የ2012 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ መርሐ ግብር ተካሄደ

ግንቦት 28/2012 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ፤ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስከያጅ እና የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት “ዛፍ ለምድራችን ልብስና ደም ስር ነው፣ ዛፍ ከሌለ ምድሪቱ ጤነኛ አትሆንም ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከህጻን እስከ አዋቂ ዛፍ መትከል አለበት፡፡ ተክሎ መሄድ ብቻ ሳይሆን እንክብካቤ ማድረጉም ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል፡፡

ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ በበኩላቸው በዛሬው እለት የተተከሉት ችግኞች አድገው ዛፍ ብቻ ሳይሆኑ ፍሬ የሚሰጡ እና ለምግብነት የሚውሉም ናቸው ብለዋል፡፡
አዳዲስ ችግኞችን ከመትከል በተጨማሪ የተተከሉትን በአግባቡ የመንከባከቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኢ/ር ታከለ ተናግረዋል፡፡

የችግኝ ተከላው መርሐ ግብሩ የተካሄደው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዘጋጀት ቤት ሲሆን በዘንድሮ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 5 ቢሊዮን ችግኝ፣ በአዲስ አበባ ደረጃ ደግሞ 7 ሚሊዮን ችግኝ ይተከላል ተብሎ ይጠበቃል።

በ2011 ዓ.ም በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ በሀገረ አቀፍ ደረጃ በ20 ሚሊዮን ዜጎች 4 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በአንድ ቀን እስከ 354 ሚሊዮን የሚደርሱ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 84 በመቶ መጽደቃቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *