፣ በጥበብና በየዋህነት እየተመራ፣

 • የእግዚአብሔርን መንጋ መጠበቅ
 • የጠፋውን መፈለግ
 • የባዘነውን መመለስ
 • የደከመውን ማጽናናት
 • የታመመውን ማከም
 • የተሰበረውን መጠገን
 • በጨለማው ዓለም የሚኖረውን ሕይወት በኢየሱስ ክርስቶስ የብርሃን ጉዳና እንዲመላለስ ማድረግ፣
 • አልጫውንና መራራውን ዓለም ለውጦ ማጣፈጥ ኃላፊነቱና ተግባሩ በመሆኑ ይህን ኃላፊነት ተወጥቶ የማያልፈውን የክብር አክሊል ለመቀዳጀት የሚያስችል ዓቅም ብቃትና ሙሉ ፍላጎት ይዞ መነሳት እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡ ሕዝ፡34፡1-31፡፡ 1ኛ፡ ጴጥ፡5፡2-4፡፡

ካህን የወገኖቹን ችግር ችግሩ ኃዘናቸውንም  ኃዘኑ አድርጎ ሲያዝኑ አዝኖ ሲያለቅሱ አልቅሶ ሲደሰቱ ተደስቶ በማጽናናቱ፣ በምክሩና በትምህርቱ የሻከረውን ልብ የሚያለዝብ ያዘነውንም የሚያጽናና የሥነ ልቡና መምህር ወይም ሳይኮሌጂስት ነው፡፡ ሮሜ፡12፡15፡፡ መዝ፡34፡13-14፡፡
ካህን መምህረ ሕግ ወሥርዓት ከመሆኑም ሌላ ለሚጠብቀው መንጋ ራሱን አሳልፎ የሰጠ በመሆኑም የሚያስበውና የሚጨነቀው ስለሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወት ብቻ አይደለም፡፡ ዘእንበለ ሥጋ ኢትቀውም ነፍስ መባሉ ለእንዲያው አይደለምና ሰው ነፍስና ሥጋውን ማኖር የሚስችለውን ጥረት ልማት እንዲያደርግ ሥጋዊና መንፈሳዊ መግባባቱን ለማረጋገጥ ማስተማር ሓላፊነቱና ግዴታው ነው፡፡ ዘፍ፡2፡15፡፡ 3፡19፡፡ ኩፉ፡4፡9፡፡ 5፡7፡፡ ማቴ፡5፡13-16፡፡

የእውነተኛ ዕረና መመዘኛ ነጥቦች

የክህነት አገልግሎት ሰማያዊና ምድራዊ መግቦት ከሆነ ለዚህ ከባድ ኃላፊነት ብቁ ሆኖ ቸር ጠባቂና ታማኝ የክርስቶስ አምባሳደር እኔ ነኝ ብሎ በልበ ሙሉነት የሚቀርቡ ሰው እሱ ማነው ቢባል ሁኔታው ከባድ ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን ቅ/ጳውሎስ በዚህ ሐዋርያዊ አገልግሎት ለመሰለፍ መመኘት ከሁሉ የበለጠ መልካሙን ሥራ መመኘት መሆኑን ስለ አንቀጸ ካህናት በጻፈው መልእክቱ፣ ‹‹እሙን ነገር ዘይፈቅድ ይሠየም ጳጳስ ሠናየ ግብረ ፈተወ፡፡›› ካለ በኋላ ለክህነት አገልግሎት የሚሰለፍ ሰው፡-

 1. ዘአያደሉ ለገጽ፡፡ በፍርድ በብያኔ፣ በጸሎት፣     አይቶ የማያዳላ፡፡
 2. ዘኢያፈቅር ንዋየ፡፡ ኃላፊውን ነብት የማይወድ፣
 3. መፍቀሬ ነገድ ወዘሠናይ ምግባሩ፣
 4. ዘአንጽሐ ርዕሰ ጻድቅ ወኄር፣
 5. ዘምሁር ቃለ ሃይማኖት መምህር ወመገሥጽ በትምህርተ ሕይወት ወይዘልፎሙ ለእለ ይተዋስኡ በማለት መመዘኛዎቹን አስቀምጦአቸዋል፡፡ 1ኛ ጦሞ፡3፡1-7፡፡ ቲቶ 1፡5-9፡

የአንድ ካህን ዋና ዓላማውና ተግባሩ የወንጌል ገበሬ ሆኖ መንግስተ እግዚአብሔርን ለመስበክ መሰለፍ ነው፡፡ ስለሆነም የሚከተሉትን መርሖች ቀዳሚና ቋሚ መርሕ አድርጎ መንቀሳቀስ፣ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

