“ይኩንኪ በከመ ተአመንኪ” /እንዳመንሽ ይሁንልሽ/ ማቴ.15፥28

ይህ ቃል ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለከነናዊት ሴት የተናገረው ቃል ነው፡፡ ታሪኩም /በማቴዎስ ወንጌል ም.15፡21-28/ ላይ ይገኛል፡፡ ታሪኩም እንደሚከተለው ተገልጻል፡፡
“ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ፡፡ በዚያም ከነናዊት ሴት ጌታ ሆይ! የዳዊት ልጅ ማረኝ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዟታል ብላ ጮኸች፡፡ እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም፡፡ ደቀመዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት፡፡ እርሱም መልሶ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ፡፡ ይህም ማለትትምህርት፣ መምህር አጥተው የተጎዱ እስራኤልን ላስተምር ሰው ሆኛለሁ ማለቱ ነው፡፡ እርሷ ግን ጌታ ሆይ፡- እርዳኝ እያለች ሰገደችለት፡፡ እርሱ ግን መልሶ የልጆችን እንጀራ ለውሾች መስጠት አይገባም አለ፡፡ እርስዋም አዎን ጌታ ሆይ፡- ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይባላሉ አለች” የልጆችን እንጀራ ለውሾች መስጠት አይገባም ሲል የምስጢር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ቃል አባቶቻችን ሊቃውንት ሲያመሰጥሩት ለእስራኤል የማደርገውን ተአምራት ለአሕዛብ አላደርገውም ማለት ነው፡፡ ይህች ከነናዊት ሴት ከአሕዛብ ወገን ናትና፡፡ እርሷም የሰጠችው መልስ ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፡፡ የዚህም ምስጢር ለእስራኤል ደጋጉን ተአምራት ብታደርግላቸው ለኔ ደግሞ ጥቃቅኑን ተአምራት አታደርግልኝም? ማለት ነው፡፡

በዚህን ጊዜ የምሕረት ባለቤት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልሶ አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅነው፡፡ “ይኩንኪ በከመ ተአመንኪ” /እንዳመንሽ ይሁንልሽ አላት/ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ልጇ ዳነች፡፡
ሊቃውንት እንደሚያመሰጥሩት ይህች ከነናዊት ሴት ሦስት ነገሮችን ይዛ ስለተገኘች ልጇ ድናላታለች፡፡ እነዚህም ሦስት ነገሮች ሃይማኖት፣ ትሕትና፣ ጥበብ ናቸው፡፡ ሃይማኖት፡- ልጄን ያድንልኛል ብላ ሳትጠራጠር በፍጹም እምነት መቅረቧ ነው፡፡ ትሕትና፡- “የልጆችን እንጀራ ለውሾች መስጠት አይገባም” ሲላት ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” በማለት መልስ መስጠቷ ነው፡፡
ጥበብ፡- “የልጆችን እንጀራ ለውሾች መስጠት አይገባም” ብሎ በምሳሌ ሲነግራት ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” በማለት በምሳሌ መመለስ መቻሏ ነው።

መጀመሪያ ከሃይማኖት ስንጀምር ይሆንልኛል ይደረግልኛል ብሎ በክርስቶስ አዳኝነት አምኖ መምጣት ትልቅ እምነት ነው፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወት መሠረቱ እምነት ነው፡፡ እየተጠራጠርን የምናቀርበው ልመና ከደመና በታች ነው የሚቀረው ለዚህም ቅዱስ ያዕቆብ የተናገረው ቃል ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ ይህም “ጥበብን ያጣት ሰው ቢኖር ሳይነቅፍና ሳይነፍግ ለሁሉ በልግስና የሚሰጥ እግዚአብሔርን ይለምን፡፡ ለእርሱም ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን አምኖ ይለምን አይጠራጠርም የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና ለዚያ ሰው ከእግዚአብሔር ምንም የሚያገኝ አይምሰለው ሁለት ልብ የሆነ ሰው በመንገዱ ሁሉ ይታወካልና” /ያዕ. 1፡5-8/ በዚህ መሠረት እንደዚች ከነናዊ ሴት እምነተ ጠንካራ መሆን ያስፈልጋል፡፡

ሁለተኛ ይህች ከነናዊት ሴት ይዛ የተገኘችው ትሕትናን ነው፡፡ ትሕትና ራስን ዝቅ አድርጎ ሌላውን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላልና” /ሉቃ. 14፡11/
ትሕትናን መጀመሪያ ያስተማረን የትሕትና ባለቤት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱ ፍጹም ትሕትና ነው፡፡ “አትሒቶ ርእሶ ነሥአ አርአያ ገብር ወተመሰለ ከመ ብእሲ” ራሱን ዝቅ አድርጐ የሰውን ሥጋ (የተገዢን) ሥጋ ተዋሐደ እንደ ሰውም ሆነ እንዲል /ፊልጵ.2÷7/ እንዲሁም የጸሎተ ሐሙስ ዕለት “እንግዲህ እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም እንዲሁ የባልንጀሮቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል፡፡ እኔ እንደ አደረግሁላችሁ እናንተም ልታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” /ዮሐ. 13፡ 14-15/ ሲል ለደቀ መዛሙርቱ ስለትሕትና አስምሯቸዋል፡፡ ስለዚህ እኛም ይህን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ የትሕትና ሰው መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ከፍ ያደርገናል በአንጻሩ ትዕቢትን ገንዘብ ካደረግን ደግሞ ዝቅ እንላለን፡፡ ይህንንም ቅዱስ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” /ያዕ. 4፡6/ በዚህ መሠረት ከላይ ታሪኳ እንደተገለጸው ከነናዊት ሴት ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍ እንዲያደርገን ትሕትናን ገንዘብ እናድርግ፡፡
ሦስተኛ ይህች ከነናዊት ሴት ይዛ የተገኘችው ጥበብን ነው፡፡ ጥበብን መያዝ እንደሚገባ ታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን እንደሚከተለው ተናግሯል፡፡ “በላ ለጥበብ እኅተ ዚአየ” /ጥበብን “አንቺ እኅቴ ነሽ” በላት/ /ምሳ. 7፡4/
“የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” /መዝ. 110፡10 /ምሳ. 9፡10/ የጥበብ (የእውቀት) መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት ማለት ደግሞ ኃጢአት ብሠራ እግዚአብሔር በነፍስም በሥጋም ይፈርድብኛል ብሎ ከኃጢአት ርቆ የጽድቅ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ስለዚህ በነፍስም በሥጋም እንዳይፈረድብን እግዚአብሔርን በመፍራት መኖር ያስፈልጋል፡፡
በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እንድናገኝ እንደዚች ከነናዊት ሴት ሃይማኖትን፣ ትሕትናን፣ ጥበብን ይዘን እንገኝ፡፡
ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ /ቀሲስ/ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ስርጭት ኃላፊ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *