ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2010 ዓ.ም የልደት በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

pp009

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

-በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤

-ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤

-የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤

-በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤

-እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በልደቱ፣ ፍጻሜ የሌለው ሰላምን ያበሠረን፤ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!

ወአልቦ ማኅለቅት ለሰላሙ፤ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም፤(ኢሳ.9:7)

በዚህም ዓለም ይሁን በወዲያኛው ዓለም፣ በግዙፋኑም ይሁን በረቂቃኑ ፣ በኃያላኑም ይሁን በድኩማኑ፣ በሀብታሙም ይሁን በድሀው በአጠቃላይ በተንቀሳቃሹ ፍጡር ሀልዎት ውስጥ መቀጠል የሰላም አስፈላጊነት ከሌላው ጸጋ ሁሉ የላቀ ነው፣ሰላም ካለ ሌላው ሁሉ የትም አያመልጥም፤ ሰላም ካለ ድህነቱም ይቀረፋል፣ ጕድለቱም ይሟላል፣ልማቱም ይስፋፋል፣ዕድገቱም ይረጋገጣል፣ ፍትሕ ርትዕም ይሰፍናል፤ ወንድማማችነቱም ይጸናል፤ አንድነቱም ይረጋገጣል፣ ሰላም በዕለት ተዕለት ሥራችንና በምድራዊ ሕይወታችን በሚሆን ገጠመኝ ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪ ጋር በሚኖረን ግንኙነትም ዓቢይ ትርጉም አለው፤ ለሰላም ህልውና መጠበቅ ትልቅ ስፍራ ያለው ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነውና ፍጡራን በሰላም እንዲኖሩ መለኮታዊ መልእክቱን ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን መሥዋዕትነትም ከፍሎበታል፤ ለዚህም ዋናው ማስረጃችን የአምላክ ሰው መሆንና በሰው አካል በዚህ ዓለም ተገልጾ ስለ ሰላም የሰጠው ጥልቅ ትምህርት ነው፡፡

በትምህርትም በተግባርም እንደምንገነዘበው በሰዎች ግብታዊ ድርጊትም ሆነ፣ ሆን ተብሎ በሚፈጸም ማስተዋል የጎደለው ክንዋኔ ሰላም ሊደፈርስ ይችላል፤ በአንጻሩ ሰዎች በማስተዋል፣ አርቆ በማሰብና በብዝኃ ትዕግሥት በሚመሩት ጤናማ ሕይወት ሰላም ሊፀና ሊሰፋና ወደ ላቀ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል፡፡

በየዓመቱ የምናከብረው የጌታችን በዓለ ልደት ይህንን ሐቅ ቊልጭ አድርጎ ያሳየናል፣የበዓሉ ታሪካዊ መነሻ እንደሚነግረን የቀደሙ ወላጆቻችን ማለትም አዳምና ሔዋን ለሕይወታቸው ጠቃሚ የሆነው ሕገ እግዚአብሔር በውል ተነግሮአቸው እያለ በጎን የመጣውን የጠላት ምክር ተቀብለውና ሆን ብለው ትእዛዙን ስለተዳፈሩ ሰላም ሊደፈርስባቸው ችሏል፡፡

በመሆኑም ያደፈረሱት ሰላም ቅጣትን አስፈርዶ ዕርቃናቸውን አስቀራቸው፤ በሐፍረት አከናነባቸው፤ መሠወር ባይችሉም መሸሸግንና መሸፋፈንን እንደ አማራጭ ዘዴ ሊጠቀሙ ሞከሩ፣ እውነተኛው ዳኛ ለምን ሰላሙን አደፈረሳችሁ ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ምክንያቶችን ቢደረድሩም በቀጥተኛው ሕግ ፊት ማምለጫ አላገኙም፤ ምክንያቱም ሰላምን አደፍርሰው ሞትን እንዳይጎትቱ ማስጠንቀቂያው ከበቂ በላይ በግልፅ ተነግሮአቸው ነበርና ነው፡፡

