የኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ስብከተ ወንጌልን እንቅስቃሴን አስመልክቶ ውይይት አደረገ

                                                                                    በሚድያ ክፍሉ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኘው የኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ በቀን 29/02/2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡

በውይይቱ ላይ የሀገረ ስብከቱና፣ የክፍለ ከተማው ሠራተኞች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ የውይይቱ አጀንዳዎች ሁለት ሲሆኑ የመጀመሪያው ጥናታዊ ጽሑፍ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስብከተ ወንጌልን በመተለከተ ነው፡፡ በመጀመሪያው ክፍል በክፍለ ከተማው አዘጋጅነት መጋቤ ሐዲስ ሮዳስን በመጋበዝ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን የብራና መጻሕፍት ይዞታቸውና ያካተታቸው ምሥጢራትና በባሕር ማዶ ስለሚገኙት መጻሕፍት በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ጥናታዊው ጽሑፉ በውስጡ ብዙ ነገሮችን ያካተተ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የግዕዝ ትምህርት  በባህር ማዶ ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ መሆኑ፣ በብራና ተከትበው ስለሚገኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት፣ የጸዋትወ ዜማ መጻሕፍ፣ የጸሎትና የምስጋና መጻሕፍት፣ መጻሕፈተ ሊቃውንትት መጻሕፍተ መነኮሳት ፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የታሪክ መጻሕፍት፣ ገድለ ቅዱሳን፣ ድርሳናት፣ የፍልስፍና መጻሕፍት፣ የሒሳብ መጻሕፍት ፣ የራዕይ መጻሕፍት፣ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም በጥናቱ ውስጥ አብዛኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጥንት የብራና መጻሕፍት በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ የውጭ ሰዎች ከአገር ውስጥ  ወደ ውጪ ተዘርፈዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል በኢንግላንድ ሀገር 850፣ በጣሊያን 1100፣ በፈረንሣይ 1034፣  በጀርመን 737፣ በኔዘርላንድ 180፣ በስዊድን 88 የብራና መጻሕፍ እንደሚገኙ ጥናቱ ያሣያል፡፡ በጥናቱ መጨረሻም የጥናቱ አቅራቢ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ጠቆም አድርገዋል፡፡ የተዘረፉት የብራና መጻሕፍት እንዲመለሱ ቢደረግ፣ ለቀሩት ደግሞ ከፍተኛ እንክብካቤና ጥንቃቄ ቢደረግላቸው ቤተክርስቲያኒቷ የጥናትና ምርምር ማዕከሎችን ብትከፍት፣ ሁሉም የቤተክርስቲያን አገልጋይ የራሱን ኃላፊነት ቢወጣ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ጥናታዊ ጽሑፍን ያደመጡት ታዳሚዎችም በጥናቱ መደሰታቸውንና እነሱም የበኩላቸውን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ አስተያየታቸውንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡

ሁለተኛው የውይይት አጀንዳ ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ ሲሆን በአሁን ሰዓት በክፍለ ከተማው ያለውን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡ በመጀመሪያ ተግዳሮቶቹ የተጠቀሱ ሲሆን የመፍትሔ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡ ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያኒቷ ሕይወት እንደ መሆኑ መጠን ክፍለ ከተማው ይህንን በማሰብ መልካም የሆነ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን በዚያው መጠን ብዙ ተግዳሮቶች ተጠቅሰዋል፡፡ ወጥና ተከታታይ የሆነ ትምህርት አለመሰጠት፣ የሰባኪያን ጥራትና ችግር ማለትም በቂ የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው ሰባኪያን መኖር፣ ችሎታ የሌላቸው ስብከተ ወንጌል ላይ መመደብ እና የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍስህት ግርማ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ንግግራቸውንም ስብከተ ወንጌል ከሌለ ሕይወት የለንም በማለት ጀምረው ለወንጌል ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለብን አሳስበዋል፡፡ የቤተክርስቲያኒቷ ሕይወት ወንጌል ነው፣ ሁላችንም ስብከተ ወንጌል ላይ መረባረብ አለብን በማለት ሁሉንም የሚያነቃቃ  ንግግር ተናግረዋል፡፡ ሰባኪ የሚሰብከው በመድረክ ብቻ ሳይሆን በሕይወቱም ጭምር ስለሆነ ሰባኪያንን ምግባራቸው ላይ ትልቅ ትኩረት መሰጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በሌላ መልኩ በውይይቱ ላይ የተገኙት ባህታዊ ሊ/ት ገ/መስቀል የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡

ከላይ እስከ ታች ጥሩ መዋቅርና ቅንጅት ቢኖር፣ ሥራና ሠራተኞች ቢገናኙ፣ እሁድ እሁድ ዘወትር ከቅዳሴ በኋላ ሰፊ ጉባኤ በሁሉም ገዳማትና አድባራት ቢሰጥ፣ በንግሥ ወቀት ለዝማሬና ለገቢ ማሰባሰብ ብቻ ጊዜ ከሚሰጥ ይልቅ ለወንጌልም በቂ ጊዜ ቢሰጥ፣ በክፍለ ሀገር ለሚገኙ የገጠር አብያ ክርስቲያናት ሰባኪያነ ወንጌል በቂ የደሞዝ ጭማሪና አበል ቢደረግ የሚሉትን ሃሳቦች ጠቁመዋል፡፡

የክፍለ ከተማው የስብከተ ወንጌል ሐላፊ መ/ር ዘላለም የክፍለ ከተማውን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ አስመልክቶ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም ሊቀ ኅሩያን ሰርጸ አበበ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ዋና ኃላፊ የሆኑት ለተግዳሮቶቹ መፍትሔ በጋራ መስጠት አለብን በማለት ለታዳሚው ተናግረዋል፡፡ ሁላችንም ሓላፊነት ተስምቶን የደከመውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በእጅጉ ማጠናከር አለብን ብለዋል፡፡ መዋቅራችንንም ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ ገዳማትና አድባራት ድረስ ግንኙነታችንን አጠናክረን በመናበብ የተሰጠንን መለኮታዊ አደራ መወጣት አለብን በማለት ውይይቱ በዚሁ ተጠናቋል፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *