በዚህ ዘመን ለመብል የሚሞት ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ትንሣኤ የሚሞት አባት/ጳጳስ ያስፈልጋል ተባለ

የ2013 ዓ/ም የጌታችን ትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የእንኳን አደረሶት ዝግጅት በሀገረ ስብከቱ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

በዝግጅቱ የተገኙት በሰሜን አመሪካ የካልፎርንያ አከባቢ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ትምህርት ሰጥተዋል።

ጌታችን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? ብሎ ጴጥሮስን ሲጠይቀው “አዎን ጌታ ሆይ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” ሲለው “ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ” የሚል ትልቅ ሐላፊነት አሸከሞታል ብለዋል።

የዛሬ ጴጥሮሶች እኛው ነንና ሓላፊነታችን ልንወጣ ይገባል ያሉት ሊቀ ጳጳሱ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ፈተና ውስጥ ስለ ሆነች ሓላፊነታችን በመወጣት ተሎ ልንደርስላት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሊቀ ጳጳሱ አስቀድመን ግን ራሳችን እንመርምር ካሉ በኋላ በዚህ ዘመን ለመብል የሚሞት ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ትንሣኤ የሚሞት አባት/ጳጳስ እንደሚያስፈልግ ሳይጠቁሙ አላለፉም ።

በዝግጅቱ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ዘመን በሀገረ ስብከቱ የተከናወኑ ሥራዎችን ተዘርዝሯል።
ከነዚህ መካከል፦ ሀገረ ስብከቱ በዕቅድ እንዲመራ መደረጉ፤ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች አስፈላጊ ሥልጠናዎች መውሰዳቸው፤ ብዙ ሥር ነቀል ለውጥ መከናወናቸው፤ የሀገረ ስብከቱና የአድባራቱ ሠራተኞች ተመጣጣኝ ክፍያ/ደሞዝ እንዲያገኙ መደረጉና ብዙ መልካም ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተገልጿል።

ይህ ዝግጅት ሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ በራሱ ሊቀ ጳጳስ መመራት ከጀመረ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ መርሐ-ግብር መሆኑንም ተገልጿል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅም ወቅቱ ጌታችን በሞቱ ሞታችን ደምስሶ ነጻነታችን ያስገኘልን ስለ ሆነ የምስጋና ቀን ነው። ዘመነ ፈሲካ እንኳን አደረሳችሁ የምንባባልበት ወቅት ነው። ልዩነቱ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ነው ብለዋል።

ብፁዕነታቸው በዓሉ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በዓል እንጂ የግል ሰው በዓል አለመሆኑንም ገልጸዋል።

በዝግጅቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱና የሰባቱ ክፍላተ ከተማ የየዋና ክፍል ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አለቆች፣ ጸሓፊዎችና ሊቃነ መናብርት ተገኝቷል።

በሊቃውንትና በሰንበት ት/ት ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዜማና ቅኔም ቀርቧል።

ዘጋቢ መ/ር ኪደ ዜናዊ

ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

በቦሌ ደ/ገ/ቅ/ጊዮርጊስ እና ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ ዕረፍት በድምቀት ተከበረ

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በቦሌ ደ/ገ/ቅ/ጊዮርጊስ እና ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ጊዮርግስ በዓለ ዕረፍት በድምቀት ተከብሯል።

የ2013 የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ ዕረፍቱ ሚያዚያ 23 በሕማማት ውስጥ የዋለ በመሆኑ ክብረ በዓሉ ተሻግሮ ዛሬ ሚያዚያ 27/2013 ዓ/ም ተከብሮ ውሏል።

በዕለቱ በመጋቤ ሐዲስ ቆሞስ አባ ኒቆዲሞስ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራ የመጽሐፍ መምህር ትምህርት ተሰጥቷል።

መምህሩ ” መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ ።” (የሐዋ. ሥራ 1:8) በሚል መነሻነት በዓሉን በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል።

በክብረ በዓሉ በሊቃውንትና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በዓሉን በተመለከተ ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል።