የጉዳቱ መጠን በዚህም አላበቃም፣ በእነሱ ጠንቅ ዘራቸውም  ተቀጣ፣ በምድር ላይ የሚገኙ ፍጥረታትና ምድሪቱም ራስዋ በከባድ መርገም ተቀጣች፤ በዚህም ምክንያት የሰው ሁለንተናዊ ሕይወት ዘላቂና እውነተኛ ሰላምዋ የሆነው እግዚአብሔርን አጥታ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በተሳሳተ አምልኮና በተመሰቃቀለ ህላዌ እየታመሰች፣ ሞትና መቃብርም ያለማቋረጥ እየተናጠቋት፣ እግዚአብሔር ያዘጋጀላት ብሩህ ዓለም ተዘግቶባት በጨለማው ዓለም ውስጥ ስትማቅቅ ኑራለች፤ የዚህ ሁሉ መከራ መንሥኤው አንድና አንድ ብቻ ነበር፤ እሱም የሰላሙ ኃይል እንደዋዛ ከእጅዋ ማምለጡ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ የተወለደውና በዚህ ዓለም የተገለፀው ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም ብሎ በቅዱሳን ነቢያቱ ያናገረውን የማይታጠፍ ቃሉን ለመፈጸም ነው፡፡

ቅዱሳን መላእክትም በጌታችን ዕለተ ልደት በቤተ ልሔም ተገኝተው እግዚአብሔርና ሰው በመገናኘታቸው ሰላም በምድር ሆነ፤ ይህም በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ተከናወነ ብለው በመዘመር፣እረኞችም የመዝሙሩ ተጋሪ በመሆን ያሳዩት አንድነት የተነገረው ሰላም መፈጸሙን ያረጋገጠ ነበር ፡፡

በእርግጥም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሰላም መፈጠሩን ለመረዳት እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ከተገለጠበት ክሥተት የበለጠ ሌላ ማረጋገጫ ሊገኝ አይችልም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ልደቱ እስከ መዋዕለ ዕርገቱ ድረስ በፈጸመው የቤዛነት ተግባር፣ የደፈረሰውን ሰላም እንደገና በመመለስ በሰውና በሰው፣በእግዚአብሔርና በሰው፣በመላእክትና በሰው መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በመናድ ሰላማችንና አንድነታችንን እውን አድርጎአል፤ ከጨለማው ዓለም ብሩህ ወደሆነው ዓለም እንደገና መልሶናል፤ ይህ እግዚአብሔር በምሕረቱ ብዛት ለሰው ልጅ ያጎናጸፈው ትልቁ፣ ዘላቂውና ዘላለማዊው ሰላም ነው፤ እሱም እኔ  ሰላሜን እሰጣችኋሁ፤ እኔ የምሰጠው ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ያለ አይደለም  ብሎ የተናገረለት ሰማያዊ፣ ዘላለማዊና ሳይቀለበስ ለዘላለሙ ጸንቶ የሚኖረው፣ ከእርሱና ከፍጡራን ሁሉ ጋር የሚሆነውና መጨረሻ የሌለው  ሰላም ይህ በልደቱ ተጀምሮ በዳግም ምጽአቱ የሚደመደመው ታላቁ ሰላም ነው ፡፡

ይሁን እንጂ በምድርም ቢሆን ሰው ዛሬውኑ አዳምጦ፣ አስተውሎ፣ አምኖና ተቀብሎ በተግባር ቢያውለው ጌታችን የሰላም ትምህርቱን ለክርክር በማይዳርግ መልኩ ሰጥቶአል፤ እርሱም  ‹‹ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ  እናንተም እንደዚሁ አድርጉላቸው፤ በራስህ ላይ ሊደረግብህ የማትሻውን በባልንጀራህ ላይ አታድርግ፤ ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› የሚለው እውነተኛ የሰላም መንገድ ነው፤ ዛሬም ይህን ቃሉን ተቀብለን በተግባር ብንፈጽም ሰላማችን አስተማማኝና ዘላቂ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፡-

ሰላም ማለት የእግዚአብሔር ሕግ ማለት ነው፤ ሰላምን የፈጠረ፤ ከማንም አስቀድሞ ስለ ሰላም ያስተማረና አሰምቶ የተናገረ፤ ደጋግሞም ያስጠነቀቀ እግዚአብሔር ነው፤ቃሌን ብታደምጥ ብትጠብቀውም ሰላምህ እንደማያቋርጥ ወንዝ ይጎርፋል ያለ እርሱ ነው ፡፡

ይህም ማለት ዘላቂና ፍጹም ሰላም ያለው በእግዚአብሔር ሕግ ውስጥ መሆኑን ያሳያል፤ ይህንን ሕገ ሰላም አውቀን በታላቅ አክብሮትና ምስጋና ስንቀበለው ሰላማችን ዘላቂና አስተማማኝ ይሆናል ማለት ነው፤ ዘላቂና ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ሰላም በአንድ አጭር ዐረፍተ ነገር ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ›› ተብሎ ተነግሮናል፡፡

