የ2012 ዓ/ም ዓመታዊ የፐርሰንት አሰባሰብን አስመልከቶ ውይይት ተካሄደ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብሰባ አዳራሽ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ፤ የሀገረ ስብከቱ የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፤የሁሉም ክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች እንዲሁም የአድባራትና ገዳማቱ አስተዳዳሪዎች፤ ሊቃነ መናብርትና ሒሳብ ሹሞች በተገኙበት ዓመታዊ የፐርሰንት ገቢ ካላጠናቀቁ አድባራትና ገዳማት ጋር ውይይት ሰኔ 4/2012 ዓ/ም ተደርጓል፡፡
ወቅታዊውን የኮረና ወረርሽኝ ለመከላከል ሲባል የውይይት መርሐ ግብሩ ጠዋትና ከስአት በሁለት ክፍለ ጊዜ የተደረገ ሲሆን የውይይቱን መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት የሀገረ ስብከቱ ሒሳብና በጀት ዋና ኃላፊ ፈለገ ጥበባት መ/ር አብርሐም ያለንበት ወቅት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ አስረጅ የሚያስፈልግ አይደለም፤ሁላችንም ተጨንቀናል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከሚሰበስበው ዓመታዊ ገቢ በርካታ የገጠር አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን፤መንፈሳዊ ኮሌጆችንና የአብነት ት/ቤቶችን ከመርዳቱም ባሻገር የቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆኑ እንደ አንድ ሀገረ ስብከት የሚታይ አይደለም፤ ስለሆነም ችግሩን እየተረዳዳን የፐርስት ገቢ ሊሰበሰብ ይገባል ብለዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ ገብርኤል ነጋሽም ባደረጉት አጭር የመክፈቻ ንግግር በዚህ ስአት በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ ይገባናል፤ ነገር ግን ለውይይት የጠራናችሁ በመነጋገርና በመወያያት ችግሮች ይፈታሉ፤ ለወደፊትም በር ከፋች የሆኑ የመፍትሔ ሐሳቦች ይገኛሉ ብለን ስላሰብን ነው፤ በአሁኑ ስአት በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ለተቀመጠ የሥራ ኃላፊ ነገሮች ያስጨንቃሉ፤ወቅታዊው ወረርሽኝ በየመዋቅሩ ያለውን ያልተመጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አስተዳደር የምናስተካክልበት፤ዛሬ ላይ ቆመን ነገን የምንቃኝበትን ትምህርት የሰጠን የማንቂያ ደውል መሆኑን ተረድተን በመወያየት ለችግሮቻችን መፍትሔ እንስጥ በማለት ውይይቱን ከፍተዋል፡፡

የስብሰባው ተሳታፊዎችም ከወቅቱ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉባቸው እና ሕዝበ ክርስቲያኑም ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚመጣበት ጊዜ ከጸጥታ አካላት ጋር ችግር እየተፈጸመባቸው እንደሆነ በማብራራት የሀገረ ስብከቱ ድርሻ የሆነውን ከመቶ ሃያ ፐርሰንት መከፈል እንዳለበት አምናው አሁን ግን ለመክፈል እንደተቸገሩ ገልጸዋል፡፡ ከተሰብሳቢዎች መካከልም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የሚከበርበትን ሥራ ወጥ በሆነ መልኩ ሀገረ ስብከቱ እንዲሠራላቸው አሳስበው ያልተጠናቀቀውን የፐርሰንት ገቢ እስከ ሰኔ ሰላሳ እንደሚያስገቡ አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ ገብርኤል ነጋሽ ሀገረ ስብከቱ ያሉበትን የአሠራር ክፍተቶች ለማስተካከልና የባለ ጉዳይ ቅሬታዎችን በሚገባ ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩ የሁላችን ነው፤ ችግሩን ለመፍታት እና ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣት ሁላችን ግዴታችንን እንወጣ፤ እስከ ሰኔ ሰላሳ ድረስ ያለባችሁን ያልተጠናቀቀ የሀገረ ስብከት የሃያ ፐርሰንት ድርሻ አስገቡ በማለት አባታዊ መመሪያ አስተላልፈው ውይይቱ በጸሎት ተዘግቷል፡፡

መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *