ጎተራ አካባቢ የሚገኘው ጥንታዊው የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ሕንጻ ቤ/ክ እድሳት ሊካሄድለት ነው

በዛሬው ዕለት መጋቢት 11 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ፣ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ-ክርስቲያን አስተዳደሪ መልአከ ፀሐይ ተስፋ ማርያም ነጋሽ፣ የደብሩ ማኅበረ ካህናት እና የደብሩ የሰ/ት/ቤት መዘምራን ወጣቶች እንዲሁም በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በአባቶች ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቦ፣በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶ ጽላቱ ከዋናው ቤ/ክ ወደ ተዘጋጀለት መቃኞ የገባ ሲሆን እድሳቱም በፍጥነት እንደሚጀመርና ግንቦት 11/2013 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል። ስለሆነም የሚመለከተው አካል ሁሉ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ከደብሩ ጥሪ ቀርቧል።

በመርሐግብሩ ላይ የደብረ አስተዳደሪ መልአከ ፀሐይ ተስፋ ማርያም ነጋሽ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መመሪያ ሰጪነት በሀገረ ስብከቱ እየተከናወኑ ያሉትን መልካም ሥራዎች ለምእመናን ገለጻ አድርገዋል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ሕንጻ ቤ/ክ እድሳት ቢዘገይም አሁን መጀመሩ መልካም እንደሆነ ገልጸው ሕንጻ ቤተክርስቲያንን የማነጽና የማደስ ትልቁ ዓላማ በኅብረት በመሆን እግዚአብሔርን ለማምለክ፣ ኪዳን ለማድረስ፣ ለማስቀደስ፣ ሥጋውን ደሙን ለመቀበል፣ ወንጌልን ለምእመናን ለማሰተማር እንደሆነ አብራርተው እድሳቱ በታቀደው መሠረት እንዲጠናቀቅ መመሪያ አስተላልፈዋል።

በተያያዘ ዜናም በጠቅላይ ቤተክህነትና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዕውቅና አግኝቶ በየዓመቱ በዐቢይ ጾም “አውደ ወንጌል ዘኦርቶዶክስ” በሚል ስያሜ የሚዘጋጀው “የአድባራትና የገዳማት የአንድነት ጉባኤ” ዘወትር በደብሩ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተነግሯል። ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያን የጀርባ አጥንትና ዋና ተልዕኮዋ ስለሆነ መርሐግብሩ በሁሉም አድባራትና ገዳማት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንዖት ተሰጥቶ መልእክት ተላልፏል።

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