በክብረ በዓሉ የተገኙት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለምእመናኑ ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል። ብፁዕነታቸው በዓሉን ስናከብር ቃሉን በማክበር በፍቅር እየተመላለስን በንስሓ ታጥበን ሥጋሁና ደሙ እየተመገብን ለዘለዓለም ሕይወት ተዘጋጅተን ልንኖር ያስፈልጋል ብለዋል።

በክብረ በዓሉ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አሰተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፣ መ/ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አሰኪያጅ፣ የደብሩ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ ካህናት አገልጋዮች፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።

ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

የትንሣኤን በዓል አስመልክተው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ያስተላለፉት መልእክት


የትንሣኤን በዓል አስመልክተው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ያስተላለፉት መልእክት

ተንሥአ በከመ ይቤ” (ማቴ ፳፰፥፮)
እንደ ተናገረ ተነሥቶአል (ማቴ 28፥6)


ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱና ዋነኛው የትንሣኤ በዓል ነው። ትንሣኤ “ተንሥአ” ከሚለው የግዕዝ ግስ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም መነሣትን ያመለክታል፤ ከሞት በኋላ በነፍስ ብቻ ሳይሆን በሥጋም ጭምር ሕያው ሆኖ መነሣትን የሚገልጽ ቃል ነው።


“ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው ” (1ኛ ጢሞ 1:15) ተብሎ እንደተጠቀሰው የክርስቶስ ወደ ምድር የመምጣቱ ዋነኛ ዓላማ እኛን ከኃጢአታችን ሊያድነን በመሆኑ ምክንያት ይህንኑ ቅዱስና መለኮታዊ ዓላማ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቶ ፈጽሞታል።
በሞቱ ሞታችንን ከደመሰሰ በኋላ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል። ቅዱስ መጽሐፍም የክርስቶስ ትንሣኤ በተዘገበበት በማቴዎስ ወንጌል ምስክርነቱን እንዲህ ሲል ያስቀምጣል፦ “መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ” (ማቴ 28፥5-6)። የክርስቶስ ቃል እንደሰው ቃል አይደለም። ሰው የተናገረውን ሊረሳ ይችላል፣ መርሳት ብቻም ሳይሆን ከአቅም ማነስ የተነሣ የተናገረውንም መፈጸምም ሊሳነው ይችላል። ክርስቶስ ግን የተናገረውን አይረሳም፤ ሁሉን ቻይ ነውና የተናገረውን ይፈጽማል።


ከስቅለቱ በፊት ከሞት እንደሚነሣ በተደጋጋሚ የተናገረው ጌታ ከሞት ተነሥቷል። መልአኩም በማለዳ ተነሥተው የክርስቶስን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ወደ መቃብር ለሄዱት ሴቶች የተናገረው ይህንኑ እውነት ነው። ምንም እንኳ እነርሱ የሄዱበት ዓላማ ሥጋውን ሽቶ ለመቀባት ቢሆንም ከሄዱበት ዓላማ የሚበልጠውንና ከደስታዎችም ሁሉ በላይ የሆነውን ደስታ ማለትም የክርስቶስን ትንሣኤ ሰምተው ተመልሰዋል።
የክርስቶስ ከሞት መነሣት የክርስትና ጽኑ መሠረት ከመሆኑም ባሻገር የክርስትናን ሕያውነት ያረጋገጠ ግልጽ መለኮታዊ ማስረጃ ነው። ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኩር ነው፤ በኩር ማለት የመጀመሪያ ማለት ሲሆን ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣቱ የትንሣኤያችን በኩር ሆኗል። ሐዋርያውም ” አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል ” (1ኛ ቆሮ 15:20) በማለት ማረጋገጫ ሰጥቷል።
አይሁድ በመቃብሩ ላይ ያስቀመጡት ድንጋይ ክርስቶስን ሊይዘው አልቻለም፣ መቃብሩን እንዲጠብቁ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ጥበቃዎችም እርሱን መጠበቅ አልቻሉም ምክንያቱም ክርስቶስ እነርሱን የሚጠብቅ እንጂ በእነርሱ የሚጠበቅ አይደለም። ድንጋዩን አንሱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ። መላእክቱም የእርሱን ከሞት መነሣት ስላረጋገጡ ወደ መቃብሩ ማልደው ለሄዱት ሴቶች “ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም” (ሉቃ 24፥5) በማለት ነግረዋቸዋል።