1.    የወንጌል አገልግሎትን አውቆ ማሳወቅ

የወንጌል አገልጋይ፣ ሐዋርያ፣ ካህን፣ የሚል ክብር የተሰጠው ሰው፣ የወንጌልን መሠረተ ሐሳብ በሚገባ ሲያውቅ በቂ አገልግሎት ማበርከት ይችላል፡፡ ለትምህርተ ወንጌል መስፋፋት ወሳኙ ኃይለ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኃይለ እግዚአብሔር በሰባኪው ላይ አድሮ ሥራውን እንዲሰራ ግን ፈቃደ እግዚአብሔር ከመጠየቅ ጋር ከአንድ መምህር ወንጌል ከሚፈለጉ በርካታ ቁም ነገሮች ጥቂቶቹን ብናስታውስ፣ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡እነዚህም፡-

 1. የሰባኪውን ችሎታና ብቃት ማጠናከር፣
 2. ለመልካም ሥነ ምግባር ራስን ማስገዛት፣
 3. አርአያ ክህነትን ማክበር (መከተል)
 4. የሰማዕያንን (የተሰባክያንን) ዓቅም መመጠን፣
 5. ርእስን ጠብቆ ማስተማር መቻል፣
 6. ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣
 7. ምስጋናንና ተግሣጽን ለይቶ መጠቀም፣
 8. የሚሰጠው ትምህርት በዝግጅት ሆኖ ለሁሉም ግልጽ እንደሚሆን ማረጋገጥ፣
 9. ወቅትን የተከተለ ገላጭ ምሳሌን መጠቀም፣
 10. ቃለ ወንጌልን ከውዳሴ፣ ከንቱ፣ ከአጓጉል ነቀፋ ነፃ በሆነ መልኩ ማስተላለፍ እንጂ ጥላቻን አለመቀላቀል፣ ራስንም አለመስበክ፣ የሚሉ ናቸው፡፡

3ኛ መልካም ሥነ ምግባር፣

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ላይ እንዲገኝ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ከታመነበት ይልቁንም፣ ለዚህ አብነት መሪና ፊታውራሪ ሆኖ መገኘት ያለበት መምህረ ወንጌል ነው፡፡ አንድ ሐዋርያ ወይም አንድ ካህን አርአያነቱ ምን ያህል ለምዕመናን ጠቃሚ እንደሚሆን ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩን ጢሞቴዎስን ሲመክር እንዲህ ብሎአል፡፡ ‹‹ከመዝ መሀር ወገሥጽ፤ ወአልቦ ዘያስተአብዳ ለውርዙትከ፤ ወኩኖሙ አርአያ ወአምሳለ ለመሃይምናን በቃልከ፣ ወበምግባሪከ፣ በፍቅር ወበሃይማኖት ወበንጽህ፡፡ እንዋዲህ ምከር አስተምር ሕፃንነትህን የሚንቃት አይኑር፤ በቃልህም በሥራህም ለመሃይምናን አርአያ ምሳሌ ሁናቸው፡፡

በፍቅር በሃይማኖት በንጽሕናም፡፡… ዘንተ አንብብ ወበዝ ሀሉ ከመ ይትዐወቅ ስላጤከ በኩለሄ፡፡……. ይህን አንብብ በዚህ ጸንተህ ኑር፤ ፍጹምነትህ በሁሉ ይታወቅ ዘንድ፡፡ ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰማህንም ታድናለህ፡፡ 1ኛ/ ጢሞ፡ 4፡11-16፡፡ የወንጌል ዓላማዋና አገልግሎት፣ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ጨለማው ዓለም በብርሃን እንዲመላለስ፣ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ሆኖ የእግዚአብሔርን መንግስት ወራሽነቱን እንዲያረጋግጥ ማድግ ነው፡፡ መራራው ዓለም በቃለ ወንጌል ጣፍጦ ጣዕም እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው፣ በጨለማው ዓለም ብርሃን የሚበራው፣ አልጫውን ዓለም ለማጣፈጥ የተሰጠውን ሰማያዊ ጸጋ በአግባቡ መጠቀም የሚችል ሐዋርያ ሲኖር ነው፡፡

በሰባኪውና በተሰባኪው መካከል የዓላማ አንድነት፣ መግባባትና መተማመን ሲኖር፣ የወንጌልን አገልግሎት የሰመረ ያደርገዋል፡፡ የመምህረ ወንጌል መንገድ ቀና ከሆነ ምዕመናንም፣ ከተንኮል፣ ከቂም፣ ከበቀልና ከክፉ ነገር ሁሉ ርቀው ወደ እግዚአብሔር በምታደርሳቸው ጎዳና የመጓዝ ዕድል ያገኛሉ፡፡ በጠባቂው በመንጋው መካከል መግባባት መደማመጥና መተማመን ካለ ሐዋርያው፣ ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት ሲል፣ ምእመናንም፣ ምንተ ንግበር ይላሉ፣ መምህረ ወንጌሉ፣ ግብሩኬ እንከ ፍሬ ሠናየ ዘይደልወክሙ ለንስሓ ወትነሥኡ ጸጋሁ ለመንፈስ ቅዱስ፣ ሲል ሕዝበ ክርስቲያኑም ልባቸው ይከፈታል፡፡ ኦሆ፣ እሺ በጀ የሚለውን ቋንቋ የአፍመፈቻ ቋንቋቸው ያደርጋሉ፡፡ አንደበታቸው ለጸሎት እጃቸው ለምጽዋት የተዘጋጀ ይሆናል፡፡ እንዲህ ሲሆንም የወንጌል አገልግሎት የሠመረ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ግብ፡ሐዋ፡2፡37-40፡፡ ምዕ፡3፡19፡፡