ይህ ዓቢይና መለኮታዊ የሰላም ሕግ ከተከበረ መለያየት፣ መጣላት፣ መጨካከን፣ መገዳደል፣ በየት መግቢያ ያገኛል? እግዚአብሔር የሚፈልገው ሰላም ምን ዓይነት እንደሆነ መመዘኛውና መለኪያው እኛ ራሳችንን የምንወደው ያህል ወንድሞቻችንንና እኅቶቻችንን መውደድ ነው፤ በዚህ ፍጹምና አምላካዊ ሕግ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረውን ሰው ሁሉ እንደራሳችን አድርገን እንድንወድ ታዘናል፤ እኛም አምነን ተቀብለናል፤ ይህንን የእግዚአብሔር ድምፅ ያልሰማ ሰው በሀገራችን በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ክፍለ ዓለም ይኖራል ብለን አንገምትም፤ነገር ግን የቀደሙ ወላጆቻችን የእግዚአብሔርን ድምፅ ወደጎን ትተው በመጓዛቸው እንደተጎዱ፣ ዛሬም የሰው ልጅ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚለውን ድምፅ ቸል በማለት አጥፍቶ በሚጠፋ ቊሳቊስ እየተጣላ የሰላሙን ጭላንጭል በገዛ ራሱ እያጨለመው ይገኛል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ሰላምን ለመጎናጸፍ ሁለት ዐረፍተ ነገሮችን መቀበልና ዘወትር ስለነሱ መዘመር በቂያችን ነው፣ እነርሱም እግዚአብሔር አምላክህን በሁለመናህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚሉት ናቸው፡፡

ይህች ፍቅር የእግዚአብሔር ጸጋ ሆና የተሰጠችን፣ ሌላ አማራጭና ተፎካካሪ የሌላት ፣ ኅሊናን ሁሉ የምትረታ ናት፣ምንጩ እግዚአብሔር የሆነ የሰላምና  የፍቅር ኃይል  ድንበር ፣ ወንዝ ፣ ቋንቋ  አይገድበውም፤ በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሙሉእ ሰላምን የሚሰጠው እግዚአብሔር ስለሆነ፣ አሁኑኑ እግዚአብሔርን ያድምጥ፤ ያዳመጠ ዕለታ ‹‹ወንድምህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ፣ ወንድምህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፣ ወንድምህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› የሚል ቃል በተደጋጋሚ ከአምላኩ አንደበት ይሰማል፣ እርሱን ተቀብሎ በተግባር ሲያውል እግዚአብሔር አምላክህን በሁለመናህ ውደድ የሚለው ፍቅር በሕይወቱ ይገለጻል፤ በእርሱም ፍጹም ሰላም ያገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ በዓለ ልደቱን ስናከብር እርሱ እንደራራልን እኛም የእርሱን ፈለግ ተከትለን የተራቡትን፣ የተጠሙትን፣ የታረዙትንና የተፈናቀሉትን በመርዳት እንዲሁም ቀኑ የሁሉም ወገን የደስታ ቀን እንዲሆን በማድረግ ልናከብር ይገባል፡፡

በመጨረሻም

ጅብ በቀደደው እንደተባለው ዘላቂ የሆነ የጋራ ጥቅማችንን ሳናይ በምንፈጥረው ስሜታዊ ክፍተት ተጠቅመው ታላቅነታችንንና ዕድገታችንን የማይሹ ኃይሎች ከሕዳሴው አጀንዳችን እንዳያናውጡን ኢትዮያውያን የሆን ሁላችን፣ ከሃይማኖታችን ያገኘነውን ቅዱሱና ሰላማዊው የአንድነት ሀብታችንን ጠብቀን፣ ቂምንና በቀልን አርቀን የውስጣችንን ክፍተት ራሳችን በራሳችን አርመን በአንድነት በሰላምና ፍጹም በሆነ ወንድማዊ ፍቅር ቀጥ ብለን በመቆም ወደፊት እንድንቀጥል በእግዚአብሔር ስም መንፈሳዊመልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የልደት በዓል ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ፡፡

‹‹ወስብሐት ለእግዚአብሔር››

አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ፣

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣

ታኅሣሥ ፳ ቀን ፳፻ወ ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ፤