የእርሱ ከሞት መነሣት ለእኛ በኩራችን ነው። እኛም ሞተን በዚያው አንቀርም እንነሣለን። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል ” (ዮሐ11:25) በማለት ተናግሯል። የእርሱ መነሣት ለእኛ መነሣት ፍጹም ማረጋገጫ ነው።


የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ወቅቱ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የምናከብርበት ልዩ ወቅት እንደመሆኑ መጠን ሁላችንም እርሱ ከሞት የተነሣው መድኃኔዓለም የከፈለልንን የደም ዋጋ ከልብ በመነጨ እምነት በማሰብ ደግሞም በደም ዋጋ የተገዛን የራሳችን ሳንሆን የእርሱ የአምላካችን መሆናችንን መረዳት ያስፈልጋል።
ሲቀጥልም የሆነው ሁሉ በእርሱ መሆኑን አውቀን ከክርስቶስ በተሰጠን ጸጋ ሌሎችን በመርዳትና በማገዝ ማለትም የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጨነቁትን በመምከር፣ የታሰሩትን በመጠየቅ፣ በሀገራችን ብሎም በዓለም ላይ ሰላምን ላጡትና ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ዘርፈ ብዙ በሆኑ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙት ምእመናን በቻልነው መጠን ድጋፍንና ጸሎትን በማድረግ በዓሉን እንድናከብር አባታዊ መልእክቴን አስተላልፋለሁ::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ።

የኢየሱስ ክርስቶስን የስቅለት በዓል አስመልክተው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ያስተላለፉት መልእክት

ፍጹም ፍቅር

ጊዜው ከዛሬ 2000 ዓ.ም ገዳማ በፊት ነበር ዕለቱ ደግሞ ዕለተ አርብ ። ለዘመናት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ዕንቅፋት ሆኖ የቆየው የኃጢአት ግድግዳ የፈራረሰበትና በአንጻሩ ደግሞ ጽኑ የምሕረትና የጽድቅ ድልድይ የተገነባበት፣ በሥልጣን ላይ የነበረው ሞት በጊዜ ገደብ ምክንያት ሥልጣኑን ለሕይወት ያስረከበበት፣ ዓመተ ፍዳም ከአቅም ማነስ የተነሣ መንበረ መንግሰሥቱን ለመሪው ለዓመተ ምህረት የለቀቀበት ክስተቶች የተከናወኑበት ዕለት ነው። ታዲያ እነዚህ ሁሉ የሆኑት በዘፈቀደና በአጋጣሚ ሳይሆን በዕለቱ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው መለኪያ በሌለው ፍጹሞ በሆነ ፍቅር ነው።

ብዙ ጊዜ ሰው ሰውን ሲወድ መስፈርት ያስቀምጣል። ደም ግባትን፣ ዝናን፣ ሥልጣንን፣ የሥጋ ዝምድናን ወዘተ..። ለዚህም ነው አንድን ሰው እከሌን የምትወደው ለምንድነው ብለን ስንጠይቀው ምክንያቶችን የሚደረድርልን ። ከዚህ የምንረዳው እውነት ሰው ሰውን የሚወደው በሚለካ ነገር መሆኑን ነው። የክርስቶስ ፍቅር ግን ከዚህ ፍጹም ይለያል። ክርስቶስ ሲሞትልን ከእኛ የሚወደድ ነገር አግኝቶ አይደለም። እርሱ እንዲሁ ወደደን እኛን ለመውደድ ምክንያት አልፈለገም። መጽሐፍም እንዲህ ሲል ያረጋግጥልናል ” በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”(ዮሐ 3:16)።
በእምነት ከማስተዋል በስተቀር የክርቶስን ፍቅር ስፋቱን፣ ርዝመቱን፣ ከፍታውንና ጥልቅነቱን ለክተን ይህን ያህል ነው ብለን መግለጽ የምንችልበት መለኪያ መሣሪያ የለንም። ሐዋርያውም በመልእክቱ ” ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ “( ኤፌ 3:18-19) ይለናል። ፍጹም የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅና ለማስተዋል ዘወትር ቅዱስ ቃሉን ያለመታከት በጽኑ እምነት በማንበብ መትጋት ይኖርብናል።

በበደልነው ጊዜ አላጠፋንም ፤ ምሕረቱንና ቸርነቱን አበዛልን፤ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ነገር ሳይሆን ራሱን ነው በመስቀል ላይ አሳልፎ የሰጠን። መጽሐፉ ቅዱስ “አንዱ ስለሁሉ ሞተ” (2ኛ ቆሮ 5፥14) በማለት የክርስቶስን የፍቅር ጥግና ከፍታ ያስረዳናል። መዳናችን፣ ከዘለዓለም ሞት መትረፋችን፣ ከገሃነም እሳት ማምለጣችን፣ ሰላምና እረፍት ማግኘታችን በእርሱ በመድኃኔዓለም ቤዛነትና የደም ዋጋ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንዲህ ብሏል “ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን በጸጋ ድናችኋልና” (ኤፌ 2፥4-5 )። እኛ በበደላችን ሙታን በነበርን ጊዜ እርሱ ለእኛ ጸጋችን(ስጦታችን) ሆኖ ተሰቅሎ ሞቶ አዳነን።

በመጨረሻም በልባችን ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ቢኖር አባትና እናት ልጆቻቸው ቢታመሙ ሐኪም ወይም ጸበል ሊወስዷቸው ይችላሉ እንጂ ነፍሳቸውን ለልጆቻቸው አሳልፈው አይሰጡም። እርሱ መድኃኔዓለም ግን እራሱን አሳልፎ በመስጠት ከኃጢአት በሽታ አከመን። ደረቅ አዲስ ኪዳን በመባል የሚታወቀው ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ላይም እንደተገለጸው “በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” ይለናል። እኛ መቁሰል ሲገባን ፍቅር ባህርይው የሆነ ጌታ ስለእኛ ቆሰለ። ይህንን ፍጹም የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ዘወትር ያለመዘንጋት በእምነት በማሰብና እኛም በተሰጠን ጸጋ ለሌሎች በተግባር የሚገለጥ ፍቅርን በመስጠጥ መልካም በሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ልንጓዝ ይገባል በማለት አባታዊ መልእክቴን አስተላልፋለሁ።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

“በሞቱ ከመሰልነውም: በትንሳኤው እንመስለዋለን” ሮሜ. 6:5

ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፅ/ ቤት ሰራተኞች፣ ለገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ለሁሉም ምእመናን በያላችሁበት መልካም ሰሙነ ህማማት( የፀሎት፣ ስግደት እና የቅዱሳት መፃህፍት የንባብ ጊዜ) ይህንላችሁ::

ትንሳኤውን ለማየት በህማማቱ በኩል ማለፍ/ መሳተፍ እንደሚገባ ሲያመለክት ቅዱስ ጳውሎስ “ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከሞት፣ ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ከእርሱ ጋር እንነሳለን” ያለውን ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ታደርገዋለች: ስለሆነም የቤተክርስቲያናችን ቅፅሮችና በሮች በሰሙነ ህማማት በመአልትም በሌሊትም ተከፍተው ካህናት ከሌሊት ጀምረው ለሰሙነ ህማማት የተሰራውን ስርአተ ፀሎት፣ ስግደት፣ ንባባት እያደርሱ ቆይተው ሲነጋ ምእመናንም ከስርዓተ ፀሎቱ ተቀላቅለው አብረው ሲፀልዩ; ሲሰግዱና ከቅዱሳት መፃህፍት ስለ ክርስቶስ ህማምምና መከራ መስቀል እያነበቡ ይውላሉ: በዚህም የክርስቶስ የህማሙና መከራው አሳቢዎች ሳይሆን ተሳታፊዎች በመሆን ሳምንቱን አሳልፈው ወደ ትንሳኤው ይሸጋገራሉ::

እንግዲህ የተከበራችሁ ካህናት እና የተወደዳችሁ ምእመናን ሁላችንም በያለንበት ቅድስት የቤተክርስቲያናችን አባቶች የሰሩልንን ቀኖና እየፈፀምን: መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማህየዊት( አዳኝ) በምትሆን ህማሙ ከቁስለ ነፍስ ወስጋ; ከደዌ ነፍስ ወስጋ እንዲፈውሰን በዚህ ሰሙነ ህማማት እንትጋ::

መልካም ሰሙነ ህማማት


አባ መልከፄዴቅ የ አ/ አ/ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የሕማማትና የትንሣኤ በዓላትን አስመልክቶ መመሪያ አስተላለፉ!!

ሚያዚያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማና ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ የሰሙነ ሕማማትና የትንሣኤ በዓላት አከባበር መንፈሳዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
ከሆሳእና ጀምሮ ያሉት የሕማማትና የትንሣኤ በዓላት ልዩ ልዩና በርካታ መንፈሳዊ ሥርዓቶች የሚፈጸሙባቸው በዓላት በመሆናቸው ከአገልጋይ ካህናት ጀምሮ ሁሉም የበዓሉ ተሳታፊ ምዕመናን ራሳቸውን በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ከሚገኘውና ብዙ ወገኖቻችንን ካሳጣን የCovid-19 በሽታ ራሳቸውን እንዲጠብቁና የወጣውን አዲስ መመሪያ እንዲያከብሩና ከጸጥታ አካላት ጋር ተናበው የአካባቢያቸውን ሰላም ጠብቀው እንዲያስጠብቁ አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም ከበዓላት መከበር ጋር ተያይዞ የሚዲያ አካላት በዓሉን አስመልክተው የሚጋብዟቸው እንግዶች በትውውቅና በመጠቋቆም ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ በትክክል የሚያሰሙና ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ እንዲሆኑ በሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት በኩል ለሁሉም የሚዲያ አካላት ደብዳቤ መጻፉ አሳውቀው፡፡
ዘጋቢ፡- መ/ር ሽፈራው እንደሻው

በዓለ ሆሣዕና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ የሆሣዕና በዓል ነው፡፡ ስለዚህ በዓል አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፤ ከትንቢቶቹም አንዱ እንደሚከተለው ተጠቅሷል፡፡ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያና በአህያይቱ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” /ትን. ዘካ. 9፡9/
ከዚህም ጋር ስለበዓለ ሆሣዕና አራቱም ወንጌላውያን ጽፈዋል፡፡ ይህም፡- ማቴ. 21፡1-11፣ ማር. 11፡1-10፣ ሉቃ. 19፡28-40፣ ዮሐ. 12፡12-15 አራቱም ወንጌላውያን የጻፉት የበዓሉ ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጻል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፡፡ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ገና ማንም ያልተቀመጠባት አህያ ከውርንጫይቱ ጋር ታሥረው ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማንም ስለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ አላቸው፡፡ የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፡፡ እነርሱም አህያዋንና ውርንጫዋን ሲፈቱ የአህያው ባለቤት አህዮቹን ስለምን ትፈቷቸዋላችሁ? አላቸው እነርሱም ለጌታ ያስፈልጉታል አሉ ፈቀደላቸው ወዲያው አመጡለት፡፡ የታሠሩትን ፈትታችሁ አምጡልኝ ማለቱ ሰው ሁሉ ከኃጢአት ማሠሪያ የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ ነው፤ ደቀ መዛሙርቱም ልብሳቸውን በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ጎዘጎዙ የዚህም ምስጢር ኮርቻ ይቈረቍራል ልብስ አይቈረቍርም የማትቈረቍር ሕግ ሠራህልን ሲሉ፤ አንድም ልብስ በአካል ያለውን ነውር ይሸፍናል አንተም ከባቴ አበሳ /በደልን የምትሸፍን/ ነህ ሲሉ ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአህያዋና በውርንጫው ላይ በጥበብ በአንድ ጊዜ ተቀምጦባቸዋል ለእርሱ የሚሳነው ነገር የለምና፡፡ በአህያ የተቀመጠበት ምክንያት ደግሞ ቀድሞ ነቢያት ዘመነ ጸብዕ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው ይታያሉ፡፡ ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉና ዘመነ ሰላም ደረሰ ሲል ትንቢቱን ባወቀ አናግሯል ምስጢሩም በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም እሱም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝ አልታጣም ሲል ነው፡፡ ሲሄዱም ሕዝቡ ልብሳቸውን በመንገድ አነጠፉ፡፡ እንኳንስ አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ነው፡፡
እንዲሁም ሕዝቡ፣ ሕፃናቱ ሳይቀሩ ዘንባባ ይዘው የሚቀድሙትም የሚከተሉትም “ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር” /ለዳዊት ልጅ መድኃኒትን መባል ይገባዋል፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው/ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ያመሰግኑ ነበር፡፡ ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው፡፡ የዘንባባው ምስጢርም፡- አብርሃም ይስሐቅን፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፤ እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፣ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ ዘንባባ ይዘው እግዚአብሔርን አመስግነዋልና በዚህ መሠረት ሕዝቡ፡- የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲሄድ ዘንባባ ይዘው አመስግነውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሲያመሰግኑ ከሕዝቡ መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ መምህር ሆይ፡- ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ መልሶም እላችኋለሁ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግናሉ አላቸው፤ ድንጋዮች ሳይቀሩ አመስግነውታል፡፡ (ሉቃ. 19፥40)
በዚህ መሠረት ይህ በዓል የምስጋና በዓል ነው፡፡ እኛም ፈጣሪያችንን ሁልጊዜ ማመስገን አለብን የተፈጠርነውም ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ነው፡፡ ስሙን ለመቀደስ ማለት ስሙን ለማመስገን ማለት ነው፤ ክብሩን ለመውረስ ማለት ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ማለት ነው፡፡ የተፈጠርነው ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ስለሆነ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል፡፡ ምስጋናውም በፍጽም እምነት፣ በቅንነትና በንጹሕ ልብ መሆን አለበት፡፡ “እባርኮ ለእግዚአብሔር በኵሉ ጊዜ ወዘልፈ ስብሐቲሁ ውስተ አፉየ” /እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ ምስጋነውም ዘወትር በአፌ ነው/ /መዝ. 33፡1/
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመስግነን መንግሥቱን ለመውረስ እንድንችል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም የቅዱሳን አማላጅነታቸው አይለየን፡፡
ለበዓለ ሆሣዕና ያደረሰን አምላክ ለብርሃነ ትንሣኤውም በሰላም ያድርሰን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከላእከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ /ቀሲስ/
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በምሁር ኢየሱስ ገዳም የእኩለጾም (የደብረ ዘይት) ክብረ በዓል በድምቀት ተከብሮ ዋለ

በቀን 26/2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ፣ የጉራጌ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የገዳሙ አስተዳዳሪ መ/ር አባ ዘኢየሱስና በርካታ ምእመናን በተገኙበት ዓመታዊው የእኩለጾም (ደብረዘይት) ክብረ በዓል በምሁር ኢየሱስ ገዳም በድምቀት ተከብሮ ዋለ።
በገዳሙ ስር የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ሲሆን የአብነት ትምህርት፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት፣ የህጻናት ማሳደጊያ ማዕከል፣ የሙዚየም አገልግሎት፣ የእደጥበብ ማምረቻና መሸጫ ይገኛሉ።
በክብረ በዓሉ ላይ በአምስት መምህራንና በ12 ዓመት ህጻን ልጅ የዕለቱ ወንጌል ተነቦና ተተርጉሞ ተብራርቷል። የበገና ዝማሬም በበዓሉ ላይ ባማረ መልኩ ቀርቧል።
ብፁዕነታቸው ዕለቱን በተመለከተ በክብረ በዓሉ ላይ ለተገኙት ምእመናን ትምህርተ ወንጌል ያስተላለፉ ሲሆን ደብረ ዘይት የአምስተኛው ሰንበት መጠሪያ ስም መሆኑን ገልጸው ዕለቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ነገረ ምጽአቱን ያስተማረበት ስለመሆኑ አብራርተው ሁላችንም ዘወትር በንስሐ ሕይወት እየተመላለስን ዳግም ተመልሶ የሚመጣውን አምላካችንን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ተዘጋጅተን መጠበቅ እንደሚኖርብን አጽንዖት ሰጥተው አስተምረዋል፤ አባታዊ ምክራቸውንም አስተላልፈው።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳን ሰጥተው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል ።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በቦሌ ቡልቡላ ፈለገ ዮርዳኖስ ቅዱስ ሚካኤልና ተክለሃይማኖት አንድነት ገዳም በመገኘት ገዳሙ በተጠናከረ መልኩ እንዲገደም መመሪያን አስተላለፉ

በዛሬው ዕለት መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ከሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ ከክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጆችና ከአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ጋር በመሆን በቦሌ ቡልቡላ ፈለገ ዮርዳኖስ ቅዱስ ሚካኤልና ተክለሃይማኖት አንድነት ገዳም በመገኘት ገዳሙ ከዚህ በፊት ከነበረው ይበልጥ እንዲገደም መመሪያን አስተላለፉ።
በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ መመራት ከጀመረ በኋላ በአስተዳደር ሥራዎች፣ በልማት ሥራዎችና በመንፈሳዊ አገልግሎት የተሻለ ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸው ይህንን ገዳም ወደ ትልቅ ደረጃ ላይ ለማድረስ በሀገረ ስብከቱ ዕቅድ መያዙን አብራርተዋል። አያይዘውም ቦታው ለመንፈሳዊ ትምህርትና ለገዳማውያን ምቹ መሆኑን ገልጸው በቦታው የሚያገለግሉ ቀሳውስትና ዲያቆናት ወደ ሌላ አድባራትና ገዳማት ተዘዋውረው በእነርሱ ምትክ ገዳሙ ሙሉ በሙሉ በአባቶች መነኩሳት እንዲገለገል በሀገረ ስብከቱ ዕቅድ መያዙን አክለው አውስተዋል።
መርሐ ግብሩን የመሩት የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን በገዳሙ ውስጥ ከአባቶች መነኮሳት በተጨማሪ እናቶች ገዳማዊያትም እንደሚገኙ ጠቅሰው ክፍለ ከተማው ገዳሙን ይበልጥ ለማጠንከር ከምንጊዜውም በላይ ጠንክሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በገዳሙ የተገኙት የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች የቦታውን አቀማመጥ ለገዳማዊ ኑሮና ለመንፈሳዊ ትምህርት ምቹ መሆኑን ደጋግመው የገለጹ ሲሆን ገዳሙን ለማሳደግና ለማጠናከር በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል። በገዳሙ የሚገኙትን ቀሳውስትና ዲያቆናት ወደ ደብራቸውና ገዳማቸው ለመውሰድ መልካም ፈቃዳቸውንም ገልጸዋል።
ገዳሙን በመጀመሪያ ያቋቋሙት መ/መንክራት ኃይሌ አብርሃ የገዳሙን ታሪካዊ ደኃራ ለብፁዕነታቸውና በገዳሙ ለተገኙት ሁሉ አብራርተው ከአሁን በኋላም ላለው ሥራ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ ገዳሙን ለመገደም በሚደረገው ትብብር የተለያዩ አካላትን እንደሚያስተባብሩ ገልጸዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በዚህ አንድነት ገዳም ከዚህ በፊት ከሁለትም ሦስት ጊዜ በቦታው በመገኘት ቦታው ለገዳማውያን ሕይወትና ለአብነት ትምህርት ምቹ መሆኑን እንደተመለከቱ ጠቅሰዋል። ከሀገረ ስብከቱና ከክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እንደተመከረበትና ዕቅድ ተይዞ አሁን በፍጥነት ወደ ትግበራ እንደሚገባ አብራርተዋል። አያይዘውም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ስለሌለው እንደ እግዚአብሔር መልካም ፍቃድ በዚህ ገዳም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና እንዲሠራ ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው የክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙና ምእመናንን አስተባብረው ከገዳሙ አስተዳዳሪ መ/ኃ ቆሞስ አባ ቢኒያም ጋር በጋራ በመሆን የገዳሙ ሕንጻ ቤ/ክ በፍጥነት እንዲጀመር መመሪያ ካስተላለፉ በኋላ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