4ኛ/ በወንጌል አገልግሎት አለማፈር

በማንኛውም ሥራ ውጤት ማስገኘት የሚቻለው አምነውበት ሲሰሩ ነው፡፡ ይልቁንም ትምህርት ወንጌል፣ ፍጹም የሆነ መጥዎተ ርእሰን ይጠይቃል፤ ለዚሁም ቅዱስ ጳውሎስ የሚከተለውን ያስተምረናል፡፡

 • ‹‹እስመ ኢየኃፍር ምህሮ ወንጌሉ እስመ ኃይሉ ለእግዚአብሔር ውእቱ ዘይሐይዎሙ ለእለ የአምኑ ቦቱ፡፡ ወንጌሉን ማስተማርን አላፍርም፤ የእግዚአብሔር ኃይሉ ስለሆነ ያመኑበትን ሁሉ የሚያጽናናቸው፡፡›› ሮሜ፡1፡16፡፡
 • ‹‹እስመ አኮ መንፈሰ ፍርሐት ዘወሀበነ እግዚአብሔር ዘእንበለ መንፈስ ኃይል ወንጽሕ ወተፋቅሮ ወጥበብ፡፡ እግዚአብሔር የፍርሐት መንፈስን የሰጠን አይደለም የኃይል፣ የንጽሕና የፍቅር የጥበብ መንፈስን እንጂ፡፡ እንግዲህ ለጌታችን ስለመመስከር አትፈር፣ እኔንም እስረኛውን አታሳፍረኝ፣ በእግዚአብሔር ኃይል ለማስተማር ድከም እንጂ፡፡ ‹‹ 2ኛ/ ጢሞ፣ 1፡7-8፡፡

5ኛ/ የሰማዕያንን ዐቅም መመጠን

የማስተማር ዘዴ፣ ልዩ ሥልጠና የሚያስፈልገው፣ ጥልቀትና ምጥቀት ያለው ሙያ እንደሆነ ይታመንበታል፡፡ በዚህ ሙያ የሚመደቡ መምህራንም የሥነ ልቡና ጠበብት በመባል ይታወቃሉ፡፡ ሙያቸውን በተግባር ለመተርጎም የሚጠበቅባቸው ጥረት ልዩ ነው፡፡ ትምህርታቸውን ከሰው ኅሊና ለመቅረጽ የእያንዳንዱን ሰው ማንነት ፍላጎትና አቅም ይለካሉ፡፡ ሰውን ወደ ትምህርት የሚያገቡት በመናገር ብቻ ሳይሆን ሰውን በመምሰል ነው፡፡ ይህንኑ ብልሃት ቅዱስ ጳውሎስም ሲጠቀምበት እንመለከታለን፡፡

6ኛ/ የሚገባ ተግሣፅ

ብዙ ሰዎች ተግሳፅ አስፈላጊ አይደለም፣ የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ ነገር ግን ተግሣፅና ምስጋና ጊዜያቸውን ጠብቀው ሲነገሩ እኩል አገልግሎት አላቸው፤ምስጋና አለቦታው ገብቶ ሲነገር የሚጎዳውን ያህል ተግሣፅም አለቦታውና አለጊዜው ሲነገር ይጎዳል፡፡ ምስጋና በሚጋባ ሲነገር የሚጠቅመውን ያህል ተግሣፅም በአግባቡ ሲነገር ጥቅሙ በእጅጉ የጎላ ይሆናል፡፡

7ኛ/ ምእመናንን ማበረታታት

ምእመናን በሃይማኖት የጸኑ፣ በምግባር የቀኑ ይሆኑ ዘንድ በሞራል ሊገነቡ ይገባል፡፡ እንደዚህ ሲባል ግን ከላይ እንደተጠቀሰው በእውነት ላይ የተመሰረተ ምስጋና፤ ሞራላቸውን ይገነባል ለማለት እንጂ ባልሰሩት ይመስገኑ ማለት አይሆንም፡፡ የማይገባ ምስጋና ስድብ ነው፡፡ የሚገባ ምስጋና ግን ትልቅ ሽልማት ነው፡፡